በዓለ ቅድስት ሥላሴ
እንኳን ለቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ!
ቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
ሐምሌ፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? አሜን! የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን! የሐምሌ ሰባት በዓለ ቅድስት ሥላሴን በተመለከተ አጭር ጽሑፍ አቅርበንላችኋል፤ ተከታተሉን!
በዚህችም ቀን ልዩ የሆኑ ሦስቱ አካላት ቅድስት ሥላሴ በኦሪት መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ወደ አብርሃም ቤት ገቡ ያቀረበላቸውንም ተመገቡ። የይስሐቅንም ልደት አበሠሩት ባረኩት፤ አከበሩትም። (መጽሐፈ ስንክሳር ዘሐምሌ ሰባት)
አብርሃም አባታችን በተመሳቀለ ጎዳና አራት በር ያላት ግንብ ሠርቶ ያለፈውን ያገደመውን የወጣውን የወረደውን ሲቀበል ይኖር ነበር:: ሰይጣን በዚህ ቀንቶበት ግንባሩን ገምሶ፣ ልብሱን፣ ገፎ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን በደም ለውሶ ሄዶ፡፡ ወደ አብርሃም ቤት መሄጃ መንገድ ላይ ተቀምጦ ወደ አብርሃም ቤት እንግዳ ሲመጣ “ወዳጄ ወዴት ትሄዳለህ?” ይለዋል፤ “ወደ አብርሃም ቤት” ይለዋል:: “አይ አብርሃም የቀድሞው አብርሃም መሰለህ? እኔ ያጎርሰኛል፤ ያለብሰኛል ብዬ ብሄድ ይኼው እንደምታየኝ ግንባሬን ገምሶ፣ ደሜን አፍሶ ሰደደኝ፤ እኔን ያገኘ መከራ እንዳያገኝህ ይቅርብህ፤ ባትሄድ ይሻልሃል” እያለ እንግዳ መለሰበት::
ከዚህ በኋላ አብርሃም “ማዕደ እግዚአብሔር ያለ ምስክር እንዴት ይቀርባል?” ብሎ ሦስት ቀን ጾሙን አደረ። ቅድስት ሥላሴ ርኅሩኃን ናቸውና በእንግዳ ልማድ ሄደው ከደጁ ከመምሬ ዛፍ ተቀምጠው አያቸው፤ እርሱም ሊቀበላቸውም እየሮጠ ወጣ፤ በቀረበም ጊዜ ወደ ምድር ሰገደ፤ “አቤቱ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ ብዬ በእውነት እለምንሃለሁ፤ ከቤቴ ገብታችሁ ዕረፉ” አላቸው:: “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ” ብሎ መናገሩ አንድነቱን፣ ጥቂት ውኃ ይምጣላቸሁ እግራችሁን ታጠቡ ብሎ መናገሩ ሦስትነታቸውን ለመግለጽ ነው:: ይህ ምሳሌ ነው፤ ዛፏ የእመቤታችን ምሳሌ ናት፤ ሥላሴ በዛፏ ሥር ተቀምጠው እንደ ታዩ አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ ለተዋሕዶ በእመቤታችን የማደራቸው ምሳሌ ነው:: ይህቺ ዛፍ በአብርሃም ደጃፍ ተተክላ፣ ቅርንጫፎቿን አንሰራፍታ ቅድስት ሥላሴን ለመቀበል እንደበቃች፣ እመቤታችንም ከአብርሃም ዘር ተወልዳ፣ ጸጋዋ ተንሰራፍቶ፣ ክብሯ፣ ልዕልናዋ ሰፍቶ የሥላሴ ማደሪያ ለመሆን በቅታለችና፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “አንቲ ውእቱ ዕፀ ድርስ ዘለአብርሃም በርስአኒሁ ዘብኪ አጽለለ እግዚአብሔር በሥላሴሁ፤ለአብርሃም በእርጅናው ወቅት እግዚአብሔርን በሦስትነት ያስጠለለብሽ የወይራ ዛፍ አንቺ ነሽ” በማለት ገልጾታል:: (እንዚራ ስብሐት)
ቅድስት ሥላሴም “አዝለህ አግባን” አሉት ጽንዐ ፍቅሩን ለማጠየቅ ነው፡፡ አብርሃምም አንዱን አዝሎ ሲገባ ሁለቱን ገብተው አግኝቷቸዋል! አብርሃም ሣራን “ሦስት መስፈሪያ ዱቄት አምጥተሸ በአንድ አድርገሽ ጋግሪ” አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፤ “ወአቅረበ ሎሙ መዓረ ወዕቋነ ወእጓለ ላህም ስቡሓ፤ ድፎ ዳቦ አቅርቦላቸዋል፤ ላህም ሠውቶላቸዋል” ባርከው አስነሥተውለታል! ሕያዋን እንደሆኑ ለማጠየቅ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ልጅ እንደሚወልድ ነግረውት ሲሄዱ ከሦስቱ አንዱ “የዛሬ ዓመት በእውነት ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅ ትወልዳለች” ብሎ ተስፋውን ነግሮት ሄደዋል:: (ዘፍ.፲፰፥፲)
ቅድስት ሥላሴ በእንግዳ አምሳል የገቡት በቤተ አብርሃም መስተናገዳቸውን ቅዱስ ያሬድ ሲናገር “አብርሃም ርእየ ሠለስተ እደወ በዛቲ ዕለት ምሥጢረ ሥላሴ ዜነወ እትነሣእ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ውእቱ ኀይልየ አምላኪየ ረዳእየ ወመድኀንየ፤ አብርሃም ሦስት አረጋውያንን ተመለከተ፤ በዚያች ዕለት የሥላሴን ምሥጢር ተናገረ፤ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስ ኀይሌ፣ አምላኬና መድኀኒቴ ነው ብዬ እነሣለሁ” በማለት የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ተገልጦለት እንደተናገረ ሊቁ በዜማው መስክሯል:: (ድጓ ዘሥላሴ ኆኅተ ሰብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ ገጽ ፭፻፰፯)
ይስሐቅን ሳይወልድ አብራም ይባል ነበር፣ አበ ውሁዳን ማለት ነው፡፡ ይስሐቅን ከወለደ በኋላ ግን አብርሃም ተብሏል አበ ብዙኃን ማለት ነው፡፡ (ዘፍ.፲፯፥፮ አንድምታ ትርጓሜ)
አባታችን አብርሃም ይስሐቅን ሳይወልድ “አብራም” ይባል ነበር፤ “አበ ውሁዳን” ማለት ነው፡፡ ይስሐቅን ከወለደ በኋላ ግን “አብርሃም” ተብሏል፤ “አበ ብዙኃን” ማለት ነው፡፡ ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ እግዚአብሔር ለአብርሃም ምሥጢር እንደገለጠለት ሲናገር “አብርሃምን መረጠው ወዳጄም አለው፤ የተሰወሩ ምሥጢራትን ሁሉ ገለጠለት፤ አብርሃም እንደ ፀሐይና እንደ ንጋት ኮከብ ብሩህ እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ነገረው” ሲል ዘምሯል፡፡ (ድጓ ዘሥላሴ፣ ኆኅተ ሰብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቀጽ ፪ ገጽ ፭፻፰፯)
ስለዚህ በአብርሃም በኩል ምሥጢሩን ለገለጡለት ለቅድስት ሥላሴ ምስጋና እንደሚገባ ሲናገር “ንግሩ ምሕረቶ ለሥላሴ ወዜንዉ ሠናይቶ ለሥላሴ መሃይምናን ንግሩ ምሕረቶ ለሥላሴ፤ የሥላሴን ምሕረቱን ንገሩ፤ የሥላሴ በጎነቱን መስክሩ! እናንተ ምእመናን የሥላሴ ምሕረቱን ተናገሩ” በማለት ያሳስባል።
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስትነት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው። በዚህ ጊዜ ተገኙ፤ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም፤ መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸው። እንግዲህ ሥላሴ ስንል፦
*ሥላሴ ዋሕድ* በአንድ እግዚአብሔር ከሚገኝ ከሦስቱ አካላት ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ በቀር፥ ቅድመ ዓለም ቢሆን ፣ ድኅረ ዓለማት ቢሆን ፈጽሞ ሌላ መንቲያ ወይም ተመሳሳይ የሌለውና ብቻውን የሚኖር ልዩ ሦስት “ሦስትነት” መሆኑን የሚያረጋግጥ አብነት ነው።
ሃሌ ሉያ ለአብ ፥ሃሌ ሉያ ለወልድ፥ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ሥላሴ ዋሕድ።
*ሥላሴ ዘለዓለም (ዘለዓለም ሥላሴ)* ይህ ሲባል የሥላሴ መጠሪያ ስም ከጊዜ በኋላ የተገኘ ሳይሆን ከዘለዓለም በሥላሴነቱ የነበረ ያለ የሚኖር መሆኑን የሚታወቅበት ገለጻ ነው። እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ሀሎ እግዚአብሔር በትሥልስቱ፤ እግዚአብሔር ከዓለም በፊት እስከዘለዓምም ድረስ እግዚአብሔር በሦስትነቱ አለ፡፡ (ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ)
*ሥሉስ ቅዱስና ልዩ ሦስትነት* ይህ ሦስትነት አንድነት ያለው በመሆኑ ሥሉስ ቅዱስ ይሰኛል ማለት ሦስት አካላትን የያዘ ቅዱስ የተለየ ባሕርይ ያለው እግዚአብሔር ወይም መለኮት ማለት ነው።
*ልዩ ሦስትነት* የእግዚአብሔር ልዩ ሦስት ሲባል በሦስትነት በአንድነት የሚገኙ ልዩ ምሳሌዎች አሉና ከዚያ ለይቶ ለማስገንዘብ ነው። ከእነዚህም አንዱ የአካል ሦስትነት ቢኖራቸውም የባሕርይና የህልውና አንድነት የላቸውም። ለምሳሌ “አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ” ብለን የምንጠራቸው ሦስት ስሞች ናቸው።
እንደዚሁም ደግሞ በአንድ የአካል ስም ሲጠሩ በኩነታት ሦስትነት ያላቸው አሉ። እነርሱም ፀሐይ፣ እሳት፣ ቀላይ፣ ባሕር፣ ተክልና ንፋስ ናቸው። የሰው ነፍስ ብትሆንም እንኳን የኩነት፣ የግብር ሦስትነት አላት እንጂ የአካል ሦስትነት የህልውና አንድነት የላትም።
ሥላሴ ግን የአካል፣ የግብር፣ የኩነት ሦስትነት፥የመለኮት የባሕርይ የህልውና አንድነት አላቸው። ልዩ ሦስት “ቅድስት ሥላሴ” ይባላሉ።
ዳግመኛም ሥላሴ፡-
ወላድያነ ዓለም “ቅዱስ” ሥላሴ ማለት ትተን “ቅድስት” ሥላሴ ብለን በሴት አንቀጽ እንጠራቸዋለን፤ የምንጠራበት ምክንያት ምንድን ነው? ስንል ስለ ብዙ ምሥጢር ነው፤ እንደ ሊቃውንቱ ትንታኔ ሴት ርኀርኅተ ልብ ናት፤ ሥላሴም ለፍጥረታቸው ርኅሩኃን ናቸውና፡፡ አንድም ሴት ከባሕርይዋ ልጅ ትወልዳለች! ሥላሴም ወላድያነ ዓለም ናቸው፤ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ካለመታየት ወደ መታየት አምጥተው የፈጠሩ ፈጥረውም የሚያስተዳድሩ ቅድስት ሥላሴ ናቸውና:: አንድም ጽኑዕ፤ ንጹሕ፣ ክቡር፣ ልዩ ሲል ነው፡፡ ሰውን ጽኑዕ ቢሉት እስከ ጊዜው ነው፤ እንጂ ኋላ በሕማም በሞት ይለወጣል:: ቅድስት ሥላሴ ግን መቼም መች ሕልፈት ውላጤ ድካም ሕማም የለባቸውም፡፡
አምልኮት መሠረት
ቅድስት ሥላሴ የአምልኮታችን መሠረት ነው፤ ይህ ማለት ምስጋናም ሆነ አምልኮት የሚጀመረው በቅድስት ሥላሴ ነው፤ የማንኛውም አገልግሎት መክፈቻም ሆነ መዝጊያ የቅድስት የሥላሴ ስም ነው! ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ብላ ጀምራ “ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ብላ ትዘጋለች::
ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ሲናገር “ሃሌ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ አአትብ ወእትነሣእ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሠለስተ አስማተ ነሚእየ እትመረጐዝ እመኒ ወደቁ እትነሣእ ወእመኒ ሖርኩ ውስተ ጽልመት እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ በእግዚአብሔር ተወከልኩ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለም አሳልፎ የሚኖር በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተነሥቼ አማትባለሁ፤ እነዚህን ሦስት ስሞች ይዤ እመረኮዛለሁ፤ ብወድቅ እነሣለሁ፤ ወደ ጨለማ ብሔድ እግዚአብሔር ያበራልኛል፤ በእግዚአብሔር ታመንኩ” ሲል የሃይማኖታችን መነሻና መድረሻ ቅድስት ሥላሴ መሆኑን መስክሯል:: (ድጓ ዘሥላሴ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ ገጽ ፭፻፹፰)
ዳግመኛም ቅድስት ሥላሴ የአምልኮታችን መሠረት የእምነታችን ምንጭ እንድሆነ ሊቁ ግልጥ አድርጎ ሲነግረን “ነአምን ወናመልክ በአሐዱ እግዚአብሔር ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ ወነአምን በካልዑ እግዚአብሔር ዘበምልክናሁ ለአብ ይመስሎ ወነአምን በሣልሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዘይመልዕ፤ ቅድመ ዓለም በነበረ በአንዱ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን እናመልካለን፤ አብን በጌትነት በሚመስለው በሚተካከለው በእግዚአብሔር ወልድ እናምናለን እናመልካለን፣ በዓለም ምሉዕ በሆነው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናምናለን እናመልካለን” ሲል ቅድስት ሥላሴ የአምልኮታችን ማዕከል መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ (ድጓ ዘሥላሴ)
የሚሠዋው መሥዋዕት፤ የሚጸለየው ጸሎት፣ የሚታጠነው ዕጣን የሚቀርበው ቁርባን ሁሉ የሚያርገው ወደ ቅድስት ሥላሴ ነው:: ሊቁ እንዲህ እንዳለ “አንትሙሰ ከመ ዕብነ ሕይወት ተሐነጹ ቤቶ ለመንፈስ ቅዱስ ወለክህነቱ ቅዱስ ከመ ታዕርጉ መሥዋዕተ ወትንግሩ ሠናይቶ፤ ለቅዱስ አገልግሎት ሕያው መሥዋዕትን ታሣርጉ ዘንድ በጎነቱን ትነግሩ ዘንድ፣ እናንተ እንደ ሕይወት ድንጋይ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆናችሁ ታነጹ” በማለት ዘምሯል፡፡ (ድጓ ዘሥላሴ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ ገጽ ፭፻፹፰)
ሙሴ የያዛቸው ሦስት ስሞች
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ወደ ከነአን ሲጓዝ ለጉዞው መሳካት የእግዚአብሔርን ረድኤት የሚጠይቅበትና ሕዝቡ ሲበድሉ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚማፀንበት ሦስት ስሞች ነበሩ፡፡ እነዚህን የያዛቸው ሦስት ስሞች ደጋግሞ መጥራት የፈጣሪውን ምሕረትና ረድኤት አግኝቷል፤ እነዚሀ ሙሴ የያዛቸው ስሞች ምንድን ናቸው? ሙሴ በአብርሃም፣ በይስሐቅ፣ በያዕቆብ ስም ፈጣሪውን ይማጸን እንደነበር ተናግሯል፡፡ እነዚህ ሦስት ስሞች የሥላሴ ምሳሌ ናቸው፤ እነዚህ ስሞች የቃል ኪዳን ማስታወሻ ናቸው፤ እግዚአብሔር ለጊዜው ምድራዊቷ ርስት ከነአንን እንደሚያወርስ፣ ለፍጻሜው ደግሞ ሰማያዊቷን ርስት ወደ መንግሥተ ሰማያትን እንደሚያወርስ ከሕዝቡ በረድኤት እንደማይለይ ቃል ኪዳን ይገባ የነበረው በእነዚህ ስሞች ነበር፤ ሕዝቡም ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ የገባውን ቃል ኪዳን አስቦ የእግዚአብሔር ልብ እንዲራራላቸው ያደርጉ ነበር።
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ይገልጠዋል “መፍቀሬ ሰብእ ክርስቶስ ፈኑ ሣህለከ ወምሕረተከ ዘአንተ ታርኁ ክረምተ በጸጋከ ወትሴሲ እመዝገብከ ስብሐት ለከ ወዐቢይ ኀይልከ ዘሠራዕከ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ዘሠርዐ ለአብርሃም ወመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ንስእለከ ወናስተበቊዐከ እስመ ኵሉ ዘሥጋ ያንቃዓዱ ኀቤከ፤ ሰው ወዳጅ ክርስቶስ ሆይ ይቅርታህንና ምሕረትህን ላክ፤ አንተ ክረምትን የምትከፍት፣ ከመዝገብህ በጸጋህ ትመግባለህ፤ ምስጋና ለአንተ ይገባል፤ ኀይልህ ታላቅ ነውና፤ ለዕረፍት ሰንበትን የሠራህ፤ ለአብርሃም ለይስሐቅ የማልክ፤ ለያዕቆብ ምስክርነትን ያቆምክ” ሲል ዘምሯል፡፡ እነዚህ ሦስት ስሞች (አብርሃም ይስሐቅና ያዕቆብ) የእግዚአብሐር ሕዝብ የመሆን ምልክት ነበሩ፤ ሥላሴም የሃይማኖት ምልክት ናቸውና፡፡ (ድጓ ዘሥላሴ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ ገጽ ፭፻፹፱)
ቅዱስ ያሬድ ሲናገር “ነሡእየ ማዕተበ ዘወልደ እግዚአብሔር አአትብ በሥላሴ እመኒ ወደቁ አቲብየ እትነሣእ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኀይለ መስቀሉ እትመረጐዝ፤ የወልደ እግዚአብሔርን የኢየሱስ ክርስቶስ ምልክት የኾነውን ቅዱስ መስቀል ይዤ በሥላሴ ስም አማትባለሁ፤ ብወድቅ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አማትቤ እነሣለሁ፤ በመስቀሉም እመረኮዛለሁ” ሲል ዘምሯል:: (ድጓ ዘሥላሴ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፪ ገጽ ፭፻፹፱)
በአጠቃላይ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መርምሮ መረዳት ለማንም ቢሆን አይቻለውም። እርሱ ባወቀ ግን በብዙ አይነት በብሉይ ኪዳንም ይልቁንም በሐዲስ ኪዳን ምሥጢረ ሥላሴን እራሱ ባለቤቱ በጥምቁቱ ገልጦልናል፡፡ ይህንንም በዓል ሰናከብር እግዚአብሔር (ሥላሴ) በአብርሃም ቤት ተገኝተው፣ የአብርሃምን ቤት በርከው ሊመጣ ያለውን የሐዲስ ኪዳን ነገረ ድኅነት በግልጥ ነገሮናል። እኛም በዓሉን ሰናከብር እምነታችን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ በቀናች ሃይማኖት ልንጸና ይገባናል!
እንደ አብርሃም ንጹሕ ልብ ይዘን፣ ከኀጢአት ርቀን እንግዶችን እንድንቀበል አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ በሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
አምስቱ አዕማደ ምሥጢር በምኑን በኀበ ሰብእ
ሃይማኖተ አበው ተስፋ ገብረ ሥላሴ
ምሥጢረ ምሥጢራት በገብረ መድኅን እንየው እና መዝገበ ቃል ገ/ሕይወት