በዝቋላ ገዳም የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር በሚዲያ የተሰራጨው ዜና ማረሚያ እንዲሰጥበት ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ
የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም.
በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ በመጋቢት ወር መጨረሻ የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር መስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋ መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነና ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመግለጽ የተላለፈው መረጃ እርማት እንዲደረግበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ለክቡር አቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ፡፡
“የሃይማኖቶች እኩልነት በታወጀበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕግ መንግሥት አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን እምነት መንቀፍም ሆነ መንካት እንደሌለበት ተደንግጓል” ያሉት ቅዱስነታቸው፤ በሚዲያ ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን የሚተላለፍ፤ የገዳሙን መናንያን መነኮሳትና በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያኖችን የሚያስቆጣ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ለተዘገበው ጉዳይ እርማት እንዲሰጥበት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ለክቡር አቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
ዝርዝሩን ከሚመለከታቸው አካላት እንደደረሰን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡