በሐዋሳ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ሰባኪያነ ወንጌል ተመረቁ

ነሐሴ 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

በዲ/ን ያለው ታምራት ከሐዋሳ ማእከል

awa mer 2006 1በማኅበረ ቅዳሳን ሐዋሳ ማዕከል በተለያዩ አምስት ቋንቋዎች የሚያስተምሩ 33  ሰባኪያነ ወንጌል በሐዋሳ ካህናት ማሠልጠኛ ለአንድ ወር በቀንና በማታ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እና ሥልጠናዎችን ሲከታተሉ ቆይተው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል  የሲዳማ፣ የጌዲኦ፣ የአማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት  ሐምሌ 27 ቀን 2006 ዓ.ም በሐዋሳ ደብረ ምጥማቅ  መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በድምቀት አስመረቀ፡፡

awa mer 2006 2ተመራቂ ሰልጣኞቹ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ባልተስፋፋባቸው የገጠር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከሲዳማ፣ ከጌዲኦ፣ ከአማሮና ከቡርጂ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ ሲሆን፤ በሲዳምኛ፤ በጌዲኦኛ፤በኩየርኛ፤በቡርጂኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በአንድ ወር ቆይታቸውም ከሚሰጣቸው መንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ በስብከት ዘዴ ላይ ያተኮረ የልምምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ለተመራቂዎቹ የምስክር ወረቀት፤ ለአገልግሎት የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ እና ማጣቀሻ መጸሕፍትን ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት “ከአማርኛ እና ግዕዝ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስተማር ግዴታችን ነው፤ ሥልጠናውም ወደፊት ተጠናክሮ በመቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡

 

በዕለቱ ተመራቂ ሠልጣኞች በደብረ ምጥማቅ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ለተገኘኙ ምእመናን በቋንቋቸው በማስተማር ያገለገሉ ሲሆን፤ ምዕመናንም ይህን ላደረገ እግዚአብሔር በእልልታ እና በጭብጨባ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

የሐዋሳ ማእከል ሰብሳቢ ቀሲስ ደረጀ ሚደቅሶ በበኩላቸው ማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማእከል በተከታታይ ለስድስት ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ያሰለጠናቸው ሰባኪያነ ወንጌል ቁጥር 274 ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ ሠልጣኞችም ወደ መጡበት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ተመልሰው ምእመናን በሚገባቸው ቋንቋ እያስተማሩ በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፤ ወደ ሌላ እምነት የተቀየሩትንም አስተምረው ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው እንዲመልሱ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ከሀገረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ በተጨማሪ የሀገረ ሰብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የደብር አለቆች፣ ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡