በስልጤና ሀድያ፣ ጉራጌ፣ ከንባታ ሀገረ ስብከት በፖሊሶች የፈረሰው የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በአክራሪ ሙስሊሞች ፍርስራሹ ተቃጠለ፡፡

ኅዳር 21/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባዬ

፠በቃጠሎው ወንጀል የስልጤ ቲትጎራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የስልጢ 2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ተሳትፍበውታል፡፡
፠የስልጢ አረጋውያን ሙስሊሞች ድርጊቱን ተቃውመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስልጤና ሀድያ፣ ጉራጌ፣ ከንባታ ሀገረ ስብከት በስልጤ ደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያምና ቆቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስር የተመሠረተው የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም ረፋድ ላይ በአክራሪ ሙስሊሞች ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን ለመረዳት ተችሏል፡፡

DSC01450

የቤተ ክርስቲያኑ መቃጠል እንደተሰማ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና የማኅበረ ቅዱሳን ልዑካን በቦታው ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ወደ ስልጢ ከመሔዳቸው በፊት በቡታጅራ ከተማ ተገኝተው በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የማጽናኛ መልእክት በማስተላለፍ የቡታ ጅራ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲረጋጋ አድርገዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ለምንና እንዴት እንደተቃጠለ ለማጣራት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የጸጥታ አስተዳዳር ምክትል ሓላፊ አቶ ኢዮብ አንበሳ፣ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ፋሲል ጌታቸውና የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ የሥራ ሒደት ሓላፊ አቶ በረከት ጌኤ  ተገኝተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ እንዲቃጠል ከፍተኛውን ድርሻ ወስደው ተማሪዎችን ሲቀሰቅሱ የነበሩ በስም የሚታወቁ ግለሰቦችና አክራሪ ሙስሊሞች እንደሆኑ ተገንዝበናል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት ወንጀሉ እንዳይፈጸም የቅድሚያ ዝግጅት ለምን እንዳላደረገ ለቀረበለት ጥያቄ እንደ መንግሥት አስተዳደር በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ስለሌለብን ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እስከ የት እንደሆነ በግልጽ ማብራራት ያልቻሉት የስልጤ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሐያቱ ሙክታር “የተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን አይደለም” የሚል ማስተባበያ ለመስጠት መሞከራቸውን አረጋግጠናል፡፡ ሆኖም የተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን ለመሆኑ የፎቶግራፍ ማስረጃ ለክልሉ ባለስልጣናት ሊቀ ጳጳሱ አቅርበዋል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ተከባብረው፣ ተፈቃቅረው ለሰላም       ለልማትና ለእድገት በሚተጉበት በዚህ ወቅት መንግሥት ባለበት ከተማ እንዲህ ያለ ወንጀል መፈጸሙ ያሳዘናቸው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ወንጀሉን የፈጸሙ አካላትን ጉዳይ ለፍርድ የማቅረቡን ሒደት ከሚመለከታቸው የበላይ የመንግሥት አካላት ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ወጥተው ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል ያነሣሣቸውን አካል በሕግ መጠየቅ እንዳለበት ያብራሩት የክልሉ የጸጥታ አስተዳዳሪም የሕዝበ ክርስቲያኑን ትእግሥት አድንቀዋል፡፡

ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም አመሻሽ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የስልጢ ከተማ ምእመናንና የክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ የምእመናን ተወካዮች ተመርጠው ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት ጋር ወንጀለኞችን ለማጋለጥ የማጣራቱ ሒደት ቀጥሏል፡፡

ዛሬ በደረሰን መረጃ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በምእመናን የተመረጡ ከ25 እስከ 30 የሚሆኑ ሽማግሌዎች ሥራቸውን እንዳይጀምሩ እየተደረገ ነው፡፡ በተለይ ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ የደብረ ስብሐት ቅድስት ማርያምና ቆቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለጥምቀተ ባሕር የሚጠቀሙበት ቦታ ለሌላ አገልግሎት መዋል የለበትም የሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩ ካህናት በኮሚቴ ውስጥ ቢመረጡም ሥራቸውን መቀጠል አልቻሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳዩን በደንብ የማያውቁት ሰዎች እንዲተኩ መደረጋቸው የችግሩን መንስኤና ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማግኘት አጠራጣሪ እንደሆነ የአካባቢው ምእመናን ጠቁመዋል፡፡

 

ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኑን መፍረስ የዘገብን መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቃጠሎውን ተግባር የፈጸሙት በእድሜ ያልበሰሉ ሕፃናት ናቸው ተብሎ ወንጀሉ እንዲዳፈን መደረጉ እንዳሳዘናቸው የስልጢ ምእመናን እያሳሰቡ ነው፡፡