በዘመናችን የቤተክርስቲያን ፈተናዎች

የተከበራችሁ አንባብያን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸመውን ግፍ የሚገልጽ ተከታታይ ጹሑፍ በማቅረብ ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ነጠቃ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና የምእመናን ግድያ  ዋናዎቹ የግፍ ተግባራት ናቸው፤ ከባለፈው የቀጠለውንና የመጨረሻውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ መልካም ንባብ

በማርክሲዝም ሌሊዝንም አስተምሮ የተበረዘ ሰው ሁል ጊዜ ባላንጣና ጠላት በመፈለግ ጠላቱን ካላጠፋ መኖር እንደማችል ሲሰብክ የሚኖር መሆኑን በሙያው ምርምር ያደረጉ አካላት ይናገራሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሃይማኖትም እየተጋባ መጥቷል፡፡ ከሃይማኖት ሰዎች የሚጠበቀው እናመልከዋለን የሚሉትን አምላክ በቃልም በምግባርም መግለጥ ነው፡፡ ሌላውን እያጠፉና  አማራጭ እያሳጡ እምነትን ማስፋፋት አይቻልም፡፡ ሌላውን አጥፍተው መኖር የሚፈልጉት የሚያደርጉት ምድራውያን ገዥዎች ናቸው፡፡ ስለሃይማኖት የሚያስተምሩ አካላት ከዚህ ዓለም የተለየ ዘለዓለማዊ ርስት እንዳለ የሚያምኑ በመሆናቸው ዘለዓለማዊ ርስት ማውረስ የሚችለውን አምላክ የሚያስደስቱበትን ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ሰው በመግደልና ተቀናቃኝን በማጥፋት ተደስቶ የሚኖር የሚመሰለው ምድራዊ የሥጋ ፍላጎት ያለው ምድራዊ ገዥ እንጂ ዘለዓለማዊ መንግሥትን የሚሻ መንፈሳዊ ሰው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወደ አሕዛብ የምትገባው ወንጌልን ይዛ እንጂ እንደ ቀኝ ገዥዎች በአንድ እጅ ወንጌል በሌላ የጦር መሣሪያ ይዛ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን የምታደርገው ባለቤቱ በወንጌል እንዲያምኑ ያደረገው በፍቅር እንጅ በግዳጅ ባለመሆኑ ነው፡፡እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር የቤተ ክርስቲያን አለመሆኑን መረዳት የሚገባውም ቤተ ክርስቲያን በሞት እንጂ በመግደል ጸንታ ስለማታውቅ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የገጠማት ፈተና ያላሳሰባቸው አካላት የሰጡት መግለጫ መንግሥትን በሚከተለው መንገድ  አሳስቧል፡፡ ሀገርና ሕዝብን ለመምራት የተቀመጠው መንግሥት  በየአካባቢው  እየደረሰ ባለው  የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ፣ የኦርቶዶክሳውያንን መፈናቀል ፣ድብደባ ከዚያም ሲያልፍ አሰቃቂ ግድያ ላይ ያሳየው ቸልተኝነት የበርካታ ሚሊዮን አባሎቻችንን ልብ በእጅጉ የሰበረ ወደፊትም ቢሆን ለደኅንነታችን መጠበቅ ምንም አይነት ዋስትና እንደሌለን እንዲሰማን ያደረገ በመሆኑ የመንግሥትን ለዘብተኝነት በእጅጉ  እንቃወማለን ›› ይላል፡፡ አንድ መንግሥት ለዜጎቹ ዋስትና  ሲሰጥ ዜጎቹን በመንግስት እምነት  ማሳደር ብቻ  ሳይሆን  ለመንግሥትም  ጠበቃ ይሆናሉ፡፡ ምርጫ ቢደረግ ይመርጡታል፤ ቢናገር ይሰሙታል፡፡ ቢያዝዝ ይፈጽሙለታል፤ እንኳንም ተናግሮ ሳይናገርም ማድረግ የሚገባቸውን ይሠራሉ ፡፡ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ በጌታ ለገዥዎቻችሁ ታዘዙ ›› የሚለውን  አምላዊ ቃል ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ወደ ፊትም ይፈጽሙታል፤ ይህ ማለት ግን በክርስቲያኖች ላይ በደል ሲፈጽም መንግሥትን አያሳስቡም ማለት አይደለም፡፡ ለገዥዎቻችን መታዘዝ እንዳለብን የሐዋርያውን ቃል አምነን እንሠራለን፡፡ አድሎአዊ ተግባር  ሲፈጸም ስናይ ደግሞ እንናገራለን፡፡ ነህምያ የኢየሩሳሌም መፍረስ ሲያሳስበው ስለኖረ ኃዘንና ትከዜው በፊቱ ላይ መነበብ በጀመረ ጊዜ የማረከው ንጉሥ ምን እንዳሳዘነው ጠየቀው ፡፡ ነህምያም ከዚህ በላይ መከራ አለመኖሩን በመረዳት አባቶቼ የሠሯት ኢየሩሳሌም ፈርሳ እንዴት ደስተኛ እሆናለሁ በማለት መለሰለት፡፡ በነህምያ መልስ ቅንነቱን ሲመለከት የኖረው ንጉሥ የሚያመልከው አምላክ የሚመለክበትን ቤተ መቅደስና ሙሉ ከተማዋን እንዲያንዱ ፈቃድ ሰጥቶ ሰደደው፡፡ በእኛ ዘመንም መፈጸም ያለበት እንዲህ ነው፡፡ አንተ ከፈርኦን አታንስ እኛም ከሙሴ አንበልጥ የሚለውን ንግግር ማሰብ ይገባል፡፡

 ሀገራችን ክርስቲያኖችን እያጠፉ የሚደሰቱበት ክርስቲያኖች ደግሞ በኃዘን የሚኖሩባት መሆን የለባትም፡፡ ሁላችንም እኩል ደስታውንም ኃዘኑንም የምንካፍልባት መሆን ይኖርባታል፡፡በሃይማኖት ሰበብ የተቀሰቀሰ ግጭት ቶሎ ስለማይበርድ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ሠለስቱ ምእት የመቶ ሃያ ማኅበራት ኅብረት ደግሞ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጅማ፣ በኢሉባቡር፣በከሚሴ፣በድሬድዋ፣በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣በፍቼ፣ሶማሌ (ጅጅጋ) ፣በባሌ፣ በአሩሲና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፤ ክርስቲያኖች እየተገደሉ፤ እየተሰደዱና ተገደው ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ፤  ንብረታቸው እየተቀማና እየተቃጠለ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች ጥምቀተ ባሕርን ጨምሮ እየተቀሙ እንደሆነ በተለያዩ ሚድያዎች የሰማነውና በአካልም በቦታው ተገኝተን ያየነው እውነታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር ባለውለታ መሆኗ ተረስቶ ቤተክርስቲያንና አማኞቿን የማይመጥን ስም እየተሰጣት እንዲህ ያሉ ጥቃቶች መንግሥት ባለበት ሀገር እየተፈጸሙ፤ ሰዎች በነፃነት የፈለጉትን የማምለክና በሰላም ወጥቶ የመግባት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተነፍገው በስጋትና በመከራ ውስጥ በመሆናቸው የተሰማንን ጥልቅ ኃዘን እንገልጣለን›› ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ የምትታወቅባቸው የመስህብ ቦታዎች የቤተክርስቲያኗ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ቤተክርስቲያንን አጥፍተን ሌላ እንመሥርት ካልተባለ በስተቀር እንዲህ አይነት ተግባር በየትም ተደርጎ አያውቅም፡፡እንዲህ አይነት ዘመኑን የማይመጥን  ጥፋትና አድሎአዊ አሠራር መቆም ይኖርበታል፡፡ሥልጣን ላይ ስንቀመጥ መልካም ብንሠራ እኛ ዘለዓለማዊ አይደለንምና ስንወርድ ደግሞ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንኖራለን፡፡ ሰዎች በመውረዳችን ያዝናሉ መልካም ተግባራችንን ሲዘክሩ ይኖራሉ እንጂ እንኳን ወረዱ አይሉንም፡፡ስለዚህ አጥፊዎች ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ አጥፊዎች እንወክለዋለን የሚሉትንም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኖችን፤ አባቶችን አቅርቦ ማወያየትና ችግሩን በመለየት የማያዳግም እርምት መስጠት ይገባል፡፡

      ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፯