በዓለ ልደቱ ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ጥር ፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ ግብጽ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው ፴ (ሠላሳ) ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ ‹‹ሥልጣኑ ከሰማይ ከፍታ ከፍ የሚል ንጽሕናው ከሚካኤል ከገብርኤል የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነቢይ ኤልያስ የሆነ ልጅ እንቺ ተቀበይ›› አላት፡፡
አቅሌስያም በመጋቢት ፳፱ ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ ፳፱ ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ ‹‹የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን›› አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም ‹‹ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን›› አለ፡፡
ከዚህም በኋላ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ተፀንሰው ታኀሣስ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ተወለዱ፡፡ አባታችን ዓይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ተነሥተው «ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘዓውፃእከኒ እምጽልመት ውስተ ብረሃን» ብለው አመስግነዋል። ቅዱስ አባታችን ለአምላካቸው ሰግዶ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ካመሰገነ በኋላ እናታቸው አላቀፈቻችውም፤ ጡትም አልጠቡም፡፡
መላው ሕይወታቸውንም በምድረ በዳ የኖሩ አባት ናቸው፤ በዝቋላ ተራራ ባለው ባሕር ውስጥ ፻ (መቶ) ዓመት ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያውያን ምሕረትን በመለመን ለብዙዎች ድኅነት የሆኑ ታላቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ የተወለዱት ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ቢሆንም በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ምክንያት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት ጥር ፭ በድምቀት እናከብራለን፡፡
የጻድቁ አባታችን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና ረድኤት አይለየን፤ አሜን!
ምንጭ፡- ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ