በዓለ ዕርገት

መምህር ሙላት ደምሌ

ግንቦት፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

የበዓለ ዕርገት ታሪካዊ አመጣጥ ከራሱ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ለሐዋርያቱ ለአርባ ቀናት እየተገለጸ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምሯቸዋል። (ግብረ ሐዋርያት ፩፥፫) እነዚህ አርባ ቀናት ሐዋርያት ትንሣኤውን እንዲያረጋግጡና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያውቁ ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ።

በአርባኛው ቀን ጌታችን ሐዋርያቱን እስከ ቢታንያ አወጣቸው፤ ይህም በደብረ ዘይት ተራራ አካባቢ ነው። እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው፤ እየባረካቸውም ሳለ ከእነርሱ ተለየ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። (ሉቃስ ፳፬፥፶-፶፩) ሐዋርያትም እርሱ ሲያርግ በዓይናቸው ተመልክተዋል። ደመናም ከዓይናቸው ሠውራዋለች።

እነርሱም ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ፣ እነሆ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆመው “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከተ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” አሏቸው። (ግብረ ሐዋርያት ፩፥፱-፲፩)

የጌታችን ዕርገት ድንገተኛና ያልተጠበቀ ክስተት አልነበረም። በብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለዚህ ነገር ትንቢት ተናግረው ነበር። ለምሳሌ፡- “እግዚአብሔር በእልልታ ዐረገ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።” (መዝሙረ ዳዊት ፵፮፥፭)

“ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ።” (መዝሙረ ዳዊት ፷፯፥፲፰)

ስለዚህ የበዓሉ ታሪካዊ መሠረት ጌታችን ራሱ ያከናወነው የዕርገቱ ሥራ ነው።

የጌታችን ዕርገት በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊና የአበው ምሥጢራዊ ምንጮች አሉት። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-

የክርስቶስ በምድር የነበረው አገልግሎት ማጠናቀቂያና የክብሩ መገለጫ፦ ዕርገቱ የክርስቶስ የማዳን ሥራ ምድራዊ ክፍል ፍጻሜ ነው። በሥጋ ተገልጦ፣ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ተነሥቶ ካሳየን በኋላ፣ ወደ ቀደመ ክብሩ፣ ወደ አባቱ መመለሱን ያመለክታል። ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ “ጌታችን ያረገው ሥጋ ለባሽ ሆኖ ነው፤ ይህም ሥጋችን በሰማያት ቦታ እንዳለውና እንደሚከብር ያረጋግጥልናል” በማለት እንደሚያስተምረው፣ የሰው ልጅ በበደሉ ያጣውን የልጅነት መብትና ክብር ክርስቶስ በዕርገቱ መልሶለታል።

ክርስቶስን የተዋሐደው ሥጋችን መክበሩ (የተዋሕዶ ምሥጢር ፍጻሜ)

ጌታችን አምላክ ወልደ አምላክ ሲሆን የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ፣ በተዋሕዶ ሥጋ ማረጉ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ክብር ነው። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ “ወልድ በባሕርይው ከአብ ጋር በባሕርይ አንድ ሆኖ ሳለ፤ በተለየ አካሉ ሥጋችንን ተዋሕዶ ወደ ሰማይ አሳረገው፤ ይህም እኛም እርሱን ተከትለን፤ ወደዚያ ክብር እንደምንደርስ የሚያሳይ ነው” በማለት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረትና ክብር ያሳያል።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና የቤተ ክርስቲያን መመሥረት፦

ጌታችን ለሐዋርያቱ “እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ ፲፮፡፯) ስለዚህ ዕርገቱ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ (የበዓለ ጰራቅሊጦስን) የገለጠ ነው። ጌታችን ጰራቅሊጦስ የተባለውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚልክላቸው ነግሯቸው ነበር፡፡ (ዮሐንስ ፲፬፥፳፮)

የቤተ ክርስቲያን ራስ መሆኑ፦

ክርስቶስ ወደ ሰማይ በማረጉ፣ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ የተገለጠበት ነው። (መልእክት ኀበ ሰብአ ኤፌሶን ፩፥፳-፳፫) ቤተ ክርስቲያንም አካሉ ናት፤ እርሱም ዘወትር ቤተ ክርስቲያን ይመራል፤ ይጠብቃል፤ ያጸናል።

የዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል ማረጋገጫ (የዳግም ምጽአት ተስፋና የፍርድ ቀን ማስታወሻ)፦ መላእክት እንዳበሠሩት፣ ጌታችን እንዳረገ እንዲሁ ዳግመኛ በክብር ይመጣል። ዕርገቱ ለዳግም ምጽአቱና ለፍርዱ ማረጋገጫ ነው። (ግብረ ሐዋርያት ፩፥፲፩)

ለእኛ የሰማያዊ ቦታ ዝግጅት፦ ጌታችን “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ … ሄጄም ስፍራ አዘጋጅላችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ ፲፬፥፪-፫) ዕርገቱ ይህንን የተስፋ ቃል የሚያረጋግጥና ለእኛም በሰማያዊው መንግሥት ቦታ እንዳለን ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በዓለ ዕርገት በክርስቲያኖች ሕይወት ያለው ቦታ

የጌታችን ዕርገት በክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ጥልቅ አንድምታ አለው፡-

የሰማያዊ ተስፋ ምንጭ፦ የክርስቶስ ዕርገት የእኛም የወደፊት ዕርገትና በሰማያዊው መንግሥት የመኖር ተስፋችንን ያጸናል። ልባችንንና ሐሳባችንን ወደ ሰማያዊ ነገር እንድናደርግ ያሳስበናል፤ (ልባችንን ወደ ሰማይ የማሳረግ ጥሪ)፦ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ። በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።” (መልእክት ኀበ ሰብአ ቆላስይስ ፫፥፩-፪)

በመንፈሳዊ አገልግሎት እንድንበረታ ያደርጋል፦ ጌታችን ከማረጉ በፊት ታላቅ ተልእኮ ሰጥቷል። (ማቴዎስ ፳፰፥፲፱-፳) ዕርገቱ ይህንን ተልእኮ በኃይልና በሥልጣን እንድንፈጽም ያበረታታናል።

ዕርገቱ የመንፈስ ቅዱስን መምጣት እንደገለጠ ሁሉ፣ እኛም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ታድሰንና በርተን እንድንኖር ያስታውሰናል።

በዓለ ዕርገትን ስናከብር ልናደርጋቸው ስለሚገቡ ክርስቲያናዊ ተግባራት

በዓለ ዕርገትን ስናከብር የሚከተሉትን ክርስቲያናዊ ተግባራት ከአበው አስተምህሮ ጋር በማስተባበር ልናከናውን ይገባል፡-

  • በጸሎት፣ በምስጋናና በቅዳሴ መትጋት፦ ዕርገት የድልና የክብር በዓል ነው። ስለዚህ ጌታችን ላደረገልን የማዳን ሥራ፣ በተለይም ሥጋችንን አክብሮ ወደ ሰማይ ስላሳረገልን ልባዊ ምስጋና ማቅረብ ይገባል። በቤተ ክርስቲያን ተገኝቶ በቅዳሴ ሥርዓት መሳተፍ፣ የዕለቱን ምስጋና፣ ጸሎትና የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት በመካፈል ከጌታችን ጋር ያለንን ኅብረት ማጽናት ይገባል።
  • የቅዱሳት መጻሕፍትንና የአበውን ትርጓሜ ማጥናት፦ የዕርገቱን ምሥጢር በሚገባ ለመረዳት ተገቢ የሆኑትን የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች (ግብረ ሐዋርያት ምዕ. ፩፣ ሉቃስ ምዕ. ፳፬፣ መልእክት ኀበ ሰብአ ኤፌሶን ምዕ. ፩ እና መልእክት ኀበ ዕብራውያን ምዕ. ፩) እንዲሁም የአበውን ድርሳናት ማንበብ መንፈሳዊ ዕውቀታችንን ያሰፋል።
  • ልብን ከምድራዊ ነገር ለይቶ በሰማያዊው ላይ ማድረግ፦ አበው እንዳሳሰቡን፣ የጌታችን ዕርገት አሳባችንን ከዚህ ዓለም ጊዜያዊ ነገር ላይ አንሥተን በሰማያዊውና በዘላለማዊው ነገር ላይ እንድናደርግ ያነሳሳናል።
  • ምጽዋትና የፍቅር ሥራዎች፦ ጌታችን “ለእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” እንዳለው፣ የክርስቶስን ፍቅር በተግባር መግለጽና በረከትን ማካፈል ነው። (ማቴዎስ ፳፭፥፵)

አምላካችን እግዚአብሔር ከበዓሉ በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ አሜን!