በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ለማድረግ እና ሰላምና አንድነትን ማምጣት እንዲቻል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምር ለ2000 ዓመታት አንድነቷን፣ ዶግማዋንና ቀኖናዋን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ቢፈራረቁባትም ፈተናዎቹን በመቋቋም፣ እምነቷን በማጽናት፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን በመጠበቅ፣ ተከታዮቿን በመምከርና በማስተማር ሀገርን ሰላም እያደረገች ኖራለች፡፡
ሆኖም በ1984 ዓ.ም. የነበሩት 4ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተወሰኑ አባቶች ጋር ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ለ26 ዓመታት ተከታዮቿ ምእመናን እያዘኑ በከፍተኛ የሰላም እጦት ውስጥ አሳልፏለች
ይህ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ከችግሩ መፈጠር መነሻ ማግስት እና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በአራት የተለያዩ የስብሰባ ጊዜያት ዕርቀ ሰላሙን ለማምጣት ሊቃነ ጳጳሳትን መድቦ አሜሪካ ድረስ በመላክ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት በሚያደርጋቸው ጉባኤያት የሰላሙ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡
ይህ የምእመናን ልጆቻችን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ሰላሙ መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ የ2010 የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የዕርቅ ሰላም ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሟል፡፡
በዚሁ መሠረት ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ሂደት ፍጻሜ የሚያገኝበት በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲሆን በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንድትተጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ መንፈስ እየሄደችበት ያለው የሕዝቡን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል፡፡
ከዚሁ ጋር ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዘቦች ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለው ጅምር ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋጽኦ የምታደርግበት ይሆናል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ በውስጧ የሚገኙ ችግሮቿን ከጥንት ጀምሮ ይዛው በቆየችው ትዕግሥትና የሰላም ሂደት በቀኖናዋ ወሠረት የምትፈታው ሲሆን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን በብቃት የምታከናውንበት አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀምጧል፡፡
በቀጣይ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያናችን ካለፈው በበለጠ ማስፈን እንዲቻል የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ሊፈቃ ያስችላል በሚል በባለሙያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ማዋል እንዲቻል ጥናቶቹ ለ2011 ዓ.ም. የጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
አሁን በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ያለምንም መሰናከል ለውጤት ይበቃ ዘንድ ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አለመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
በዕርቀ ሰላሙ ሂደት በሚደረገው ማንኛውም ውይይት የነበረውንና ቤተ ክርቲያናችን ይዛው የቆየችው ቀኖና በተመለከተ ውይይቱም ሆነ ዕይታው በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ የሚታይ ይሆናል፡፡
አሁን ለተጀመረው የዕርቀ ሰላምና የአንድነት መገኘት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ብፁዓን አባቶች ጉዞአቸው የተቃናና የተሳካ ሆኖ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሁላችንም ተባብረን እንድንሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችንና
ለሕዝባችን ሰላሙን ይስጥልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ