በኦሞ ወንዞች ዙሪያ ተስፋ የሚያደርጉ ዓይኖች!

በማኅደረ ታሪኩና ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ሰኔ 03፣ 2003 ዓ.ም 
 

Debub_Omo1.jpg

 
ከሐመር ብሔረሰብ አባላት ለአንዱ፣ የፈጠራችሁ ማን ነው? ብላችሁ ጥያቄ ብታቀርቡ በእምነት በጠጠረ፣ ጥያቄያዊ በሆነ ፊትና የዋሕ ልቡና “ቦርጆ ነዋ! ቦርጆ፣ ከእርሱ በረከት ያልተቋደሰ፣ በእርሱ እቅፍ ውስጥ የሌለ፣ እርሱ ያላበላው፣ እርሱ ያላጠጣው ማን አለ? እርሱ ሁሉን በፍቅር የሚንከባከብ፣ ሕፃናትን የሚያሳድግ የፍቅር አምላክ ነው” ይሏችኋል፡፡

በዚህም አያቆሙም “ቦርጆ በእኛ መካከል ሲኖር ነበር፣ በቆይታ አንዳንዶችDebub_Omo22.jpg በልባቸው ክፉ አስበው አስቀየሙት፣ ቦርጆን ገረፉት፣ መቱት፣ አቆሰሉት፡፡ እርሱም ከእንግዲህ ‘ከእናንተ ጋር ሆኜ /እየኖርኩ/ የማበላችሁ የማጠጣችሁ አይምሰላችሁ፡፡ ወደ ሰማይ እሄዳለሁ በልባችሁ ግን ለምኑኝ አበላችኋለሁ፣ አጠጣችኋለሁ’ ብሎን ሄዷል፡፡” በማለት ስለ አምላካቸው ያብራራሉ፡፡

 
ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገልጻል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያን ክፍል አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አቡነ ዜና ማርቆስ እና ሌሎችም ቅዱሳን አበው የደከሙበት፣ የወንጌልን የምሥራች፤ የጌታችንን በዚህ ዓለም ከእኛ ጋር ተመላልሶ ማስተማሩን፣ አበርክቶ ማብላቱን፣ ተአምራት ማድረጉን፣ መገረፉን፣ መሰቃየቱን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መነሣቱን፣ ማረጉን ያስተማሩበት፣ ያመኑትንም ያጠመቁበት፣ በኪደተ እግራቸው የባረኩት ምድር ነው፡፡ ማን ያውቃል ይሄ የቦርጆ ትርክት ከዚያ መጥቶ ቢሆንስ? ለአሁኑ እግረ መንገዳችንን አንሣነው እንጂ ጉዳያችን ይሄ ሆኖ አይደለም፡፡ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት እየተሠራ ያለውን ስብከተ ወንጌል የማስፋፋት አቢይ ተግባርና ተያያዥ ጉዳዮችን በአጭሩ ለመቃኘት እንጂ፡፡
 
ሀገረ ስብከቱ
ከአዲስ አበባ 781 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ መቀመጫውን ጂንካ ከተማ ያደረገው የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በሥሩ ዘጠኝ ወረዳዎች ያሉት ሲሆን በእነዚህ ወረዳዎች እስከ 1998 ዓ.ም 29 አብያተ ክርስቲያናት ታንጸው ነበር፡፡
በዞኑ 440.623 የሚጠጋ ሕዝብ ያለ ሲሆን ከእነዚህም 24.35 በመቶው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ቀሪዎችም የባዕድ አምልኮ የተወሰኑትም የሌሎች እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡
ከ16 ያላነሱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ሐመር፤ በና፤ ፀማይ፤ ካሮ፤ ዲሚ፤ ባጫ፣ ዳሰነች፣ ኤርቦሬ፣ ማሊ፣ አሪ፣ በዲ፣ ሙርሲና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ እንደሚናፍቅ ነፈሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፡፡

በሀገረ ስብከቱ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የታነፁት ከተማን መሠረትDebub_Omo15.jpg አድርገው በመሆኑ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገጠራማ ቀበሌዎች ሕዝብ ያገናዘበ አልነበረም፡፡ ስለዚህም የገጠሩ ሕዝብ መጠመቅ እያማረው ሳይጠመቅ፣ መማር እያማረው ሳይማር፣ መስቀሉን መሳለም እያማረው ሳይሳለም፤ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ እንደሚናፍቅ ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች” እንዳለው ነፍሳቸው አምላክን እንደናፈቀችና እንደተጠማች ብዙ ቀኖች መሽተው ብዙ ሌሊቶች ነግተዋል፡፡ መዝ 41፥1

አንድ የአካባቢው ምእመን ‹‹ከእንግዲህ ብሞትም አይቆጨኝ፤ ሥጋዬ እንዲሁ በየሜዳው አይወድቅምና ይህ የዕድሜ ዘመኔ ሙሉ ናፍቆቴ ነበር” የሚለው ንግግራቸው የናፍቆታቸውን ልክ ያሳያል፡፡

Debub_Omo13.jpgየሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም በየቦታው በሚደርሱበት ጊዜ የሚኖረው አቀባበልና የሕዝቡ ስሜት፥ ለመጠመቅ ያለው ጉጉት ልዩ ነበር፡፡ አባታችን “ዝናብ አምጡልን የሚለው” የሽማግሌዎች ጥያቄ በፈጣሪ ያላቸውን ተአምኖ ያሳያል፡፡ አንድ አረጋዊ አባትም “እኛ እድላችን ሆኖ ታቦት በመምጣቱ እናመሰግናለን፡፡ አባታችንም በመምጣታቸው ደስ ብሎናል” በማለት በአስተርጓሚ ሲናገሩ በልዩ ስሜት ነበር፡፡

በቅርብ ጊዜ ሀገረ ስብከቱ ለሚያደርገው አብያተ ክርስቲያናትን የማነጽ፣ የመሠረት መስቀል የማስቀመጥ ሰፊ እንቅስቃሴ፥ ማኅበረሰቡ ሁሉ ርስቱ፣ ጉልቱ ማንነቱ የሆነውን መሬቱን በገዛ ፈቃዱ ነበር ቆርሶ የሰጠው፡፡ ይሄም የማኅበረሰቡን ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅርና ጉጉት አጉልቶ የሚያሳይ ታሪካዊ ክንዋኔ ነው፡፡

ከዚህም በላይ አንደኛው ሲጠመቅ ሌላኛው እኛስ መቼ ነው የምንጠመቀው? እያሉ ሀብተወልድና ስመ ክርስትና የሚያገኙበትን ቀን በመናፈቅ የሚያቀርቡት ጥያቄ ብፁዕነታቸው በደረሱበት ካህናትም በታዩበት ሁሉ የሚያጋጥም ነው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረትና የሀገረ ስብከቱ ምላሽ

እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳን ክርስትናን ቢናፍቁም የተለያዩ ምክንያቶች ፍላጎታቸው እንዳይማላ እንቅፋት ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት በሞግዚትነት መተዳደሩ አንደኛው ሲሆን ብሔረሰቦቹ ወደ ሰፈሩባቸው ቦታዎች ለመጓዝ በእግርና በበቅሎ እንጂ በተሽከርካሪ አስቸጋሪ መሆናቸው ይሄንንም ተቋቁሞ ለማስተማርና ለመቀደስ የሚችሉ በቂ ካህናት አለመኖራቸው እንደዋነኛ ምክንያት ይወሰዳሉ፡፡

ይሁንና ቅዱስ ሲኖዶስ ለቦታው በሰጠው ትኩረት ከ1998 ዓ.ም ወዲህ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ መንበሩን ጅንካ ከተማ ላይ ተክሎ እንዲንቀሳቀስ ፈቅዶ ሊቀ ጳጳስ መድቦለታል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ለውጦችን ለማምጣት እያደረገ ያለው እንቀስቃሴ የሚበረታታ እንደሆነ የተሠሩት ሥራዎች ያሳያሉ፡፡

Debub_Omo9.jpg90 በመቶ የሚሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል ያማከሉ በተጨማሪ 37 ቦታዎች ላይ የመሠረት መስቀል ተቀምጧል፡፡ ወደፊት ቤተ ክርስቲያን እንደሚሠራባቸው ተስፋ ይደረጋል፡፡ ለጊዜው የአካባቢው ምእመናን በየዋሕ ልቡናና በፍጹም እምነት ቦታዎችን እየተሳለመ ይጠብቃቸዋል፡፡

እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት አጥምቁን እያሉ በርካቶች እስከ አሁን እየመጡ ይገኛሉ፡፡ በዞኑ ከሚገኘት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች 50,000 የሚሆኑትን በማጥመቅ የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት እጅግ የሚያበረታታ ነበር፡፡

ተባርከው የመስቀል ምልክት ከተደረገባቸው 37ቱ ቦታዎች የ16ቱ ግንባታDebub_Omo24.jpg ተጀምሯል፡፡ ከእነዚህም 6ቱ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነው በ3ቱ አገልግሎት መሥጠት ተጀምሯል፡፡  አማኞችን ለማብዛት፣ ያመኑትን ለማጽናት፣ ቀድሶ ለማቁረብ በቋንቋቸው የሚያስተምራቸው የአካባቢው ተወላጅ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከተጠመቁትም ካልተጠመቁትም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የአብነት ትምህርት እንዲማሩላቸው ፈቃደኛ የሆኑትን ልጆቻቸውን ሙሉ ወጪአቸውን በመሸፈን ጂንካ ከተማ በሚገኘው የአንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ገብተው እንዲማሩና የዲቁና ማዕረግ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም ከወዲሁ አገልጋዮችን ለማግኘት የማስቻል ሥራን ያጠናክራል፡፡ ከዚህ ሁሉ የብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ትጋትና ኖላዊ አባግዐነት ዋናውን ስፍራ የሚይዝ ነው፡፡

Debub_Omo27.jpgብፁዕነታቸው ከየብስ እስከ የባሕር ላይ ጉዞ፣ ከጂንካ እስከ ኬንያ ጠረፍ፣ ከእግር ጉዞ በሞተር ላይ ተፈናጥጦ እስከ መጓዝ ድረስ በ16ቱም የብሔረሰብ አባላት ዘንድ እየተገኙ ከደከመኝ ሰለቸኝ፣ ሕመም ተሰምቶኛልና ዛሬን ልረፍ፣ ዛሬ አይመቸኝም አልገኝም፣ ዙፋን ዘርጉልኝ ምንጣፍም አንጥፉልኝ ሳይሉ፣ እንደቀየው አብረው ተመግበው፣ ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በአንድ እቃ ቦርዴ ፉት በማለት ጠጥተው ማኅበረሰቡን መስለውና ተዋሕደው አፅናንተዋል፣ መክረዋል፣ አስተምረዋል፣ አጥምቀዋል፡፡ የሕፅናትን መዝሙር፣ የወጣቶችን ጭፈራ፣ የሽማግሌዎችን ምርቃት ተቀብለዋል፡፡
 
ቀሪ ተግባሮች

ይህ ሁሉ ሆኖ አሁንም ብፁዕነታቸውን የሚያሳስባቸው የአብያተ ክርስቲያናት መታነጽ፣ የማኅበረሰቡ በአንዲት ተዋሕዶ ጥላ ሥር መሰብሰብ ነው፡፡ “ከአሥራ ስድስቱም ወረዳዎች በርካታ ወገኖችን አጥምቀናል እያጠመቅንም ነው፡፡ በዝግጅት ላይ ያሉ እነዚህ ወገኖች ቤተ ክርስትያን ያስፈልጋቸዋል፣ ለወገን ደራሽ ወገን ስለሆነ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለን ለእነዚህ ወገኖች እንድረስላቸው፤ በሚያልፈውም ገንዘብ የማያልፈውን ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” በማለት ያሳስባሉ፡፡

ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም ገና የቀሩ ሥራዎች እንዳሉ መረዳት አያዳገትም፡፡ የሰው ሕንፃ መሠረት ተጣለ እንጅ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የላቸውም፡፡ የብፁዕነታቸው ንግግርም ይሄንን ይገልጻል፡፡ የመሠረት መስቀል ከተቀመጠባቸው ቦታዎች 88 በመቶው የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት ያልታነፁባቸው በመሆኑ ሕብረተሰቡ መስቀሎቹን በመሳለም የቀሪዎቹን ወገኖች መጠመቅ፣ የእነርሱን ዕለት ዕለት ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ማድረስን ተስፋ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የሀገረ ስብከቱን አገልግሎት ከባድ አድርጎ የቆየው አንዱ ጉዳይ የሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል በአስተርጓሚ መሠጠቱ ነው፡፡ ከየብሔረሱ ሰዎች አዲስ አበባ ድረስ አምጥቶ በማሰልጠን መልሶ ወደ አካባቢያቸው ማኅበረሰብ በመላክ ገብተው በቋንቋቸው እንዲያስተምሩ በማድረግ አጥጋቢ ውጤት ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ ሥራ በዋነኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ለዚህም በጀት፣ አሠልጣኝ፣ የሥልጠና ቦታና ቁሳቁስ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከየትም አይመጣም፣ ከምእመናን እንጅ፡፡

በተለይም በእነዚህም በረሀማና ጠረፋማ በሆኑ አካሳቢዎች የወንጌል አልግሎት በዘላቂነት የሚዳሰስበትን መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡

የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛ ባርያዎቹ ተነስተን እንሠራለን፡፡

የተጠቀሱት ችግሮች አጣዳፊ ምላሾችን የሚፈልጉ እንዲሁም በረጅም ጊዜ እቅድ የሚሠሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም የምእመናንን ርብርብ የሚጠይቁ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

Debub_Omo10.jpgይህንን ለማስተባበር የሚችል በሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የሚመራ አንድ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ “የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያልማትና ልማትና ሕንፃ ቤተ ክርስትያን አሠሪ ኮሚቴ” በሚል ስያሜ የተቋቋመው ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢ/ር ዳንኤል ኃይለ “እኛ ተነስተናል የሰማዩ አምላክ ያከናውንልናል፡፡ ሕዝቡ ምኞቱ የመሠረት መስቀል የተሠራባቸውን ቦታዎች ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ማየት ነው፡፡ ስለዚህ የመሠረት መስቀል የተተከለባቸው 37ቱ አብያተ ክርስትያናት እስኪሠሩ ድረስ፣ ስብከተ ወንጌል በአሥራ ስድስቱም ብሐሮች ቋንቋ እስኪሰበክ ድረስ እንተጋለን፡፡” የሚሉት ምክትል ሰብሳቢው ይቀጥሉና “ይህንን ለማድረግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልታዊ ዕቅድ በመዘርጋት ከየብሔረሰቦች ዲያቆናትን፣ ካህናትን፣ መምህራንን አምጥቶ በማሰልጠን እናወጣለን ብለን እናስባለን፡፡ ይህንንም ከእግዚአብሔር ጋር እናሳካዋለን” ይላሉ፡፡

ለዚህ ሥራ እንዲያግዝ በማሰብ ኮሜቴው የሀገረ ስብከቱን እንቅስቃሴና የምእመኑን ሁኔታ የሚያሳይ አሳዛኝና ልብ የሚነካ ፊልም አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ “በእውነት በዚህ ፊልም ሐዋርያዊ ተልዕኮ ምን እንደሚመስል ይረዱበታል” የሚለው ፊልሙን የተመለከተው ዲያቆን በረከት ነው፡፡ “ምን አልባትም ቀጣዮች ቅዱሳን ከዚያ አካባቢ ይመጡ ይሆናል፣ ማን ያውቃል?” በማለት ራሱን የሚጠይቀው ዲየቆን በረከት የምእመኑ ንፁህ እምነትና የዋህነት ልቡን የነካው ይመስላል፡፡

በዋነኝነት ግን ትኩረት ተሰጥቶ ለጊዜው የተሠራባቸውና እየተሠራባቸው ያሉ ዝግጅቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከግንቦት 24 እስከ 28/2003 ዓ.ም በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ውስጥ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ነበር፡፡ በአውደ ርዕዩ የሀገረ ስብከቱ እንቅስቃሴዎች በሰፊው የተዳሰሱ ሲሆን ብዙ ምዕመናን ጎብኝተውታል፡፡ “እኔ ፕሮቴስታንት ነበርኩ፤ ከዛሬ ጀምሮ ግን ኦርቶዶክስ ሆኛለሁ፤ መጠመቅም እፈልጋለሁ” በማለት አንድ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ አውደ ርዕዩን በማየት የተመለሰበት ሁኔታ ነበር፡፡  

እነዚህን ወገኖቻችን ለመታደግ ከተዘጋጁት መርሐ ግብራት ውስጥ በርካታ ምእመናን ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሰኔ 5 ቀን 2003 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሾች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ይኸውም ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ የሚደረገው ነው፡፡ ጉባኤው በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሰ/ት/ቤቶች ኅብረት ጋር በጋራ የተዘጋጀ እንደሆነ ታውቁል፡፡

ይህ ጉባኤ የኢንተርኔትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በመላው ዓለም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊሠራጭ የሚችልበት እድል እንደሚኖር አስተባባሪ ኮሜቴው ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ባለ እዳ ብትሆንም ገና ያላስተማረቻቸውና ያላጠመቀቻቸው በሥሯ ብዙ ምዕመናን አሉ፡፡ እነርሱም ሁሌ ጡት እንደሚፈልግ ሕፃን እጃቸውን ይልካሉ፣ እናቱ እንደጠፋችበት ሕፃን በር በሩን ይመለከታሉ፡፡ መቼ ይሆን የምንደርስላቸው? በእንደዚህ ዓይነት ጉባኤያት? ምን አልባትም አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡