በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ ራሳቸውን “ጉባኤ አርድዕት” ብለው የሰየሙ ቡድኖች እየተፈጠሩ መሆናቸው ተገለፀ፡፡

ሰኔ 09 ቀን 2004 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባለፉት ረጅም ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን አልፋ የተጓዘች መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተለይም ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሰየሙ ቡድኖች ተመሳስለው ውስጧ በመግባት ውስጥ ለውስጥ ሲያደሟት ቆይተዋል፡፡

የእነዚህ ድብቅ ቡድኖች አካሄድ ለብዙ ጠንካራ ኦርቶዶክሳውያን ግልፅ የነበረ በመሆኑ ላለፉት ተከታታይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት ማንነታቸው ተገልጾ ውግዘት የተላለፈባቸውና በሕግ የሚጠየቁትም በሕግ እንዲጠየቁ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተገልጾ ለምዕመናን እንዲደርስ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት በ25 አባላት መሰራችነት የሚመራ አዲስ ቡድን በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡

የቡድኑ ዋና አላማ ነው ተብሎ ከተገለፀው መካከል የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሥራ ላይ እንዳይውል የሚያደርጉትን ጥፋት መደገፍና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትን ከማስፈራራት ጀምሮ ማንኛውንም ጫና በማድረግ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡

የጉባኤ አርድዕት መሪዎችና መስራቾች “ማኅበር ለቤተ ክርስቲያን አያስፈልግም” ብለው ሲሟገቱ የነበሩ ሲሆን ለእነርሱ እስከጠቀማቸው ድረስ “ጉባኤ አርድዕት” ወደ “ማኅበረ አርድዕት” ለመቀየር ሀሳብ ያላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡