‹‹በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር›› (ዘፀ.፳፥፲፮)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፲፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን! በፈቃደ እግዚአብሔር የጀመርነው ዐቢይ ጾም (ጾመ ክርስቶስ) አምስተኛው ሳምንት ላይ እንገኛለን፤ በአቅማችሁ በመጾም በጸሎት እየበረታችሁ እንደሆነ ተስፋችውን ነው፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ማስቀደስና መንፈሳዊ ትምህርትን ከመማርም መዘንጋት የለብንም!
በእግዚአብሔር ቤት ስናድግ እንባረካለን፤ አምላካችንም ጥበቡንና ማስተዋሉን ያድለናል፤ በጥሩ ሥነ ምግባር አድገን፣ ለራሳችን ለቤተሰቦቻችን እንዲሁም ለአገራችን መልካም የምንሠራም እንሆናለን፡፡ በዘመናዊ ትምህርታችሁም በርትታችሁ መማር ይገባል፡፡ የሁለተኛ መንፈቀ ዓመት እየተገባደደ ነውና በርትታችሁ ትማሩ ዘንድ አጥኑ፤ ያልገባችሁን ጠይቁ፤ አብዛኛውን ጊዜያችሁን በትምህርታችሁ አተኩሩ፡፡ መልካም! በዛሬው ትምህርታችን ሐሰት (ውሸት) በሚል ርእስ እንማራለን፡፡
ሐሰት ማለት “ውሸት፣ አሉታ (ያልሆነ) የእውነት ተቃራኒ፣ ትክክል ያልሆነ፣ ያልነበረውን ፈጥሮ መናገር” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፬፻፷፮) ሐሰት መናገር (መዋሸት) እንደሌለብን ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡ ከዐሥርቱ ትእዛዛት አንዱ ‹‹… በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር…›› የሚል ነው፡፡ (ዘፀ.፳፥፲፮) ሐሰትን መናገር (መዋሸት) ተገቢ አይደለም፡፡ ‹‹ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ…›› (ዘፀ.፳፫፥፩) በምንም ነገር ውሸትን መናገር (ሐሰተኞች) መሆን የለብንም፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሐሰትን መናገር (መዋሸት) ጥሩ አይደለም፤ ከሰዎችም፣ ከእግዚአብሔርም ያርቃል፤ የምንዋሽ ከሆነ ክብርን፣ መወደድን፣ መታመንን እናጣለን፤ ሁል ጊዜ ታማኝ መሆን አለብን፤ አባቶቻችንን እንኳን በብሂላቸው (በምክራቸው) ‹‹እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር..›› ይላሉ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰዎች ለምን ይዋሻሉ? ቢባል ከምክንያቹ አንዱ ያጠፉትን ጥፋት ለመሸፈን (ሌላ ሰው እንዳያውቅባቸው) በማለት ይዋሻሉ፤ ይህ ደግሞ ሌላ ጥፋት ይሆናል፡፡ ስናጠፋ እውነቱን መናር አለብን እንጂ ዋሽተን ሌላ ጥፋት በመሥራት በራሳችን ላይ ችግር ማምጣት አይገባም፡፡ እስኪ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ታሪክ እንመልከት፡፡
ሶስና የምትባል እግዚአብሔርን የምትፈራ ደግ ሴት ነበረች፤ አንድ ቀን ሁለት ሰዎች በውሸት ከሰሷትና እንዲፈረድባት ለምስክር ቆሙ፤ ይገርማችኋል! ሶስና ምንም ጥፋት አልሠራችም፤ ግን ደግሞ ሁለቱ ሰዎች በውሸት ጥፋት ስትሠራ አግኝተናታል ብለው መሰከሩባት፡፡ ከዚያም በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሶስና መቀጣት አለባት ተብሎ ተወሰነ፡፡
በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው ነቢዩ ዳንኤል ለዳኞቹ እንዲህ አለ፤ ‹‹አባቶቼ የተሳሳተ ፍርድ ፈርዳችሁ ንጹሕ ሰው እንዲሞት አታድርጉ፤ ሶስና ላይ የፍርድ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት እነዚህን ምስክሮች የምጠይቃቸው ጥያቄ አለኝ፤ እንዲፈቀድልኝ በአክብሮት እጠይቃው፤›› አለ፡፡ ከዚያም ተፈቀደለትና ሁለቱንም ሰዎች በተራ በተራ ጠየቃቸው፤ አንደኛውን ለብቻው አደረገና ‹‹ወንድሜ ሆይ፥ እውነት ትናገር ዘንድ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ ለመሆኑ ሶስናን ከባሏ ውጪ ከሌላ ሰው ጋር ያየሃት በየትኛው ሥፍራ ነው?›› ሲለው እየተርበተበተ (መናገር እያቃተው) ‹‹እ..እ.እ ከመናፈሻው በስተቀኝ በኩል በኮክ ዛፍ ሥር›› አለ፡፡
ከዚያም ነቢዩ ዳንኤል ‹‹አባቶቼ ሁለተኛውን ሰው እንድጠይቅ እንዲገባልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ›› አለ፤ ሁለተኛውም ሰው ሲመጣ ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ ‹‹ለመሆኑ ሶስናን ከባሏ ውጭ ከሌላ ሰው ጋር ያየኻት በየትኛው ሥፍራ ነው?›› ሁለተኛውም የሚናገረው ጠፍቶት እየተርበተበተ ‹‹እ እ..እ…እ.መናፈሻ ውስጥ በስተግራ በኩል…….በሾላው ዛፍ ሥር›› አለ፤ ሁለቱም የተለያየ ንግግር ተናገሩ፡፡ በዚህም ሐሰተኞች (ውሸታሞች) መሆናቸው ታወቀ፤ ሶስናም በሐሰት ከመከሰስ ዳነች፤ እርነሱ ደግሞ ተቀጡ። (መጽሐፈ ሶስና)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሐሰት ለጊዜው ነው እንጂ የምትሸፈነው አንድ ቀን እውነቱ ሲወጣ ሐሰተኞች (ውሸታሞች) ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፡፡ ከዚህም በኋላ በሰዎችም በእግዚአብሔርም ዘንድ ክብርን አያገኙም፤ ወሸታም ሰው ለጊዜው ቢታመንም እውነቱ ሲታወቅ ግን በሰዎች ዘንድ የነበረውን መወደድ ያጣል፡፡ በምንም ምክንያት በሰዎች ላይ በውሸት መመስከር የለብንም፤ ሐሰትን የሚናር ሰው ሕግን ይተላለፋልና፡፡ ቅጣቱ በመጨረሻ ራሱ ጋር ይመጣል፡፡
ሌላ ታሪክ ደግሞ እንመልከት፡-
የያዕቆብ ልጆች የዮሴፍ ወንድሞች ወንድማቸውን ደብድበው እንደገናም ደግሞ አገልጋይ እንዲሆን ለሌላ አገር ሰዎች ሸጡት፤ ከዚያም ጥፋታቸውን ለመደበቅ ብለው የዮሴፍን ልብስ በፍየል ደም ነክረው (ቀብተው) ወደ ቤት ሄደው ለአባታቸው ለያዕቆብ ‹‹ይህንን ቀሚስ መንገድ ላይ ነው ያገኘነው የልጅህ ቀሚስ መሆኑን እይ›› አሉት፡፡ ያዕቆብም ሲመለከተው የልጁ የዮሴፍ ቀሚስ ነው፤ ‹‹ልጄን አውሬ በልቶት ይሆናል›› ብሎ አለቀሰ፤ በጣም አዘነ፤ ዓይኖቹ ማየት እስኪሳናቸው ድረስ አለቀሰ፡፡ ዮሴፍ ግን አልሞተም ነበር፤ ልጆቹ ጥፋታቸውን ለመሸፈን ብለው አባታቸውን ዋሹት፤ በዚህም ኀዘኑን አበዙበት ለዓይኑ መጥፋት ምክንያት ሆኑ፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት ፴፯፥፳፱)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሐሰት ራስን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብንም ይጎዳል፤ በፍጹም ውሸት መናገር የለብንም፤ የዮሴፍ ወንድሞች በመዋሸታቸው የአባታቸውን ዓይን እንዲጠፋ አደረጉ፤ ጥፋትን ላለመሥራት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ ምን አልባት ከተሳሳትን (ካጠፋን) እንኳን በመደበቅ ሌላ ጥፋት ከመሥራት እውነቱን መናገርና ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አያችሁ አይደል! መዋሸት ምን ያህል ነጻነትን እንደሚያሳጣ! ሐሰተኛም ሰው በራሱ ነጻነት የለውም፤ ሰላምም የለውም፤ ጥፋቴ ይታወቅብኝ ይሆን? እያለ ሲጨነቅ ይኖራል፤ ስለዚህ በምንም ምክንያት መዋሸት ጥፋታችንን መደበቅ የለብንም፤ ለወላጆቻችንን (ለቤተሰብ) ማማከር አለብን፤ ያን ጊዜ ለጥፋታችን (ለችግራችን) መፍትሔ እናገኛለን፡፡
ዘወትር እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ፤ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!