በሽተኛው ተፈወሰ!
መጋቢት ፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ሕመም፣ በሽታና ክፉ ደዌ በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎች ናቸው፡፡ የሰው ዘር በሙሉ ከአዳም ጥፋት በኋላ ይህ ቅጣት እንደመጣበት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ አዳምና ሔዋን አትብሉ ተብሎ የነበረውን ዕፀ በለስ ከበሉ በኋላ ከደረሰባቸው መርገምት መካከል በሕመምና ሥቃይ እንዲቀጡ ነው፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፮-፲፱)
በሥነ ፍጥረት ታሪክ ውስጥ እንደተገለጸውም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሰዎች በተለያዩ በሽታዎችና ሕመሞች ሲሠቃዩ ኖረዋል፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ያለፉ በርካታ አባቶችና እናቶች በአንድም በሌላ በበሽታ ይቀጣሉ፤ ይሠቃያሉ፡፡ አንዳንዶች ፈውስና መፍትሔ ሲያገኙ ‹‹በሽታንም ከአንተ አርቃለሁ›› እንዲል፣ ሌሎች ግን በአልጋ ቁራኛ ተይዘው፣ ማቅቀው፣ አስታማሚ፣ አጉራሽ አልባሽ አጥተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ( ዘጸ.፳፫፥፳፭)
በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የምናገኘው አንድ ታሪክ እዚህ ላይ እናንሣ፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል (፭፥፪-፱) መፃጉዕ የተባለ አንድ በሽተኛ ለሠላሳ ስምንት ዓመት በደዌ ተይዞ በአልጋ ቁራኝነት የኖረ ሰው በአምላካችን ድንቅ ተአምር እንዴት ፈውስ እንዳገኘ ይተርካል፡፡ የዐቢይ ጾም አራተኛው ሳምንትም ይህን ታሪክ በማውሳት “መፃጉዕ” ተብሎ ይጠራል፡፡
ጌታችንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ በበጎች በር አጠገብ በነበረች መጠመቂያ ቦታ ስሟም በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ቤተ ሳይዳ›› ወደ ምትባል ቦታ ደርሶ በዚያ ያሉ ዕውራኖችና አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ሲጠባበቁ አገኛቸው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ፥ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ይፈወስ ነበርና፡፡
በመካከላቸውም ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ እንኳን ጠፍቶ በበሽታው ስም “መፃጉዕ” የተባለውን ሰው ጌታችን ተመከተውና ወደ እርሱም ቀርቦ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ በሽተኛውን ጠየቀው፡፡ መጠየቁ ሰውየው መዳን እንደሚፈልግ ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን ‹‹በዕለተ ዓርብ ፈውሰኝ ሳልል ፈውሶኛል›› ብሎ የሚመሰክርበት ነውና አስፈቅዶ ለማዳን ጠየቀው፡፡ አንድም በድኅነት ውስጥ ሰው የራሱ ሱታፌ እንዳለው ለማስተማር ነው፡፡
ድውዩም ‹‹ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› ብሎ መለሰለት። ቸሩ አምላካችንም ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው። መፃዕጉም ጉልበቱ ጸንቶ ተነሣ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ፈሪሳውያን ግን ‹‹በሰንበት አልጋህን ተሸክመህ መሄድ እትችልም፤ ፈውስም በሰንበት መሆን የለበትም›› ብለው ተቆጡ፡፡ (ዮሐ.፭፥ ፩-፱)
አይሁድም ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሠውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና፥ ‹‹እነሆ፥ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ›› አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ ‹‹አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ›› አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ‹‹ሰንበትን የሚሽር ነው፤›› እግዚአብሔርን ‹‹አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል›› በማለት ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፡፡
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡›› (ዮሐ.፭፥ ፩-፳፬)
ለምድራዊም ይሁን ለዘለዓለማዊው ሕይወታችን መገኘት፣ ድኅነትም ሆነ ፈውስ የሚገኘው በእግዚአብሔር አምላካችን ስናምንና ለእርሱ ስንታመን እንደሆነ ማወቅ ይገባል፡፡ መፃጉዕ ለጊዜው የተጠየቀው ነገር ከያዘው ደዌ እንዲድን ቢመስልም ጌታችን ግን የነፍሱንም ድኅነት ጠይቆታል፡፡ ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ የጠየቀው ስለ እምነቱ ነበር፡፡ ከበሽታው ለመፈወስም እንኳን ቢሆን እምነት ከሌለ ሊድን እንደማይችል በቃሉ አስረድቶታል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የነፍሱንም ነገር እንዲያስብ አሳስቦታል፡፡
መፃጉዕ ግን ከተፈወሰ በኋላ መካዱን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ያዳነውን ሲጠየቅ እንኳን አለማወቁን ተናግሯል። (ዮሐ.፭፥፲፫) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደስ ሳለ ያን ያዳነውን ሰው አግኝቶ ከዚህ የከፋ ‹‹ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ እንዳያገኝህ ሁለተኛ እንዳትበድል›› ያለውን ዘንግቶ ደዌ ኃጢአትን ሠራ፤(ቁ.፲፬) በዕለተ ዓርብም የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ `ሰላ` ቀርታለች።
ተወዳጆች ሆይ! በማኝኛውንም ዓይነት በሽታና ሕመም ስንሠቃይ ፈውስን መሻታችንና መመኘታችን አይቀሬ ነው፡፡ አያድርስና ግን አንዳንድ ጊዜ የዚህ ዓለም ጠበብቶች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች ማዳንም መፈውስ የማይችሉት በሽታ ይይዘን ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ልናስብ የምንችለው አንድም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ በጸበል፣ በቅብዐ ቅዱስ ወይም በእምነት ተቀብቶ መዳን ካልሆነ ግን ሞትን መጠበቅ ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ በፊት ግን እኛ ሰዎች በፈጣሪያችን፣ በአምላካችን፣ በመድኃኒታችን አምነን ዘወትር በእርሱ ቸርነት ጥላ ሥር ብንኖር እንዲህ ያለው ሥቃይ ሲገጥመን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በእምነት ጸንተን ፈውሰ ሥጋንና ፈውሰ ነፍስን ልንናገኝ እንችላለን፡፡
የማይካድ እውነት ስለመሆኑ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናትና ገዳማት በጸበል የዳኑ አማኞች በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎች መድኃኒት አይገኝላቸውም ከተባሉ በሽታዎች እንደ ኤች፣ አይ፣ ቪ ካሉ ወረርሽኞች እንደዳኑ ሰምተናል፤ አይተናልም፡፡ አስከፊና አሰቃቂ ከሆነውና በቀላሉ በትንፋሽ ተላለፊና ገዳይ በሽታ “ኮኖና” እንኳን ሰዎች በጸበል እንደዳኑ መስማታችን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
በእምነት ጸንተን ልንኖር እንደሚገባ እዚህ ላይ እንረዳለን፡፡ አለበለዚያ ግን ፈውሰ ሥጋን ካገኘን፣ ከሕመማችን ከተፈወስንና ከሥቃያችን ከተላቀቅን በኋላ እንደ መፃጉዕ መልሰን አምላካችንን መርሳት አልያም መካድ ይሆናልና በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በእምነት ጸንተን እንኑር!
አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ጸሎታችንን፣ ጾማችንና ንስሐችንን ይቀበለን፤ አሜን!