“በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን ?” (ሐዋ.፰፥፴)

ኢዮብ ዘገነተ ጽጌ
መስከረም ፳፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በዘመነ ስብከቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ቅዱስ ወንጌል ለጊዜው በእግር በኋላ በግብር የተከተሉት ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበሉ በኋላ ከመምህራቸው (ከጌታችን) የተማሩትን ወንጌል ለዓለም ሁሉ እየሰበኩና እየተረጎሙ ለንስሐና ለልጅነት ጥምቀት በማብቃት የወንጌሉን አደራ በመወጣት ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ሐዋርያቱ ከእነርሱ ሥር የተማሩትን በአገልግሎታቸው የተተኩትን አርድዕትና ሐዋርያነ አበው እንዲሁም ዲያቆናትን እያስተማሩና ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጎሙ ከላይ ካሉ ነገሥታት ታች እስካለው ማኅበረሰብ ድረስ ንጹሕ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር በማስተማሩ ብዙዎችን ወደ ክርስትና አምጥተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል አንዱ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በዲያቆኑ ፊልጶስ አማካኝነት በሠረገላው ላይ ሳለ ክርስትናን የተቀበለው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ባኮስ ነው፡፡ ይህ ባለሥልጣን በጊዜው “የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ በገንዘብም የሠለጠነ” እንደነበረ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ የተገለጸ ሲሆን በቀደምት የታሪክ ጸሐፊያንና መተርጉማንም ባኮስ ከሀገሪቱ ንግሥት ሕንደኬ በታች ሆኖ በገንዘብ እና በሀገሪቱ የውጪ ግንኙነት ሥራ ላይ የተሾመ እንደነበረ ይነገርለታል:: (ሐዋ.፰፥፳፯)

ከሰባቱ ዲያቆናት መካከል አንዱ የነበረው ፊልጶስ በጊዜው በኢየሩሳሌምና በሰማርያ እየተዘዋወረ ወንጌልን በማስተማር ብዙዎችን ያስጠመቀ ሲሆን ከዕለታትም በአንዱ ቀን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነው መንገድ ሂድ“ በማለት ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ እንዲያገኘውና እንዲያስተምረው ተልዕኮን ሰጥቶታል፡፡ ፊልጶስም በስፍራው እንደደረሰ በሠረገላው ላይ የተቀመጠ በሠራዊቶቹም ታጅቦ የሚሄድ መኮንን (ባለሥልጣንን) ይመለከታል፡፡ ይህም “ባኮስ” የምንለው አንዳንዶችም ላካሳ(Lacasa)፣ ኢንዳ (Inda) ፣ ኢንዲካ (Indica) በማለት ስሙን ይገልጹታል፡፡ ፊልጶስም ወደ ሠረገላው በተጠጋ ጊዜ ጃንደረባው “የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።” (ሐዋ.፰፥፳፰)

ጃንደረባው በሐዋርያት ሥራ ላይ ሐዋርያት ዲያቆናትና አርድዕት ለማስተማር ከተገናኟቸው ሰዎች የተለየና በአዎንታዊ መንገድ ለወንጌል ትምህርት በሚመች ተግባር ላይ የነበረ እንዲሁም ለማንበብ ቀርቶ ረጅም ርቀት ተቀምጦ ለመሄድ አዳጋች በሆነ በሠረገላ ላይ ተቀምጦ እያነበበ የታየ ተግባሩም የተደነቀለት ሹም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚያ ዘመን (፴፬ ዓ.ም) እንኳን መጻሕፍትን የማንበብ ባሕላቸው የጠነከረና በሚንቀሳቀሱበትም ስፍራ ጭምር ያለመታከት ያነቡ እንደነበረ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ ላይ ሲናገር “በጉዞ ላይ ሆኖ ያውም በሠረገላ ላይ ተቀምጦ ማንበብ አለማቋረጥ ምን ያህል ትጋት የሚጠይቅ እንደሆነ እንድታስተውሉ እጠይቃችኋለሁ በቤታቸው እንኳን ቁጭ ብለው ማንበብን ለማይፈልጉ ሰዎች ይህ ታሪክ ሊስተዋል ይገባዋል፤ ይልቁንም መጻሕፍትን ማንበብን ጊዜን እንደማጥፋት የሚቆጥሩ ወይንም ለትዳር አጋሮቻቸው ጊዜ መስጠት አለብኝ የሚል ምክንያት የሚያቀርቡ፣ በውትድርና አገልግሎት ላይ ነኝ የሚሉ፣ ልጆቼን እየተንከባከቡ ነው ከንባብ ኑሮዬን ማስቀደም ይኖርብኛል የሚሉ ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን የማንበብ ጠቀሜታ አይታያቸውም” (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሐዋርያት ሥራን በተረጎመበት) በማለት አድንቆ ተናግሯል፡፡

አባ ጄሮም የተባሉ አባትም የጃንደረባውን ነገር ሲያደንቅ “እዚህ ላይ ታሪኩን ትቼ ወደ ራሴ መለስ ልበል፤ የንግሥቲቱን ቤተ መንግሥት ትቶ ከምድር ዳርቻ ከኢትዮጵያ ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ከተጓዘውና ለእግዚአብሔር ሕግና ለአምላካዊ ዕውቀት ካለው ፍቅር የተነሣ በሠረገላው ላይ ሆኖ እንኳን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሚያነበው ከዚህ ጃንደረባ የተሻልኩ ጻድቅም ጽኑዕም አይደለሁም” በማለት የሐዋርያት ሥራን በተረጎመበት ላይ ተናግሯል፡፡

ጃንደረባው በጊዜው ያነበው የነበረው የኢሳይያስን የትንቢት መጽሐፍ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አሁኑ ታትሞ ባልተሠራጨበትና የነቢያቱ መጻሕፍት አንድ ላይ ባልተጠረዙበት በዚያ ዘመን አንድን መጽሐፍ በግለሰብ ደረጃ ማግኘት እጅግ ከባድ ነበር፡፡ መጽሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈበትን ብራና ወይንም ፓፒረስ ቅጂ (Autograph) ማግኘት ጨርሶ የማይታሰብ ቢሆንም የመጻሕፍቱ ቅጂም ከሰው ወደ ሰው የሚሻገረው ሙሉ ሥራቸው መጻሕፍትን ከብራና ወደ ብራና እየጻፉ መገልበጥ በነበረው በቁምራን ዋሻ ይኖሩ እንደነበሩት ጸሐፍት (scribes) ዓይነት ሰዎች አማካኝነት ነበር፡፡ ይህንን የመጻሕፍት ቅጂ የራስ ለማድረግ እጅግ ባለ ጸጋ መሆን ይጠይቅ የነበረ ሲሆን አንድ ሰው የራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አለው ማለት ባለጸግነት ወይም ሌላ የጠነከረ አቅምን የሚፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህ ጃንደረባው መንገድ ሲሄድም ይዞት የሚጓዘው የራሱ የትንቢተ ኢሳይያስ ጥቅል የነበረው መሆኑ ከቤተ መንግሥት ሥልጣኑ ጋር ባለ ሀብታም እንደነበረ የሚያሳይ ነው፡፡ መኮንኑ (ጃንደረባው) መጻሕፍትን ማንበቡ እንዳለ ሆኖ የኢሳይያስን ትንቢት ማንበቡ ደግሞ በኋላ ላይ በፊልጶስ አማካኝነት ለሚቀበለው ክርስትና ትልቅ መቅድምና መደላድል የነበረ ነው፡፡ አባ ጄሮም “የኢሳይያስ መቅድም” በሚለው መጽሐፉ “ኢሳይያስ ነቢይ ከሚባል ወንጌላዊ ቢባል ይሻላል፤ ምክንያቱም መጽሐፉ የሚመጣውን ነገር የሚናገር ሳይሆን የተፈጸመን ታሪክ የሚጽፍ እስኪመስል ድረስ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢራት ሁሉ ስለሚያትት ነው” ብሎ ሲገልጸው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ደግሞ “ከማንኛውም ነቢይ በላይ የወንጌልን ምሥጢር ያወቀው ኢሳይያስ ነበር” ሲል አድንቆ ይናገራል፡፡

ጃንደረባው በማንበብ ላይ እያለ ፊልጶስን መንፈስ ቅዱስ “ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኘው” ስላለው ይነጋገረው ዘንድ ወደርሱ ቀርቦ “በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፤ የፊልጶስ ንግግር ምናልባትም ለአንድ በሠራዊት ለተከበበ መኮንን ዘንድ ቁጣንና ተግሣፅ የሚያስከትል የነበረ ሲሆን ጃንደረባው ግን መጽሐፍ አንባቢነቱ በእርሱ ሰብዕና ውስጥም በጎ ተጽዕኖን እንዳሳደረበት ቀጥሎ በተናገረው ነገር ተገልጧል፤ “በአይቴ አአምር ለእመ አልቦ ዘመሀረኒ ወአስተብቁዖ ለፊልጶስ ከመ ይዕርግ ወይንበር ኅቡረ ምስሌሁ፤ እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል አለው፤ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።” (ሐዋ.፰፥፴፩) ከጃንደረባው ዘንድ ሁለት ጥንካሬዎችን ተመለከትን፤ አንደኛው የነበረውን ትሕትናና የቅንነት መንፈስ ነው፡፡ እንደ ልማዱ ከሆነ በሠራዊት የተከበበ መኮንን ቀርቶ ሐዋርያት ለማስተማር ወደ ሀገራትና መንደሮች ሲገቡ እንኳንስ ወደ ራሳቸው ለማቅረብ ቀርቶ ደብድበው ብዙ ሥቃይ አድርሰው ከዚያም ቀለል ቢል እንኳን በጽኑ ቃል ይቃወሟቸዋል፤ ጃንደረባው ግን ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይሰጠው ፊልጶስ “የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲለው የመናቅ አልያም የመደፈር ስሜት አልፈጠረበትም፤ ከዚያ አልፎ ከሠረገላው ላይ አጠገቡ እንዲቀመጥ በማድረግ ትሕትናውን ገልጧል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሐዋርያት ሥራን በተረጎመበት ድርሳኑ “ጃንደረባው ለውጫዊ ገጽታ ትኩረት የማይሰጥ ሰው እንደሆነ ተመልከቱ፤ “አንተ ማነህ?” ብሎ እንኳን አልጠየቀውም፤ እንከን አልፈለገበትም፤ ሊያስመስልም አልሞከረም፤ እንደ ዐዋቂ ሊታይም አልወደደም፤ ዐለማወቁን ገለጠ እንጂ፤ ስለዚህም ተማረ፤ ቁስሉን ለሐኪም ገልጦ አሳየ፤ ፊልጶስ ስለ ጉዳዩ እንደሚያውቅና ለማስተማር ፈቃደኛ የሆነ ሰው እንደሆነ ተረድቷል” በማለት አድንቋል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የጃንደረባው አስተዋይነት ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለ ትርጓሜ (ያለ ማብራሪያ) እና ያለ ተርጓሚ መምህር እንዲሁ በደረቁ ብቻ አንብበው ሊረዱት እንደማይቻል ማወቁ የሚደነቅ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉ መናፍቃን ከዚህ መኮንን የሚማሩት ይህንን አስተዋይነቱን ነው፡፡ ምናልባትም “እንደገባኝ እረዳዋለሁ” ወይንም “ፈጣሪ ይገልጥልኛል” ብሎ ወደ ንባቡ መመለስ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ምን ያህል ተርጓሚ እንደሚያሻቸው መስክሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “ይህንን መጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደለትም” እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስን ትርጓሜም ተርጓሚም የሚያሻው ነው፡፡ (፪ኛጴጥ.፩፥፳) ለምሳሌ የዕለተ ማግሰኞ ፍጥረታትን ብንመለከት በጥሬው እንዲሁ የሚበሉ፣ ተልጠው የሚበሉ እና በእሳት አብስለን የምንመገባቸው በየዓይነት ሆነው ተፈጥረዋል፤ እነዚህም የመጽሐፍ ቅዱስን አረዳድ የሚያስተምሩን ናቸው፡፡ እንዲሁ ሳይላጡ የሚበሉት እንዲሁ ያለ ትርጓሜና ያለ ማብራሪያ አንብበን የምንረዳቸው ሲሆኑ ተልጠው የሚበሉ ማለት ደግሞ ንባባቸው ከማንበብ ቀጥሎ ውስጣዊ ምሥጢራቸውን በትርጓሜ በሊቃውንት ማብራሪያ ልንረዳቸው የሚመደቡ ናቸው። ሌሎቹም በእሳት አብስለን የምንመገባቸው ደግሞ በእኛም ንባብ በመጻሕፍትና በሊቃውንትም ትርጓሜ ተብራርተው መረዳት ያልቻልናቸውን “እሳት” በተባለ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸልየን /በእግዚአብሔር ገላጭነት/ የምንረዳቸው ናቸው፡፡ ታዲያ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብና ለመረዳት ምን ማድረግ ይኖርብናል።

፩. በትሕትና ማንበብ

ጌታችንን ይከተሉት የነበሩት አምስት ገበያ (፶፻) ሰዎች ሁሉም ተመሳሳይ የመዳን ዓላማ እንዳልነበራቸው ሁሉ፥ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎችም ልክ እንደዚህ ናቸው፡፡ መረጃ ለማግኘት ብቻ የሚያነብ አለ፤ ስሕተት ለመፈለግ የሚያነብ አለ፤ ሥነ ጽሑፋዊ ዘይቤው ደስ ብሎት ብቻ የሚያነብ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ዓላማ አንጻር ሲታይ ምንም አይጠቅምም፡፡ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ለመዳን (በድኅነት ጉዞ ውስጥ ባለው ድርሻ) ማንበብ አለባቸው፡፡ ይህም በትሕትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግ (ዐላዋቂ በማድረግ) መሆን አለበት፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንዳለ፡- “ወደዚህ ወደ ትሑት መንፈሱም ወደ ተሰበረ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ” (ኢሳ.፷፮፥፪)፡፡

፪. ጽሙና

ቅዱስ መጽሐፍ በመጀመሪያ ማስተማር ያለበት አንባቢውን ነው፡፡ ስለሆነም ሰው “የማስተምረው” ብሎ ሳይሆን “የምማረው” እያለ በተረጋጋ መንፈስ ማንበብ ይገባዋል፡፡ ይህ መረጋጋት ሕግጋቱን (መጻሕፍቱን) በዓይነ ሥጋ ከማንበብ ባሻገር በዓይነ ልቡናው ዘወትር እንዲመለከታቸው ይረዳዋል፡፡ ነቢዩ “ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ፤ ሕጉን በቀንም በሌሊትም የሚመለከት ሰው ንዑድ ክቡር ነው፡፡ በፈሳሽ ውኃ እንደተተከለችና ፍሬዋን በየጊዜው ለባለቤትዋ እንደምትሰጥ ዕፅ ይሆናልና” እንዲል (መዝ.፩፥፮)፡፡ ይህም ማለት በቀን ያነበበውን በሌሊት፥ በሌሊት ያነበበውን ሕግ በቀን የሚፈጽመው በጽሙና በማንበቡ ነው፡፡ በየሰዓቱ ባነበበው ሕግ ጸንቶ መገኘቱ ከዕለቱ ሙሉ ጊዜ እንዳነበበ እንዳስቆጠረለት እናስተውል፡፡

፫. ያልተረዳነውን ለጊዜው ማለፍ

ሰው ቅዱስ መጽሐፍን ሲያነብ ሁሉንም አነጋገሮችና ምሳሌዎች ይረዳል ማለት አይቻልም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም ሆነ አንባቢው ሰው የአንዱ መነበብ የሌላው ማንበብ በፈቃደ እግዚአብሔር በጸጋ እግዚአብሔር ነውና ሰው ያልተረዳውን ለእግዚአብሔር እንዲገልጥለት መተው አለበት፡፡ እንዲህ ሳያደርግ በራሱ ታግሎ ለመተርጐም የሚሞክር ከሆነ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያት ሃይማኖትን ሳይሆን ክሕደትን ያመጣል፡፡

፬. መጽሐፍ ቅዱስን በቤተ ክርስቲያን መረዳት

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ነው፡፡ የምንረዳውም በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነው፡፡ ያለ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚገድል ፊደል ነው (፪ኛ ቆሮ.፫፥፮)፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስን በቤተ ክርስቲያን መረዳት የምንለው ሐሳብ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ልዩ ያደርጋታል፡፡ የፕሮስቴስታንቱ ዓለም “ማንም እንደገዛ ፈቃዱ ማንበብ እና መተርጎም አለበት” ብሎ ያስተምራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ እንዳመኑትና እንደጸኑት የቤሪያ ክርስቲያኖች “ክርስቲያኖች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አለባቸው፤ መረዳታቸውም በቤተ ክርስቲያን መሠረተ ሃይማኖት እና በአባቶች ሕይወት ላይ የተመሠረተ (የማይጻረር) መሆን አለበት” ትላለች (ሐዋ.፲፯)፡፡ ይህንንም በሚፈስ ወንዝ እንመስለዋለን፡፡ ውኃው በመሐል የሚፈስባቸው ሁለቱ ግድግዳዎች (ዳርቻዎች) የቤተ ክርስቲያን ሕይወትን (አስተምህሮን) ሲወክልልን የእኛ መረዳት ደግሞ በመሐል የሚፈሰውን ውኃ ይመስላል፡፡ የምንተረጕመው እዚያው ወንዝ ውስጥ ብቻ ሆነን ነው፡፡ ነጻነታችን የተጠበቀ ቢሆንም ከወንዙ ዳርቻዎች ማለፍ አንችልም፡፡ እንዲህ ካልሆነ የቤተ ክርስቲያን መረዳት (Mind of the Church) እንስተዋለን፤ የቤተ ክርስቲያን ያልሆነና የእኛን ሐሳብም እንጨምራለን፡፡

ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመገናኛቸው ቀን መጻሕፍትን ያነቡ ነበር፡፡ ይህም በሐዲስ ኪዳን ቀጥሎ በሐዋርያት ሥራ እና በሌሎች የአበው ጽሑፍ ውስጥ እንደሰፈረው ክርስቲያኖች ጉባኤን ባደረጉ ጊዜ ሁሉ ከብሉይ ኪዳንም ከሐዲስ ኪዳንም የተውጣጡ ክፍለ ምንባባትን ያነብቡ ነበር፡፡ ይህ ትውፊት አሁንም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያን የዘመን አቈጣጠር እና ከሚከበሩ በዓላት ጋር ተስማምቶ የተሠራውን የዕለቱ ንባብ (ግጻዌው) የዚሁ መገለጫ ነው፡፡ ቅዳሴ ስናስቀድስ ብሉይ ኪዳኑ አለ (ምስባኩ)፣ ሐዲስ ኪዳኑ አለ (ወንጌል፣ የሐዋርያት ሥራ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት፣ ሌሎቹ መልእክታት እንዲሁም የዮሐንስ ራእይ)፡፡ በቅዳሴው የሚደረገውን እያንዳንዱ ሥርዓተ አምልኮውን ስንመለከት በእጅጉ እንደነቃለን፡፡ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን በአግባቡ የሚያስቀድስ፣ ከምሥጢራቱ የሚካፈል፣ ምንባባቱን በአግባቡ የሚከታተልና የሚያነብ፣ ሥርዓተ አምልኮውንም የሚያገናዝብ ከሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቀላሉ መረዳት ይችላል፤ የቤተ ክርስቲያን መረዳት (Mind of the Church) አለውና፡፡

፭. የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከሉ ክርስቶስ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ቋንቋ እንደ መጻፉ የተበታተነ መጽሐፍ አይደለም፡፡ አንድ ዓላማ ያለው እርስ በርሱ የማይጻረር መጽሐፍ ነው፡፡ ማዕከሉም ዓላማውም ክርስቶስ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በምሳሌ፣ በትንቢት እና በዕለት ዕለት ሕይወት ውስጥ ክርስቶስን የሚወክሉ ነገሮች አሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዘንድም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ ሰው ሆኖ የሠራው የማዳን ሥራ፣ በርሱ ያመኑ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ታሪካቸው እና ትምህርታቸው ክርስቶስን ማዕከል አድርጎ ተጽፎልናል፡፡ መጽሐፍም ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። ብርቱም መልአክ፥ መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ፡፡ በሰማይም ቢሆን በምድርም ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም፡፡ መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ፡፡ ከሽማግሌዎቹም አንዱ፡- አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቷል አለኝ” (ራእ.፭፥፩-፮)፡፡ የተዘጋ መጽሐፍ የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ ይልቁንም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ ድል የነሣው አንበሳ የተባለውም ክርስቶስ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ክርስቶስ ፈሪሳውያኑን እንዲህ ብሎ ገሥጿቸዋል፡- “እናንተ በመጻሕፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፡፡ እነርሱም ስለ እኔ የሚሰክሩ ናቸው” (ዮሐ.፭፥፴፱)፡፡

፮. ለእኛ እንደተጻፈ ማሰብ

“ኩሎ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ” እንደተባለ (ሮሜ.፲፭፥፬) የተጻፈው ሁሉ እኛን ለመገሠጽ ነው፡፡ ክቡር ዳዊትም “እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል” ይላል (መዝ.፹፮፥፮)፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ሐሳብ የሚናገርበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ሦስት ደረጃዎችን ማለፍ አለበት፡፡ የመጀመሪያው ታሪኩን ማጥናት ነው፡፡ ሁለተኛው ራሳችን በባለታሪኩ ቦታ ማስገባት ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ ያንን ታሪክ ለግል መንፈሳዊ እድገታችን መጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ከሉቃ.፲፥፴፡ ጀምሮ ያለውን የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ስናነብ ታሪኩን ካጠናን በኋላ ራሳችንን በተደበደበው ሰው ቦታ፣ በአይሁዳዊው እና በካህኑ ብሎም ባዘነለት ሳምራዊው ቦታ አስገብተን ሥነ ምግባራዊና ነገረ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመውሰድ ለግል መንፈሳዊ እድገታችን የሚጠቅሙ ነገሮችን መውሰድ ይጠበቅብናል፡፡ ዛሬ በዓለማችን ብዙ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጻፈላቸው ሰዎች የዘለለ ትርጉም (ድርሻ) እንደሌለው አድርገው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ስሕተት ነው፡፡ እያንዳንዱ ቃል እኛን ለማስተማር ለእኛው ጥቅም በመለኮታዊ ጥበብ እገዛ የተከተበ ነው፡፡

፯. ጸሎት

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸውን ነጥቦች በኋላ ጸሎትን በመጨመር ማንበብን መጀመር አለብን፡፡ መጸሐፍ እንዲህ እንዳለ፡- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለኹሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል” (ያዕ.፩፥፭)፡፡ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ሲያናግር፣ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በጸሎት እግዚአብሔርን ትጠይቃለች፡፡ በሃይማኖት የጸና ምላሿን ትሰጣለች፡፡ ምን ጊዜም በቤተ ክርስቲያን ወንጌላትና መልእክታት ከመጽሐፍ ቅዱስ ከመነበባቸው በፊት ስለሚነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጸሎት ይደረጋል፤ “ጸልዩ በእንተ ወንጌል ቅዱስ” እንዲል፡፡ እኛም “ይረስየነ ድልዋነ ለሰሚዐ ወንጌል ቅዱስ፤ ቅዱስ ወንጌልን ለመስማት የበቃን የተዘጋጀን አድርገን” እንላለን፡፡ (ሥርዓተ ቅዳሴ)
በጸሎት መንፈስ ቅዱስ በእኛ ዘንድ ሆኖ ለቅዱሳን የገለጠውን ቅዱሳት መጻሕፍቱን ይገልጥልን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምናለን፡፡ ይህ ጸሎት ልቡናችንን በምድራዊ ግብር ከመባከን ለይቶ ወደ ሰማያዊው ምሥጢር በጸጋ እግዚአብሔር ይሰቅለዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ጥቂት እንመልከት፡፡ · … መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የሚናገር መጽሐፍ ነው (ኢሳ.፮፥፩-፭፣ ዮሐ. ፩፥፩፣ ኢዮ. ፵፪፥፭፣ መዝ. ፸፫፥፫)።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድር ታሪክ (የሚታይ ታሪክ) ብሎም የማይታየውን ረቂቅ ታሪክ ከተመረጡ ሕዝቦች (አባቶች) ጋር ጨምሮ የያዘ መጽሐፍ ነው፤ ነገረ ቅዱሳንን (መውደቃቸውንና መነሣታቸውን) የሚያዘክር መጽሐፍ ነው (ሐዋ.፱፣ ፪ኛ ሳሙ.፲፩)፡፡ ለምሳሌ በውስጡ የክቡር ዳዊትን እንዲሁም የቅዱስ ጴጥሮስን መውደቅና መነሣት ይዘክራል፤· መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጽሐፍ ብቻ አይደለም፤ ታሪክም መዝሙርም ሕግጋትንም ከወንጌል ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ በጠለቀ የሥነ ጽሐፍ ጥበብ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የጠቢቡ ሰሎሞንን እና የቅዱስ ጳውሎስን መጻሕፍት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትሕትናን ከቅንነትና ከመጻሕፍት ንባብ ከትርጓሜ ጋር አንድ አድርገን የማንበብና የመረዳት አቅማችንን እናጎልብተው፡፡

ብዙዎች ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወጥተው የቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስን ንባብ እንዲሁ በፈቃዳቸው እና በግል ምልከታቸው ለመተርጎም በሚያረጉት ሙከራ ነው። ቤተ ክርስቲያን ግን እንደ ሠለስቱ ምዕት፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን የመሳሰሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የጻፏቸውን ድርሳናትና ትርጓሜያት ለልጆቿ በማስተማር ከግል አረዳድ ወጥተን የተነገረበትን ትክክለኛ ዐውድና ምሥጢር ጠብቀን እንድንረዳ ታስተምረናለች፡፡ የቅዱሳን አባቶቻቸው በረከታቸው አትለየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር