በመንግሥትህ አስበኝ!
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
መጋቢት ፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
በሚያስፈራ ግርማህ በምጽዓት ቀን ስትገለጥ
በፊትህ የሚቆም ጠፍቶ ዓለም ሁሉ ሲንቀጠቀጥ
መልካሙን ዘር ከክፉው አበጥረህ ስትለያቸው
በፍርሃት ያርዳል የጽድቅ ፍሬ ለሌላቸው
ለእኔም ጨንቆኛል ዳግም የምትመጣበት
በደሌ ተቆጥሮ በሥራዬ የምመዘንበት
በሥራዬ ሚዛን መልካም ፍሬ ባይኖረኝም
በምጽዓትህ ጊዜ አስበኝ እንዳልሰጥም
እኔን እኔን እንዳያጠፋኝ
አምላኬ ሆይ የት ነሽ በለኝ
በቸርነትህ ብዛት በመንግሥትህ አስበኝ
ኅሊናዬ ባዶ ሆኖ ጥርሴ ብቻ ይስቃል
ልቦናዬ ታውሮ ዓይኔም ሳያይ ያፈ’ጣል
አንደበቴም ዲዳ ሆነ ስምህን የማይቀድስ
ጆሮዬም የማይሰማ ስትጠራው የማይመልስ
እግሮቼም ከደጃፍህ ከመቅደስህ ራቁ
በድን አካሌን ተሸክመው በዓለም ተድላ ተነጠቁ
ሁሉን ቻይ መድኃኒቴ ሥጋዬን ገሥጽልኝ
በምጽዓትህ ቀን ከሙታን ጋር እንዳልገኝ
እኔን እኔን እንዳያጠፋኝ
አምላኬ ሆይ የት ነሽ በለኝ
በምሕረትህ መጠን በመንግሥትህ አስበኝ
ከክፋት ጋር ተዳብዬ በአንድ ጎጆ እኖራለሁ
ሥጋዬን ከነፍሴ እያጣላሁ ቤቴ ሰላም አጥቻለሁ
ከሞት ጋራ እየዋልኩ በጠላት ሠፈር ከትሜ
ደህና ነኝ ይመስለኛል እየሞትኩኝ በቁሜ
የኀዘን ሆኗል ቤቴ ነፍሴ የሞተችበት
መንፈሴን እያስጨነቀ ሥጋዬ የሚስቅበት
አምላኬ ሆይ ተመልከተኝ የረከሰ ማንነቴን ቀድሰው
የጎደለ እምነቴን በይቅርታህ ሙላው
የሰላም አምላክ ሆይ ሰላምህን አድለኝ
በምጽዓትህ ቀን አመፄ ለሞት እንዳይሰጠኝ
እኔን እኔን እንዳያጠፋኝ
አምላኬ ሆይ የት ነሽ በለኝ
በሩኅሩኅነትህ ብዛት በመንግሥትህ አስበኝ
በኃጢአት በረኃ የጽድቅ ውኃ በሌለበት
በሥራዬ ተቃጥዬ በምድረ በዳ ስንከራተት
የሀሜቴ ብዛቱ አንደበቴን አድርቆታል
የክፋት ሐሳብ ሙቀቱ ራስ ቅሌን አክስሎታል
በበረኃው አንበጣ በዲያብሎስ ተነድፌ
ሕይወትን ዛሬ ቀበርኳት ሞትን ለነገ አትርፌ
የበደሌ ሀሩሩ መላ እኔነቴን ሲያነደኝ
ፍቅህ ደመና ሆኖኝ በእቅፍህ ጥላ አሳርፈኝ
በለመለመ መስክ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳድረኝ
በምጽዓትህ ቀን ጠቁሬ በግራህ በኩል እንዳልገኝ
እኔን እኔን እንዳያጠፋኝ
አምላኬ ሆይ የት ነሽ በለኝ
በለጋስነትህ መጠን በመንግሥትህ አስበኝ
ቀኔ ብርሃን የለውም ሌሊቴም እጅግ ጠቁሯል
ዓመቴም ጸደይ አያውቅም በጭጋግ ተደብቋል
የጠወለገ ሕይወቴ የኃጢአት አረም የበዛበት
ከጸደይ ጋር የማያብብ የጽድቅ ፍሬ የሌለበት
የእውነት ፀሐይ ጠልቃ ሐሰት ከነገሠበት
ከጨለማ ሕይወት አውጣኝ ብርሃንህ ወዳለበት
በዘመኔ ብርሃንህ ለእግሮቼ መሪ ይሁንልኝ
በምጽዓትህ ቀን መንገዴ ወደ ሲኦል እንዳይወስደኝ
እኔን እኔን እንዳያጠፋኝ
አምላኬ ሆይ የት ነሽ በለኝ
በአምላክነትህ ሥልጣን በመንግሥትህ አስበኝ
ወየው እኔስ በደሌ ወየው እኔስ ኃጢአቴ
መግቢያዬ ወደ የት ይሆን ከሞት በኋላ ቤቴ
አድፌያለሁ በበደል ቆሽሻለሁ በኃጢአት
ምሕረትህ ትታደገኝ ከዘለዓለማዊ እሳት
ከበለስ ብጎርስም ትእዛዝህን ችላ ብዬ
ከኃጢአት ጉያ ፈልገኝ አትተወኝ ፈጣሪዬ
ርቃኔን ብሆንም የፍቅር ሸማህን ጥዬ
ልጄ ሆይ የት ነሽ በለኝ አትተወኝ ጌታዬ
አዳምን የፈለግከው እኔንም የት ነሽ በለኝ
በምጽዓትህ ስትመጣ በመንግሥትህ አስበኝ
በምጽዓትህ ስትመጣ ከቅዱሳን ጋር ደምረኝ።