በእንተ ዕረፍቱ ለተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ ፳፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

የስሙ መነሻ ፊደሉ ትእምርተ መስቀል የሆነው፣ የወንጌል ተቀዳሚ ስም ማቴዎስ፣ የቅዱስ ወንጌል ጸሐፊዋና ሰባኪዋ ማርቆስ፣ የነፍስና የሥጋ ሐኪም ሉቃስ፣ ከሁሉ ይልቅ ሥልጣኑ ከፍ ያለ ጴጥሮስ፣ ሰማያዊ አርበኛ ሚናስ፣ አነዋወሩ በብቸኝነትና በንጽሕና የሆነ ኤልያስ፣ የቤተ ክርስቲያን የልጆቿ አባት ባስልዮስ፣ የቤተ ራባው ጸዋሚ ተሐራሚ ዮሐንስ፣ ዐሥረኛው የአርማንያው ጎርጎርዮስ፣ ግሙደ እግር ያዕቆብ ሐዋርያ፣ እንግዳ መቀበል ፍጹም ተግባሩ የሆነ አብርሃም፣ ጸሐፊ ምሥጢራት ወጥበባት ሄኖክ፣ መሥዋዕቱ የሠመረለት አቤል፣ ሕዝብን የሚያስተዳድር ዮሴፍ፣ እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና የሚያመሰግን ዳዊት፣ ከሐዲዎችን የሚበቀል ቄርሎስ፣ የነገደ እስራኤል አባት ያዕቆብ የተባለ፣ መሥዋዕተ ቊርባንን የሚያሣርግ ከኪሩቤል እንደ አንዱ የሆነ፣ ትዕግሥቱ ፍጹም እንደ ኢዮብ ትዕግሥት የሆነ፣ የጳውሎስ ደቀ መዝሙር ቲቶ የተባለ፣ እንደ ሆሴዕና እንደ ዮፍኒ ልጅ እንደ ካሌብ ግብረ መልካም የሆነ፣ የእግዚአብሔር የምስጋናው አዳራሽ ጽኑዕ የምሰሶ ዐምድ የሆነ፣ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ የገሊላው ናትናኤል የተባለ፣ የመርዓስ ዓቃቤ ሕግ ቶማስና የጋዛው ፊልጶስ የተባለ፣ ለእንጦንስና ለመቃርስ ልጆች መነኮሳት በሙሉ በባሕርም ሆነ በየብስ ቢሆን ክብራቸው ሞገሳቸው የሆነው ኢትዮጵያዊው አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍት በዓሉ ይከበራል፡፡ (መልክአ ተክለ ሃይማኖት)

ጸሎቱ፣ ምልጃው፣ ተረዳኢነቱ አይለየን፤ በረከቱ ይደርብን!