በቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ላይ ያተኮረ መድረክ ሊዘጋጅ ነው፡፡
መጋቢት 17/2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደጀኔ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር አዘጋጅነት መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ላይ ያተኮረ የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል እንዳስታወቀው በዚህ የጥናት ጉባኤ የቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ክፍል የሆነው የምዕራፍ ሚናና፣ አጠቃቀም በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ጥናቱን የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርትና የመምህራን ሙያ ልማት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ውቤ ካሣዬ ሲሆኑ ጥናቱን በመምራትና በማወያየት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ መምህር በዶ/ር ሥርግው ገላው እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመርሐ ግብሩም በዘመናችን እየታየ ባለው የዜማ ችግር ላይ መፍትሔ ጠቋሚ የሚሆኑ ሀሳቦች በማንሣት፣ የሚታዩትን ችግሮች የችግሮቹንም ምንነት በመለየት ለዜማችን መሠረታዊ ችግር የሆኑትን በመፈተሽ፣ በመፍትሔው ላይ የጋራ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ከጥናትና ምርምር ማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
በጉባኤው ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆችና፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ዘማርያንና ሰባኪያን እንዲሁም ከሙያው ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚካሔድ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ምእመናን እንዲገኙ የምርምር ማእከሉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡