የተወደዳችሁ የሐዊረ ሕይወት አዘጋጆች ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነች አምናለሁ፡፡ እናም ሁለት በአእምሮየ የሚመላለሱ ጥያቄዎች አሉኝ፡፡
የመጀመሪያው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድን ለሐዋርያት በሚያስተምርበት ወቅት ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ ይህስ አይሁንብህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ጌታችን አንተ ሰይጣን ከዚህ ሂድ ብሎ በጴጥሮስ ላይ አድሮ የክርስቶስን የማዳን ሥራ የተቃወመውን ዲያብሎስን ተቃውሞታል፡፡ እኔ እንደገባኝ ከሆነ የቅዱስ ጴጥሮስ ሀዘኔታ ተገቢ እንዳልነበ ነው በጌታችን የማዳን መንገድ ልንደሰት ይገባል እንጅ በስቅለት ወቅትና በሌሎችም ጊዜያት ስለ ጌታችን ስቅለት የሚደረገው የሐዘን ስሜት ከክርስትና አስተምሮ አንጻር ተገቢ ነው ወይ?
ሁለተኛው ጥያቄ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ስለነበረው ስለአስቆሮቱ ይሁዳ ነው፡፡ እንደምናውቀው ይሁዳ አባቱን እንደሚገድል፣ እናቱን እንደሚያገባና መምህሩን እንደሚሸጥ አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረና የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ እንደተፈጸሙ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ የማዳን መንገድ በፍርድ አደባባይ ለመቆም ይሁዳ እንደምክንያት ባይሆን ኖሮ የጌታችን የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ በምን ዓይነት መንገድ ይፈጸም ነበር? እንደተማርኩት ከሆነ ጌታችን በባህርይው አስገዳጅ ስለሌለው የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ የፈጸመው በፈቃዱ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ይሁዳና ሌሎች በስቅለቱ ላይ የተባበሩት አይሁዳውያን ጥፋታቸው ምኑ ላይ ነው?
እባካችሁ ምስጢሩን እንዲገልጽልኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡
ምኅርካ ድንግል
ከአዲስ አበባ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ፡፡
በመጀመሪያ ይህንን አድራሻ ያገኘሁት ለጉዞ ካዘጋጃችሁት ትኬት ላይ ነው ፡፡ በወቅቱ በጐዞው ላይ ለመሳተፍ ባለመቻሌ ጥያቄዬን ማቅረብ አልቻልኩም እናም ከተቻለ ለዚህ አወዛጋቢ ለሆነብኝ ጥያቄ መልስ እንደምትሰጡኝ ተስፋ በማድረግ ጥያቄዬን አቅርቤያለሁ፡፡
ጥያቄ አንድ ፡ በዕድሜ የሚበላለጡ ጥንዶች ለትዳር መተጫጨት ይችላሉ?
ጥያቄ ሁለት ፡ የሚችሉ ከሆነ የዕድሜው ልዩነት ከ _ እስከ ይኖረዋል?
ጥያቄ ሦስት ፡ በአብዛኛው የተለመደው ወንዱ ከሴቷ በዕድሜ የበለጠ ነው፡፡ እኔን ደግሞ ያጋጠመኝ ሴቷ (እኔ) ከወንዱ በ 5 ዓመት የምበልጠው ሲሆን የፍቅር ጥያቄውን በዚህ
ምክንያት ለመመለስ አልቻልኩም ፡፡ እግዚአብሔር ሄዋንን ከአዳም ጐን ሲያበጃት (ሲፈጥራት) ቀድሞ አዳም ተፈጥሮ ነበርና በእኔ መረዳት ግማሽ አካሌ ነው ለማለት ከእኔ በፊት መፈጠር አለበት የሚል ግንዛቤ ስለወሰድኩ ነው፡፡
ጥያቄ አራት ፡ ድንግልናውን/ዋን የጠበቀ/ች ድንግልናውን/ዋን ካልጠበቀ/ች ጋር ትዳር መመስረት ይችላሉ? ከቻሉስ የተክሊል ስርአት ሊፈጸምላቸው ይችላል?
ስለምትሰጡኝ ትክክለኛ ምላሽ ከወዲሁ በእግዚአብሔር ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችንም አስተዋይ ልቦናን ይስጠን አሜን ፡፡
ዘፈን ስለ መዋደድ፣ መተሳሰብ፣ ሀገር ፍቅር ከሆነ ችግር የለውም ይባላል፤ እንዴት ነው? ባጠቃላይ ዘፈን በቤተ ክርስቲያን እንዴት ይገለጻል?
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ፡፡
1. አስራትና በኩራት መስጠት የሚቻለው ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው ወይስ ለተቸገሩ የትኛውም ገዳማት እና አድባራት መስጠት ይቻላል?
2. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግርን አነባብሮ መቀመጥ አይቻልም የሚባለው ከአክብሮት አንጻር ብቻ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
3. አንድ ወንድ ህልመ ሌሊት ከታየው በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ የሚችለው መቼ ነው (መቅደስ ገብቶ ማስቀደስ የሚችለው)?
በሰላም ለጉዞው አድርሶን የበረከቱ ተካፋይ ያድርገን አሜን!!