በዓለ ትንሣኤ ወዕርገታ ለቅድስት ድንግል ማርያም
ነሐሴ፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም
ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም በ፷፬ ዓመቷ በጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም ያረፈችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤዋም ሆነ ዕርገቷ በክብር የተፈጸመ እንደመሆኑ እኛም ልጆቿ ይህችን የተባረከች ቀን እናከብራለን፡፡
በዕረፍት ቀኗ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት በሄዱ ጊዜ አይሁድ ‹‹እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት›› ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በመሠረቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡ በመሆኑም እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋን ‹‹ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ›› ያሰኘውም ይህ ምሥጢር ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ‹‹ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ›› እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት ‹‹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?›› አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሆዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!