በዓለ ጰራቅሊጦስ
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ግንቦት ፳፭፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ጰራቅሊጦስ ማለት ናዛዚ፣ ከሣቲ፣ መንጽሒ፣ መጽንዒ፣ መስተስርዪ፤ መስተፍሥሒ ማለት ነው። መንጽሒ ማለት ከኃጢአት የሚያነጻ፣ የሚቀድስ፣ የቅድስና ነቅዕ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በሰውነታችን የሚያሳድር ነው። መጽንዒ ማለት የሚያጸና፣ ኃይል፣ ብርታት፣ ጥብዓት የሚሆን፣ ቅዱሳንን ከሀገር ምድረ በዳ ከዘመዳ ባዳ አሰኝቶ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ደንጋይ ተንተርሰው፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸብአ አጋንንቱን ታግሠው፣ ጸንተው እንዲኖሩ የሚያደርግ ማለት ነው። መሥተፍሥሒ ማለት ሙሐዘ ፍሥሓ የደስታ መፍሰሻ፣ ሰዎችን ደስ የሚያሰኝ፣ በመከራ በኀዘን ውስጥ ደስታን የሚሰጥ ነው። “ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” እንዲል፤ (የሐዋ.፭፥፵)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሳ በ፶ኛው ቀን በዐረገ በ፲ኛው ቀን ከሣቴ ምሥጢር ልሳነ ዓለም መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት እንደላከላቸው ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ መዝቦት እናገኘዋለን። “በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን። ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው፦ እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፦ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና።” (ሐዋ.፪፥፩-፲፫)
ከዚህ ቀል በመነሣት ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት፣ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን እንዴት ተቀበሉት እኛስ እንዴት እንቀበለው፣ ግብረ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የሚለውን ጉዳይ እንመለከታለን።
መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ከአብ የሠረፀ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል፣ ጥንት ፍጻሜ በሌላቸው በአብ በወልድ ህልው ሆኖ የሚኖረው፣ ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ ያለው በአንዲት ፈቃድ፣ በአንዲት ሥልጣን በአንዲት መንግሥት ከአብና ከወልድ ጋር ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ የሕይወት መገኛ ሕይወት ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ስለ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለ፤ “አብ ወልድ ባሉበት ቦታ በዚያ መንፈስ ቅዱስን እናየዋለን፤ በአብ በወልድ ያለ የአምላክነት ክብር ለመንፈስ ቅዱስም ገንዘቡ ነው፤ ይኸውም ቸርነት፣ ይቅርታ፣ ዕውቀት፣ ቅድስና፣ ሕይወት፣ ንጽሕና ነው።” ነበልባል ከእሳት እንዳይለይ፣ ጸዳልም ከብርሃን እንዳይለይ፣ እንዲሁ ንጽሕና፣ ሕይወት፣ ቸርነት፣ ዕውቀት ከመንፈስ ቅዱስ አይለይም።
መንፈስ ቅዱስ ሕያው እግዚአብሔርን በማሳወቅ ሁሉን ዐዋቂ የሚያደርግ፣ በነቢያት ቃል ትንቢትን ያናገረ፣ በሕግ ጸንተው ላሉ ጥበብን የገለጠ፣ ካህናትን እውነተኞች የሚያደርጋቸው፣ ለነገሥታት ኃይልን የሚሰጥ፣ መከራን ለሚታገሡ ትዕግሥትን የሚሰጥ፣ እውነተኛ ሀብትን ልጅነትን የሚያድል፣ ሙታንን የሚያስነሳ፣ እስረኞችን የሚፈታ፣ ከኃጢአት ከጣዖት የተለዩትን በጥምቀት ከሥላሴ እንዲወለዱ የሚያደርጋቸው፣ ፀሐይ በሥጋውያን ሁሉ ላይ እንዲያበራ ከእርሱም ሁሉ እያንዳንዱ በየአካላቸው ሙቀትን፣ ብርሃንን እንዲቀበሉ፣ ከእርሱ ስለተሰጠ ሙቀት ብርሃንም ምንም ምን እንዳይጎድለው መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ በፍጥረት ሁሉ ላይ ሀብቱን ሲያሳድር የማይጎድለው የማይጨመረው ሕጸጽየሌለበት ናዛዜ ሕዙናን አንዱ እግዚአብሔር ነው።›› (ሃይ.ም.፴፫፥፴፱-፶)
የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሐዋርያት ላይ ሲወርድ በእሳት አምሳል ነው። መንፈስ ቅዱስ በእሳት ለምን ተመሰለ የሚለውን እንመልከት። እሳት ምልእ ነው፤ በሁሉም ቦታ ይገኛል መንፈስ ቅዱስም ምልእ ነው። የማይገኝበት ስፍራ የለም፤ እሳት በምልአት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም፤ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናገር፣ ምሥጢር ሲያስተረጉም፣ ተአምር ሲያሠራ እንጅ አድሮ ሳለ አይታወቅም። እሳት ከመነሻው በመጠን ቢሆንም ገለባውን እንጨቱን እየጨመርን ስናቀጣጥለው ግን ኃይሉ እየጨመረ እየሰፋ እየተስፋፋ እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስም መጀመርያ በ፵ና በ፹ ቀን ከቤተ ክርስቲያን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ስንወለድ በመጠን ይሠጠናል። ኋላ ግን በገድል በትሩፋት የተሰጠን ጸጋ እያደገ ተራራ እስከ ማፍለስ ሙት እስከ ማስነሳት ያደርሳል።
እሳት ጣዕምን መዓዛን ያመጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን ያመጣል። “በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና” እንዲል። (፪ኛቆሮ.፪፥፲፭) እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፤ ከመጠን ካለፈ ግን ያቃጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ “እሳት በላዒ ለዓማፅያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ” እንዳለ አባ ሕርያቆስ፤ (ቅዳሴ ማርያም) እሳት ደረቁን ከእርጥቡ ለይቶ ያቃጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ኃጥኡን ከጻድቁ፣ መናፍቁን ከምእመኑ ለይቶ ያጠፋልና። እሳት ዱር ይገልጣል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢር ይገልጣልና። እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነትም ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና።
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን እንዴት ተቀበሉት፦ ጌታችን ሲያርግ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶአቸው ነበር። “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።” (ሉቃ.፳፬፥፵፱) ሐዋርያት ይህን የተስፋ ቃል ተቀብለው በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት ቤት ተሰብስበው ሳለ መንፈስ ቅዱስ በነፋስ ድምፅ በእሳት አምሳል ወረደላቸው። ቅዱስ ሉቃስ ስብስባቸው እንዲሁ ስብስብ ብቻ ሳይሆን “በአንድ ልብ ሆነው ሳሉ” በማለት በአንድ ልብ በአንድ ሐሳብ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ድንግል ማርያምን ከመካከላቸው ይዘው የአምላካቸውን የተስፋ ቃል ይጠባበቁ ነበር። “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር” እንዲል፡፡ (ሐዋ.፩፥፲፬)
ለሐዋርያት የወረደ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ በዲበ ጸጋ እንዲል ለእርሷም ተሰጥቶአታል። ድንግል ማርያም የድኅነታችን መጀመርያ፣ የክርስትናችን ቁልፍ ናትና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እንዲህ ይላል። “እንሆ ድንግል የቤተ ክርስቲያንን አምባ በሥላሴ ገመድ ዙሪያውን አሠራች፤ አደባባይዋንም ስለ ሥላሴ በተጋደሉ ድል በነሡም በሰማዕታት ደም ቀጠረች፤ በሥቃይ የማያዘነብሉ በምሳርና በመጥረቢያ የማይፈቱ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ምሰሶዎች አድርጋ አቆመች፤ እነርሱም ስለ ክብራቸው የሚያበሩ የጳዝዮን ደንጊያዎች ስለ ደማቸውም መቅላት ደስ የሚያሰኙ የሰንፔር ዐለቶች ስለ ምሥክርነታቸውም የጠሩ የወርቅ ፈርጦች ናቸው። መዝጊያዎቿንም ከቄድሮስ እንጨት አደረገች፤ እነርሱም ነቢያት ናቸው። በነቢያት ትንቢት በሮች ከገባው በቀር የሐዋርያትን ምሰሶነት ያይ ዘንድ መግባት የሚቻለው የለም።” (መጽሐፈ ምሥጢር ፳፱፥፰)
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ ፈሪዎች የነበሩት ጥብዓን ሆኑ፤ ደካሞች የነበሩት ኃይለኞች ሆኑ፤ ከብልየት ታደሱ፤ አንድ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩት ፸፩ ቋንቋ ተጨምሮላቸው ፸፪ ቋንቋ የሚናገሩ ሆኑ። የቤተ ክርስቲያን ልጆች አስተውሉ! ቤተ ክርስቲያን ባለ ብዙ ልሳንና በብዙ ልሳን አንዱ እግዚአብሔርን የምትሰብክ የጸጋ ግምጃ ቤት እንጅ በቋንቋ የምትለያይ አይደለችምና እናስተውል። ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ ዓርብ ጌታችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲሰቅሉት አይሁድን ፈርቶ እንዳልሸሸ ዛሬ ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕዝቡ መካከል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊናገር ቆመ። የከተማው ሰዎች “ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል” ብለው ቢሳለቁባቸውም አሕዛብ ግን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አደነቁ፤ በአንድ ቀንም ሦስት ሽህ ሰዎች አመኑ፤ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ ይህች ቀንም “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ተብላ ተጠራች።
በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት የበሰለ ከብልየት የታደሰ ማንነት እንዲኖረን እኛስ እንዴት ነው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በውስጣችን የሚቀጣጠለው? ቢሉ የመጀመርያው በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ነው። ስለ ምን? ቢሉ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የምንቀበል የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን ነውና። ቅዱስ ዲዮናስዮስ “የጥምቀት አገልግሎት ሥርዓት አንድምታ” በሚለው መጽሐፉ “በጥምቀት ውኃ መካከል በኅቡእ የሚገኝ መለኮታዊ እሳት አለ፤ ይህ እሳት የሰውነታችንን ኃጢአት አቃጥሎ ያጠፋልናል። ብረት ከእሳት ውስጥ ሲገባ ከእሳቱ ጋር በመዋሐድ ምክንያት ዝገቱ ከላዩ እንዲወገድ እንዲሁ መለኮታዊው እሳት የሆነው መንፈስ ቅዱስ በአካላችን ውስጥ ሲያድር የኀጢአት ዝገታችን ፈጽሞ ይወገድልናል።”
በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን እንደ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም በአንድ ልብ መኖር ግድ ይለናል። ኢየሩሳሌም የተባለችም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ዘወትር የማይለያት፣ መንፈሳዊት አደባባይ፣ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ የሚፈተትባት ክቡር ደሙ የሚቀዳባት ቤተ ክርስቲያን ናት። ኃይልን የምንቀበልባት፤ ኃይል የምታሰጠን የነቢያት አገራቸው ኢየረሳሌም ድንግል ማርያም ናት። “አንቲ ውእቱ ኢየሩሳሌም ሀገሮሙ ለነቢያት” እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) እንግዲያውስ ክርስቲያኖች ልዩነታችንን አስወግደን፣ አንዱን ክርስቶስ ለብሰን፣ በድንግል ማርያም ጥላ ሥር ተጠልለን፣ በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እንቀበል!
ቅድስት በምትሆን በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደ የአብ በረከት፣ የወልድም ፍቅር፣ የመንፈስ ቅዱስ ሀብት በሁላችንም ላይ ይውረድ፤ ዕፅፍ ድርብም ይሁን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!