በዓለ ደብረ ምጥማቅ

ግንቦት፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም በግንቦት ሃያ አንድ ቀን ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጐናጸፈች ናት፤ በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር፤ ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥዋ ገናናነት ይሰግዳሉ፤ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል። ‹‹አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ።››

ሁለተኛ ሰማዕታትም በየማዕርጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል፤ እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል።

ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ይህ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል፤ ምስጋናም ያቀርቡላታል። ሁለተኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ።

ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል፤ በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ፤ የተሰበሰቡትም በአዩ ጊዜ ደስታ ይመላባቸዋል፤ በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልንጀራው ‹‹ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳይኝ›› ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደ ላይ ይወረውሩላታል፤ የወደደችውንም በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች፤ ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም፣ እስላሞችም፣ አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሄድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል፤ እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ግንቦት ሃያ አንድ በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓልን ታደርጋለች፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ አሜን!

ከመጽሐፈ ስንክሳር ግንቦት ሃያ አንድ ቀን!