በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ክፍል አንድን  ማቅረባችን ይታወቃል ክፍል ሁለትን እነሆ ብለናል፡፡

ምዕራባውያንና የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ፈጽመዋል፡፡ የአሳባቸው አቀንቃኝ ኢትዮጵያዊ “ፈረንጆችንም” አግኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ሊቃውንቷንም ለመተቸት ያለ ስማቸው ስም ያለ ግብራቸው ግብር በመስጠት ጥላቻውን በመግለጽ አልሜዳ የተባለ ሚሲዮናዊ የፈጠራ ታሪክ ጽፏል፡፡ የእሱን ጥላቻ እየጠቀሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚተቹት የግብር ልጆቹ ናቸው፡፡ የእሱን ጥፋት ዳንኤል ክብረት «አልሜዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አምርሮ የሚጠላ ኋላ ቀርና በኑፋቄ የተሞላች አድርጎ የሚፈርጅ ኢየሱሳዊ /ሚስዮናዊ/ ነበር፡፡ በጽሑፎቹ ላይ ይህን ነው ሲያንጸባርቅ የኖረው፡፡ ከዚህ ጠባዩ አንጻርም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ቢተች የሚጠበቅ እንጂ የሚገርም አይደለም» (ዳንኤል፣ ፳፻፲፩፣፫‐፬) በማለት ገልጦታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆነ ተሐድሶአውያን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የሚተቹት የእሱን አሳብ እየጠቀሱ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መንቀፍና ያለ ግብራቸው ግብር መስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያስባሉ፡፡ ለኋለኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተችዎች ጀማሪና ፊታውራሪያቸው አልሜዳ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያንን አእምሮ በመበረዝ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትችት እንዲያዘንቡ ምክንያት መሆናቸውን ከአልሜዳ ጽሑፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ለመነሻ ያህል ይህን ካቀረብን በየዘርፉ የደረሱትን ችግሮች እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሀ. የቤተ ክርስቲያን መቃጠል፡- በየዘመናቱ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ ሙስሊሞች፣ በግለኝነት በታወሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠሉ ቆይተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የግል ጥላቻና የተለየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንጂ ሁሉም የሌሎች እምነቶች ተከታዮች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል አብረው የሚያዝኑና የሚያለቅሱ፣ ክርስቲያኖች ሲሳደዱና መከራ ሲደርስባቸው በቤታቸው የሚሸሽጉ ብሎም አብረው መከራ የሚቀበሉ፣ ክርስቲያኖች ኃይላቸውን እያሰባሰቡ አቅማቸውን እያጠናከሩ መልሰው ለመገንባት ሲደክሙ ከገንዘብ እስከ አሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ የሌላ እምነት ተከታዮች አሁንም በየቦታው መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ በዘመናችንም ክርስቲያኖች በጥብዐት መከራውን ተቋቁመው ክርስትና በሞት፣ በስድት፣ በእሳትና በመከራ የማይፈታ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ በዚሁ አንጻር ግን በመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ቦታዎች የሚቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት ያልታወቁ ግለሰቦች ያቃጠሏቸው እንደሆነ ቢነገርም ታስቦበት፣ ተጠንቶ፣ ምን ለማግኘትና ምን መልስ ለመስጠት አስቀድሞ እየታሰበ ቃጠሎው መፈጸሙን የሚጠቁሙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ፲፱፻፺፫ዓ.ም ሚያዝያ ፲፪ ቀን በአርሲ ሀገረ ስብከት ኮፈሌ ወረዳ ጉች ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የሚገኘው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በአክራሪ እስላሞች ለመቃጠል የቻለው ከተማ ላይ ሊያደርሱት የነበረው አደጋ በመከላከያ ሠሪዊትና በፖሊስ ስለተደናቀፈባቸው ነው፡፡ ገጠር በመግባት የክርስቲያኖችን ቤት እየመረጡ ማቃጠላቸው የታቀደና የተደራጀ ጥቃት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ ከትላንት እስከ ዛሬ መቀጠሉ ታስቦበት እየተሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በአንድ በኩል አጥፊዎች ልብ እንዲገዙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከትላንት እስከ ዛሬ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በመረዳት ለእምነት ቤቶችና ለክርስቲያኖች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ሊያነቁ፣ ምእመናንም ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ እንዲደራጁና አዲስ ነገር ሲገጥማቸው ለፍትሕ አካላት እንዲያቀርቡ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች የሚማሩት ከመከራ፣ ቅድስናቸው የሚገለጠው በፈተና መሆኑ የተጻፈ፣ ክርስቲያኖች በተግባር ፈጽመው ያሳዩት ሕይወት ነው፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት ከመስከረም ፲፮ እስከ ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም ጨጉ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቦሬ ቅዱስ ገብርኤልና በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ እስላሞች ተቃጥለዋል፡፡ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጅማ፣ በምዕራብ በወለጋና በኢሉባቡር ከ፲፫ በላይ አብያተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፰ዓ.ም በአርሲ ሀገረ ስብከት በኮፈሌ ወረዳ የምትገኘው የአይሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፀረ ክርስትና አቋም ባለው ቡድን ተቃጥላለች፡፡ አገልጋይ ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ታርደዋል፣ አሥር ክርስቲያኖች በገጀራ ተገድለው፣ አብያተ ክርስቲያናትና የክርስቲያኖች መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሟል፤ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ሰላም እንዳይሰፍን ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡

በወቅቱ አጥፊዎችን ሊያስተምር የሚችል እርምጃ መወሰድ ሲገባ ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ከመንግሥት አካላት ተጽዕኖ ይደረግ ነበር፡፡ አጥፊዎችን ማስታገስ ሲገባ ጉዳት የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ጉዳታቸውን እንዳይናገሩ መከልከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሲፈጸም መፈጸም በሕግም በሞራልም የሚያስወቅስ ነው፡፡ ይህ በምንም ዓይነት መንገድ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ለአጥፊዎች ከለላ መስጠትን እንጂ ለፍትሕ መቆምን አያሳይም፡፡ አጥፊዎች ሲያጠፋና ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ዝም ብሎ ማየት ትዕግሥትን ሳይሆን የጥፋት ተባባሪ መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡

በወቅቱ የመንግሥት አካላትን ያሳስብ የነበረው የገደሉትንና አደጋ ያደረሱትን አካላት ለመያዝ ሳይሆን አደጋው በተፈጸመበት ወቅት ከቦታው ተገኝተው የዘገቡትን አካላት ለመያዝ ነበር፡፡ ይህ ተግባር አሁንም ስለቀጠለ ቤተ ክስስቲያን እየተገፋች ድምፅ የሚያሰማላት አካል እያጣች ነው፡፡ አጥፊዎች ለስንት ሺህ ዘመናት የኖረ የሀገር ሀብት ሲያወድሙ እንደ ቀልድ እየታለፈ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በየካቲት ወር መጨረሻና በመጋቢት ወር መጀመሪያ በድሬደዋ ከተማ አጠገብ የሚገኘውን ደን በመመንጠር የቤተ ክርስቲያንን መሬት በመከፋፈል ላይ ሳሉ ሕግ አስከባሪ አካላት ቢደርሱም አልታዘዝንም በማለት ቆመው ሲመለከቱ አጥፊዎች ከቦታው እንዲሸሹ ሲያደርጉ እንደነበር የዐይን እማኞች ገልጠዋል፡፡ በሊሙ ኮሳ ወረዳ በያዝነው ዓመት በተፈጸመው ጥፋት ከወረዳ አመራር ጀምሮ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ወገኖች ጥፋቱን ያደረሱት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ወደ ሕግ ለማቅረብ አለመቻላቸውን ወረዳ ቤተ ክህነቱ ለሀገረ ስብከቱ የጻፈው የድረሱልኝ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ ምክንያት ተፈልጐ የሚያዙትና ካለ ፍርድ እስር ቤት እንዲቆዩ የሚደረጉትም ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች እንዲሞቱ የተፈረደባቸው፣ ለሚደረስባቸው  አደጋ ሁሉ ከለላ የሌላቸው መሆኑን ሲያመለክት አጥፊዎች ደግሞ ሽፋን የሚሰጣቸው ይመስላል፡፡ ይህንም በሐረር ከተማ ጥር ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ለጥምቀት በዓል በወጡ ምእመናን ላይ ለጁምአ ስግደት በአንድ መስጊድ ተሰብስበው የነበሩ ሙስሊሞች በፈጸሙት ትንኮሳ ግጭት ተፈጥሮ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በፖሊስ ቊጥጥር ሥር የዋሉት ፲፮ ምእመናን ያለ ምንም ውሳኔ ከስድስት ወራት በላይ መቆየታቸው ማሳያ ነው፡፡ ግጭቱን ማን እንደጀመረው? ዓላማው ምን እንደነበር? አጣርቶ አስቸኳይ ውሳኔ መስጠት፣ አጥፊም በጥፋቱ እንዳይቀጥል ማስተማር ሲገባ ክርስቲያኖችን መርጦ ማሰር መፍትሔ አይሆንም፡፡ ወንጀል የፈጸመ ሰው አይያዝ ባይባልም ክርስቲያኖች ብቻ ተይዘው የሚታሰሩበት፣ ቢታሰሩም ቶሎ ለፍርድ የማይቀርቡበት ምክንያት ሌላ ዓላማ ያለ ያስመስላል፡፡

በአጥፊዎች ላይ ውሳኔ ቢሰጥበትም ቤተ ክርስቲያንን ላቃጠሉ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለዘረፉ አካላት የሚሰጠው ፍርድ አንድ በግ ከሰረቀ ሌባ ጋር ልዩነት የሌለው በነፃ ከማሰናበት ያልተሻለ መሆኑ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ትኩረት መነፈጉን የሚያሳይ ነው፡፡ መረዳት የሚገባው ቤተ ክርስቲያንን አቃጥለው፣ ቅርሱን አውድመው እስከሚጨርሱ ዝም ከተባለ “ኢትዮጵያን የጎብኝዎች መዳረሻ እናደርጋለን” የሚለው አሳብ የሕልም እንጀራ መሆኑን ነው፡፡ የሚነገረው ቃልም ተፈጻሚነት ሳይኖረው ክርስቲያኖችን በማይሆን ነገር ለማዘናጋት የሚፈጸም መሆኑን የሚያሰገነዝብ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሡት አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ብቻቸውን ሳይሆኑ በጀርባቸው ሌላ አይዞህ ባይ እንዳላቸው የሚያመለክት ነው፡፡ የክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ትኩረት እንዳይሰጠው፣ በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዳያገኝና ሽፋን የሚያገኘውም ዘግይቶ መሆኑ ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰጠው አስተያየት እውነት የሚመስለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጽሙት እንዲሸፈን መደረጉ ነው፡፡

 በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሜኤሶን ወረዳ በሚገኘው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳም የካቲት ፳ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ለከብት ዘረፋ ወደ ገዳሙ ክልል የገቡ የኢሳ ጎሳ አባላትን ለመከላከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ሰደድ እሳት ተቀሰቀሰ፡፡ በወቀቱ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከ፳፻፩ ዓ.ም በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ ለ፲፭ ቀናት የቆየው ሰደድ እሳት ከ፲፩ ሺህ ሄክታር በላይ ደን አውድሟል፡፡ እሳቱ በቊጥጥር ሥር የዋለው ከዋናው የገዳሙ ግቢ ለመድረስ ፭፻ ሜትር ያህል ሲቀረው ነበር፡፡ በወቅቱ ከ፴፰ ያላነሱ ከሰል አክሳዮች ለሰደድ እሳቱ መነሣት ምክንያት ናቸው በሚል ተጠርጥረው በቊጥጥር ሥር ቢውሉም ወዲያው በዋስ ተለቀዋል፡፡ ክስ ይመሥረትባቸው አይመሥረትባቸውም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ማስተካከያ የሚሰጥ አለመኖሩን ያሳያል፡፡

ይቆየን!

ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም