‹‹በእሳትና በውኃ መኻከል አሳለፍኸን›› (መዝ.፷፭፥፲፪)

ሐምሌ ፲፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ሥራው ግሩም የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ማዳንም መግደልም የሚችል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ (መዝ.፷፭፥፫) በእርሱ የሚታመኑት ቅዱሳን ሰማዕታት የሚደርስባቸውን መከራና ፈተና ሁሉ በጽናት፣ በልበ ሙሉነት የሚያልፉት ለዚህ ነው፡፡

እሳት ለቅዱሳን ሰማዕታት ጌጣቸው ነው፡፡ በመልክአ ሥላሴ ‹‹የሰማይ ግምጃ ብርሃን ሸማኖች የሆናችሁ ሥላሴ ሆይ ልብሰ ምሕረታችሁ የሰማዕትነት ልብስን ይሁነኝ፤ የእስጢፋኖስ ልብስ ደንጊያ በእኔ ላይ የለምና፤ የሕፃኑ ቂርቆስ ጌጡ የሚሆን እሳትም በእኔ ላይ የለምና››  ብለን የምንጸልየውም ለዚህ ነው፡፡ (መልክአ ሥላሴ፡- ለአቁያጺክሙ)

ወርቅና ብር በእሳት ተፈትነው እንደሚጠሩ ቅዱሳን ሰማዕታትም በመከራ ውስጥ ተፈትነው እግዚአብሔርን አስደስተው ለእኛም የጽናት ምልክት ሆነው የክብር አክሊልን በመቀዳጀት ከገቡ መውጣት፣ ካገኙ ማጣት እና መከራ ወደ ሌለበት ዘለዓለማዊ ማረፊያቸው ይሄዳሉ፡፡

ቅዱሳን ሰማዕታት በመከራ ነፍስ ከመፈተን በመከራ ሥጋ መፈተንን መርጠው፣ ነፍሳቸውን በእሳተ ገሃነም ከመፈተን በምድራዊው ሰው ሠራሹ እሳት ውስጥ ሥጋቸውን ሳይሰቅቁ በመጨመር በመፈተን ዘለዓማዊ ዕረፍት ማግኘትን መርጠዋል፡፡

ሰው በባሕርዩ እንዲራባ በክፉ ግብር የሚራቡ አጋንንት እያደሩባቸው ዓላውያን ነገሥታት ቅዱሳን ሰማዕታት ላይ በጠላትነት እየተነሡ ያልፈፀሙት ክፉ ሥራ የለም፡፡ በሐምሌ ፲፱ ቀን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነትን ያገኙት ልጅ እና እናት ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣም ስለ ንጽሕት ሃይማኖታቸው ለመመስከር ፈተናቸው የመጣውም ከዓላውያን ነገሥታት አንዱ በሆነው በእለ እስክንድሮስ ነው፡፡

ይህ ከሓዲ መኮንን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስን ይዞ ‹‹ስምህ ማነው›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ  ‹‹ነቅዕ ዘእምዐዘቅት ንጸሕ ወእማይ ዘኢይማስን ክርስቲያን ስምየ፤ ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውኃ የተገኘ ስሜ ክርስቲያን ነው›› በማለት መልሶለታል፡፡

ሹሙ እለ እስክንድሮስ በቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ ብዛት ያላቸውን መከራ አድርሶም ስላልረካ ጭፍሮቹን በብረት ጋን ውስጥ ሰም፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ፣ የዶሮ ማር እና እርሳስ ብረትን በማስጨመር ሊያሠቃያቸው ፈለገ፡፡ ከጋኑ የሚወጣው ድምፅም እንደ ነጎድጓድ የሚሰማና ወላፈኑም እንደ ፀሐይ የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡

ይህ የጋኑ ፍላት ግርማው እጅግ ያስፈራ ነበርና ቅድስት ኢየሉጣ ተሸበረች፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ግን ይህን ፍርሃት ለማራቅ እግዚአብሔር ከእነርሱ በፊት በነበሩት ቅዱሳን በአናንያ፣ በአዛርያ እና በሚሳኤል፣ በሶስና እና በዳንኤል ሕይወት ሥራ ውስጥ የነበረውን የማዳን ችሎታ (ከሃሊነት) እያነሣ ሊያበረታት ሞከረ፡፡ ‹‹እናቴ ሆይ፥ ከሚያልፈው ዓለም ጭንቅና መከራ ለማምለጥ ስትዪ በማያልፈው ዘለዓለማዊ እሳት መቀጣት አይገባሽምና ጽኚ›› አላት፡፡ እንዲሁም ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ ወደ እግዚአብሔር እጅግ ልብን የሚነካ ጸሎት አደረሰ፡፡

‹‹ባርያህ የሆነች እናቴ የሌለችበት ለእኔ ያዘጋጀሃት ርስት ውስጥ ከምገባ ከሕይወት መጽሐፍ ፋቀኝ፤ እርሻውን ልታቃጥል ፍሬውን ልትባርክ፣ ዕንጨቱን ቁረጡና አንድዱት፤ ቅጠሉን ጠብቁት፤ ልትል አይገባም፤ ጠላት ዲያብሎስ የአንተ የሆነውን ቅዱሳኑን ድል ነሳኋቸው ብሎ እንዳይመካና ከመንጋውም አንድ በግ ቀማሁ እንዳይል አቤቱ የኃይል መንፈስ ለእናቴ በመስጠት አበርታት››  በማለት ጸለየ ፡፡ የዚህ ሕፃን ሲሆን በመንግሥተ ሰማያት ለእናቱ አባት የሆነ ቅዱስ ጸሎት ከእግዚአብሔር ደርሶ እናቱን አጽንቶ ጭራሽ የብረት ጋኑን ውኃ በምንጭ ላይ በዝቶ እንደሚወርድ ጠል ሁኖ አሳያት፤ ወዲያውም ሁለቱንም ከብረት ጋን ውስጥ ጨመሯቸው፡፡

እሳቱ ዓርባ ክንድ ወደላይ ተመዝዞ ወጥቷል (ወተለዓለ ነበልባል መጠነ አርብዓ በእመት) ፣ የሁለቱ ቅዱሳን ሰማዕታት አምላክም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ከሰማይ ልኮ በብርሃን በትር ቢመታው እንዳደረ ውርጭ ሆኗል፡፡ የብረት ጋኑም እሳት ጠፍቶ አንዳች ሳይጎዱ ምስክርነታቸውን ፈፀሙ፡፡ በዚህም አስቀድሞ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የዘመረው ቃል ተፈፀመ፡፡ ይህም፡- ‹‹አኅለፍከነ ማዕከለ እሳት ወማይ፤ በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፡፡››  በቀደመ ግብሩ እሳት የነበረ በኋላ ግብሩ ውኃ ሆነ፡፡ (መዝ.፷፭፥፲፪)

ቃሉ የማይታበል ልዑል እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢየ ልዑል ቅዱስ ኢሳይያስ የተናገረውን ቃልም በሁለቱ ቅዱሳን ሰማዕታት ተፈፅሞ አገኘነው፡፡ ‹‹ወእመኒ ዐደውከ ማየ አነ: ሀሎኩ ምስሌከ: ወአፍላግኒ ኢያሰጥሙከ ወእመኒ ዐደውከ እሳተ ነበልባል ኢያውዕየከ፤ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም፡፡›› (ኢሳ.፵፪፥፪)

እኛ እንደነ ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ከእሳት እና ከፈላ ውኃ ውስጥ ጨክኖ በመግባት በእምነት መውጣት የምንችልበት አቅምም ሆነ የጸሎት ኃይል ባይኖረንም በልባችን ጋን ውስጥ እየነደደ ለሀገራችን ኢትዮጵያም የተረፈው በፍቅርና በአንድነት እንዳንኖር ያስቸገረንን ክፉ እሳት አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንዲያጠፋልን መለመን ይገባል፡፡ ለዚህም የአምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት አይለየን!

ምንጭ ፡-

  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • ድርሳነ ቅዱስ ገብርኤል ዘሐምሌ
  • የመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜ
  • መጽሐፈ ስንክሳር
  • መልክአ ሥላሴ