ከአሜሪካ ማእከል
በማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ የዲሲ ንዑስ ማእከል አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ለሰባት ወራት ያስተማራቸውን 64 ተማሪዎችን የተማሪ ወላጆችና የማኅበሩ አመራር አባላት በተገኙበት በሜሪላንድ ግዛት አስመረቀ፡፡
በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የትምህርት ቤቱ አስተባባሪ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የማኅበሩን መልእክትና የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤትን የ፳፻፲ ዓ.ም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም “ከማኅበረ ቅዱሳን ዓላማዎች ልጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት በመማር፣ ለአባቶቹ ተተኪ እንደሆን ማድረግ በመሆኑ ላለፉት ፳፯ ዓመታት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በገቡ ወጣቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፤አሁንም እየሠራ ይገኛል” ብለዋል፡፡
አያይዘውም “ሥራው ብዙ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከሚገኘው ወጣት የተተኪ ትውልድ ቊጥር አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከሕፃናት በመጀመር ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ከ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ጀምሮ ሕፃናትና ወጣቶችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትም ትምህርት ቤት በመክፈት በማኅበሩ የሥርዓተ ትምህርትና የሙያ እገዛ እየተደረገላቸው በማስተማር ላይ ይገኛሉ” በማለት የማኅበሩን አገልግሎት ገልጠዋል፡፡
“በዲሲ ንዑስ ማእከልም ከ፳፻፲ ዓ.ም በመጀመር አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ 64 ተማሪዎችን ተቀብለን በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ለሰባት ወራት በማስተማር ቆይተናል” ብለዋል፡፡ በቋንቋ ክፍል ስድስት በቃል ትምህርት አንድ፣ ሦስት ረዳት፣ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድና አንድ ተጨማሪ በአጠቃላይ 11 መምህራን ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጠዋል፡፡
በምረቃው የተማሪ ወላጆች ማእከሉ ተማሪ የመቀበል አቅሙን ማሳደግ እንዳለበትና ያለውን ልምድ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማካፈል የሚችልበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠቁመዋል፡፡