በኬንታኪ የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር መካሔዱን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ
ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል በኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ አዘጋጅነት ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር መካሔዱን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ፡፡
የመርሐ ግብሩ ዓላማ ምእመናኑ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲበረቱ፣ ለሃይማኖታዊ ጥያቄዎቻቸውም ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ምላሽ እንዲያገኙ ለማገዝ መኾኑን የግንኙነት ጣቢያው ለአሜሪካ ማእከል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ የመጀመሪያውና ብቸኛው የጠበል አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ መኾኑን የጠቀሰው ግንኙነት ጣቢያው ምእመናን ጠበል እንዲጠመቁና ከበረከቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ፣ እንደዚሁም የአግልግሎት ትጋት ልምድን ከአጥቢያው ካህናትና ምእመናን ቀስመው አርአያነት ላለው አገልግሎት እንዲነሣሡ ለማበረታታት መርሐ ግብሩ በኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲካሔድ መደረጉን ገልጿል፡፡
የግንኙነት ጣቢያውን መረጃ ዋቢ በማድረግ የአሜሪካ ማእከል የላከልን ዘገባ እንደሚያመላክተው መነሻውን ከኢንዲያናፖሊስ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ባደረገውና ከአንድ መቶ ሠላሳ አምስት የሚበልጡ ምእመናንን ባሳተፈው በዚህ የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በጉዞ ወቅት በአውቶቡሶች ውስጥ የውይይት እና የመዝሙር አገልግሎት ለሁለት ሰዓታት ያህል ተሰጥቷል፡፡
ምእመናኑ ከቦታው በደረሱ ጊዜም በደብሩ ማኅበረ ካህናትና ምእመናን አቀባበል የተደረገላቸው ሲኾን፣ መርሐ ግብሩ በጸሎተ ኪዳን ከተጀመረ በኋላ የኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት አያልነህ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልእክታቸውም ሕዝበ ክርስቲያኑ በቅዱስ ገብርኤል ጠበል በመጠመቅ እያገኘ ያለውን ፈውስ አስረድተው የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎችም ጠበል በመጠመቅና በመጠጣት ከቅዱስ ገብርኤል በረከት እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
የሊቀ ካህናት አያልነህን ማሳሰቢያ ተቀብለው ምእመናኑ ጠበል ከተጠመቁና ከጠጡ በኋላ የጠዋቱ መርሐ ግብር የተጀመረ ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩም “የተሰወረ መዝገብ” በሚል ርእስ በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡
እንደዚሁም በሊቀ ማእምራን ዓባይ አጥሌ፣ በሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ እና በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ልዩ ልዩ ዝማሬዎች ቀርበዋል፡፡
ከምሳ ሰዓት በኋላም መልአከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከምእመናን ለተነሡ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችም በቤተ ክርስቲያን መምህራን ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
የኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ ለአሜሪካ ማእከል በላከው መረጃ እንደ ገለጸው መዝሙር በማቅረብ፣ ትምህርቶችን በመከታተልና በጥያቄና መልስ ውድድሮች በመሳተፍ ሕፃናት ጭምር በሐዊረ ሕይወቱ የታደሙ ሲኾን፣ በቀረቡት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶችም ምእመናኑ ተደስተዋል፡፡
እንደ ግንኙነት ጣቢያው ማብራሪያ ዲያቆን አሮን እና ዲያቆን ኖሃ የተባሉ ሕፃናት “በሕይወቴ በዘመኔ ደስ የሚለኝ ለኔ በወንጌል ማመኔ” የሚለውን መዝሙር በገና እየደረደሩ ባቀረቡበት ሰዓት የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች በሕፃናቱ ችሎታ የተሰማቸውን ደስታ በዕልልታ ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡
የኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እና የኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት እንደዚሁም ሰንበት ት/ቤቶቹ ከኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ ጋር በአንድነት መሥራታቸው ለሐዊረ ሕይወቱ በስኬት መከናወን የላቀ ሚና የነበረው ሲኾን፣ በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም የግንኙነት ጣቢያው ሰብሳቢ ዶክተር በላይነህ ደስታ ለሐዊረ ሕይወቱ በስኬት መከናወን ትልቅ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ዅሉ በማኅበረ ቅዱሳን ስም መንፈሳዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ከምእመናኑ የተገኘው $1747 (አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ዐርባ ሰባት ዶላር) መርሐ ግብሩ ለተካሔደበት ለኬንታኪ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ገቢ ከተደረገ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡