“በክፉዎች መንገድ አትሂድ“ (ምሳ.፬÷፲፬)
ዲያቆን ዳዊት አየለ
ሚያዚያ ፳፮፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
እግዚአብሔር መላእክትንና የሰው ልጅን ሲፈጥር የፈጠረበት ትልቁ ዓላማ ስሙን ቀድሰው ክብሩን እንዲወርሱ ነው፤ ነገር ግን ክፋትን ኃጢአትን ዲያብሎስ (አስቀድሞ ሳጥናኤል የተባለ) ከልቡ በሐሳቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለመ መላእክት አመነጫት፤ አመንጭቶም አልቀረም፤ ከራሱ ጋር ሌሎች እርሱን የመሰሉ መናፍስትን (መላእክትን) ይዞ ከሰማያዊ ክብሩ ወደቀ::
አዳምንና ሔዋንንም በእባብ ሰውነት አድሮ የእባብን አንደበት አንደበቱ አድርጎ ክፉ ምክርን በሔዋን በኩል መከራቸው፤ በምክሩም አዳምና ሔዋን ከመልካሙ ጎዳና (ከትእዛዘ እግዚአብሔር) ወጥተው በክፉ ምክሩ ተታለሉ፤ በምክረ ከይሲ ተመርተው ባጠፉት ጥፋት ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔርንና ገነትን የመሰለች ባለ መልካም መዓዛ ቦታን አጣን (እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ተዋሕዶ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ በእርሱ ቁስል እስኪያድነንና ልጅነታችንን እስኪመልስልን ድረስ)፤ ከገነት ከወጣን በኋላም ጠላት ዲያብሎስ የክፋት ምክሩን እስከዛሬ ድረስ አላቋረጠም፤ ለቃኤል የሰው ልጅን እንዴት መግደል እንደሚቻል ለመጀመሪያ አስተምሮ አቤልን እንዲገድለው ምክንያት ሆነው ከዚያ በኋላ በሰው ልጆች መካከል ክፋት ነግሦ ዛሬም ብዙዎች በዚህ በፍኖተ ቃኤል ሲጓዙ መመልከት የተለመደ ክስተት ሆኗል። (ዘፍ.፫÷፬-፭፣ዘፍ.፬፥፩-፰፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ)
ለሰው (በነፍስ በሥጋ) ጉዳት የሚሆን ሁሉ፣ ከትእዛዘ እግዚአብሔርና ከሕገ እግዚአብሔር ያፈነገጠ ነገር ሁሉ ክፋት (ኃጢአት) ይባላል። ዘረኝነት፣ የሰው ነፍስ ማጥፋት፣ የሰው የሆነውን መቀማት፣ ባዕድ አምልኮ፣ ባልንጀራ ላይ በሐሰት መመስከር፣ ራስ ወዳድነት…ወዘተ የመሳሰሉ ከክፋት መካከል ናቸው። ጠቢቡም “…በክፎዎች መንገድ አትሂድ…” ብሎ የሚናገረው ይህንኑ መንገድ መንገዳቸው አድርገው ከሚጓዙ ሕገ እግዚአብሔርን ከዘነጉ ሰዎችና መንገዳቸው (ሥራቸው) ራሳችሁን ለዩ ሲለን ነው። መንገዳቸው ከፍኖተ ክርስቶስ፣ ከፍኖተ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከፍኖተ መስቀልና ከፍኖተ ቅዱሳን ከወጣ (ከተለየ) ሰዎችና ግብራቸው ተጠንቀቁ ሲል ነው። ንጉሠ እስራኤል ቅዱስ ዳዊትም በዚህ መንገድ ያልሄደን ሰው “ምስጉን ነው፥ በዝንጉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኀጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ሰው” በማለት ያመሰግናል። (መዝ.፩÷፩) ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለተሰሎንቄ ሰዎች በላከው በመጀመሪያ መልእክቱ “ወንድሞቻችን፥እንማልዳችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትንም ገሥጹአቸው…” በማለት ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን የወጣ መንገድ ተግሣጽ የሚገባው እንደሆነ ይነግረናል። (፩ኛተሰ.፭÷፲፬)
ክፋት (ኃጢአት) እግዚአብሔርን ያሳጣል፤ እግዚአብሔርን ያጣ ሰው ደሞ የሞት ሞትን (የነፍስ ሞትን) ይሞታል፤ ፍርዱም ለዘለዓለም ነው። በነቢዩ ሕዝቅኤል አድሮ ክፋት ስለምትሠራ ነፍስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “…ኀጥአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” (ሕዝ.፲፰÷፬) እንግዲህ ትልቁ ሞት የነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት ነውና “አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ” የሚለውን የነቢዩን ቃል ሰምተን ከክፋት ጎዳና ልንመለስና የጽድቅን ሥራ ልንሠራ ይገባል። (ኤር.፲፰ ፥ ፲፩)
ክፋት ከመንግሥተ እግዚአብሔር (መንግሥተ ሰማያት) ይለያል፤ አስቀድሞም የተፈጠረንበት ዓላማ ስሙን ቀድሰን መንግሥቱን (መንግሥተ ሰማያትን) እንድንወርስ ነው፤ ነገር ግን በክፉዎች መንገድ የምንመላለስና ክፋትን የምናደርግ ከሆነ ከመንግሥቱ እንለያለን። ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኤፌሶን መልእክቱ “ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ።” (ኤፌ.፭ ፥ ፭) ስለዚህ እንደ አምስቱ ሰነፎች ደናግል ሳንሆን እንደ ብልሆቹ ደናግል መብራትና ዘይታችንን (የክፋት መንገድ ያልሆነ በጎ ምግባርን) አዘጋጅተን ሙሽራውን ልንቀበል ንቁ መሆን ይጠበቅብናል።
ክፋት ከሰውነት ያጎድላል፤ የሰው ልጅ አምሳለ ሥላሴ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ነው፤ ሰው እግዚአብሔር ወልድ አምላክ በተለየ አካሉ ሥጋውን የተዋሐደለት ድንቅ ፍጥረት ነው፤ ነገር ግን የክፋት አባቷና መሪዋ ዲያብሎስ እንደመሆኑ በክፉዎች ጎዳና የምንሄድና የምንቀና ከሆነ ግብረ ዲያብሎስን ገንዘብ እያረግን ነውና በግብራችን የእርሱ (ዲያብሎስ) ልጆች እንሆናለን። “እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ። ”(ኤፌ ፭ ፥ ፩) “እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እናንተም እኔን ምሰሉ” የሚለውን የሐዋርያውን ቃል ሰምተን የሥላሴ ሥራ የሆነውን ሰውነታችንን በክፉዎች ጎዳና ባለመጓዝ ልናከብር ልንጠብቅ ይገባል። (፩ኛ.ቆር ፲፩ ፥ ፩)
ክፋት ያቅበዘብዛል፤ ከእግዚአብሔር ይለያልና የኅሊናን ዕረፍት ይነሳል፤ የመጀመሪያው ነፍሰ ገዳይ የነበረ ቃኤል የአቤልን ነፍስ ባጠፋ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ነበር ያለው “…በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” (ዘፍ.፬፥፲፪) ጠቢቡም በተግሣጽ መጽሐፉ ስለ ክፉ ሰው ሲናገር እንዲህ ይላል “ኃጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤”(መጽ.ተግ.፬ ፥፩)
ክፋት (ኀጢአት) ከእግዚአብሔር የሚለየን እኩይ ተግባር መሆኑን ተገንዝበን በቀናው ጎዳና በትእዛዘ እግዚአብሔርና ሕገ እግዚአብሔር እየተመራን ለመንግሥቱ የሚያበቃንን መልካም ፍሬ ልናፈራ ይገባል። አባ ሙሴ ጸሊም እንዲህ ይላል፤ “ማንንም አትጉዳ፤ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፤ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፤ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው አትተማመን፤ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋራ አትደሰት። በማንም ላይ አትማረር፤ ነገር ግን ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል በል። ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፤ በሐሜቱም አትደሰት፤ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው። በማንም ላይ የጥላቻ ሐሳብ አይኑርህ፤ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት። ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው።” (ከቅዱሳን አበው በአባ ተክለማርያም ወልደ ትንሣኤ)
እግዚአብሔር አምላክ የእኛን በክፉ መንገድ ተጉዘን መጥፋትን አይፈልግምና እንዲህ ይላል፤ “ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ፣ በተራራም ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፣ ሰውንም ባያስጨንቅ፥ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ፥ ፈጽሞም ባይቀማ፥ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቆተውንም ከልብሱ ቢያለብስ፣ በአራጣ ባያበድር፥ አትርፎም ባይወስድ፥ እጁንም ከኀጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፤ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል።” (ሕዝ.፲፰፥፭-፱)
ጥሪውን ሰምተን፣ ከክፉ ጎዳና ተለይተንና በጎ ምግባር ሠርተን ለመንግሥቱ እንድንበቃ ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!