በማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረቡ
ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
በጸሎተ ሃይማኖት *ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ* የሚለው ንባብ *በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ* ተብሎ መስተካከል አለበት ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕቃ ቤትና በቅዱሳት መካናት አማካኝነት የቅርስ ቤተ መዛግብት እንደሆነች ተገልጿል፡፡
ወጣቱ ትውልድ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተነግሯል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል አዘጋጅነት *የአርዮስና መንፈቀ አርዮሳውያን ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ላይ* እና *የቤተ ክርስቲያን ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የመጠበቅ ሒደት በአድባራትና ገዳማት* በሚሉ ዐበይት አርእስት የሚመለከታቸው ምሁራንና ተሳታፊ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሜ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡
*የአርዮስና መንፈቀ አርዮሳውያን ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ላይ* በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ሲሆኑ በጥናታቸውም የአርዮስ የኑፋቄ ትምህርት የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት የሚቃወም መሆኑን ጠቅሰው አርዮስና ኑፋቄዉ በ፫፻፲፰ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በ፫፳፭ ዓ.ም በኒቅያ በተደረገው ጉባኤ ቢወገዝም ትምህርቱ ግን እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እየተፈታተናት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም በጉባኤ ኒቅያ በተወሰነው የሃይማኖት መሠረት (ጸሎተ ሃይማኖት) ውስጥ *ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ* የሚለው የግእዝ ንባብ *በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል* ተብሎ መተርጐሙ ትክክል አለመሆኑን መረጃ በማስደገፍ ገልጸው ይህ ሐረግ *በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ* ተብሎ መስተካከል እንዳለበትና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህንን ምሥጢር ለምእመናን ማስረዳት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
*የቤተ ክርስቲያን ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የመጠበቅ ሒደት በአድባራትና ገዳማት* በሚለው ርእስ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዲያቆን አለባቸው በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕቃ ቤትና በቅዱሳት መካናት አማካኝነት በቅርስ ቤተ መዛግብትነት የምትገኝ መሆኗን ጠቅሰው ወጥ የሆነ መመሪያና ዕቅድ አለመኖር፣ የቅርስ አጠባበቅና ክብካቤ ችግር፣ ወዘተ የመሰሉ ተግዳሮቶች እንዳሉባት በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡
በጥናታቸው ማጠቃለያም ቤተ ክርስቲያናችን የእምቅ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ገልጸው የዕቅድና ወጥ መመሪያ ዝግጅት፣ የአስተዳደርና የዓቅም ግንባታ ሥራ፣ ለምእመናን ስለቅርሶች ግንዛቤ መስጠትና የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርባቸው ማድረግ፣ ወዘተ የመሰሉ ተግባራት ለቅርስ አጠባበቅ ችግር መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዝርዝር አስረድተው *ሁላችንም ይህንን በመረዳትና የተጀመሩ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለወደፊት የተሻለ መሥራት ይጠበቅብናል* ብለዋል፡፡
በዐውደ ጥናቱ ላይ ከተገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ የሆኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን አስተያየት በሰጡበት ወቅት፣ *ትልቁ ነገር የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች መመለስ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን መምህራንን በመጋበዝ እንደዚህ ዓይነት ጥናታዊ ውይይት ማካሔዱ ለአባቶች ተገዢ መሆኑን አመላካች ተግባር ነው* ብለዋል፡፡ በተጨማሪም *ቤተ ክርስቲያናችን፣ Living Church of Living Faith and Ever Growing Church – ዘለዓለማዊት፣ የዘለዓለማዊው ሃይማኖት መሪ የሆነች እና ዘለዓለም የምታድግ ናት፤ ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት* ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም በሁለቱም ጥናቶች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሡ ጥያቄዎች በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶ ሲያበቃ የውይይቱ መሪ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የማጠቃለያ ንግግር ካደረጉ በኋላ በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡