ቋሚ ሲኖዶስ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ
በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
‹‹ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ፤ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ፤ ፈልጉ፡፡ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና›› ኤርምያስ ም.29 ቁ.7
ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች በተፈጠረ ችግር ደርሶ በነበረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም በወቅቱ በሞቱት ወገኖቻችን ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን ሐዘኗን መግለጿ ጸሎተ ምሕላ ማወጇ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ዓመታዊውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ከተሰበሰቡት መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሕይወታቸው ስለጠፋ ወገኖቻችን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡ ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአኀ ይከውን ሰላምክሙ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ ፈልጉ፤ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና፡፡ እንዳለው ሰላም ስንል የሰላም መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ በስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ ሰዎች ሲገናኙ ጭምር የሚለዋወጡት የሰላምታ ቃል የሰላም ውጤት መሆኑ ሁሉም የሚገነዘበው ነው፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!
አገራችን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር ተብላ ከመጠራቷም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር የሚታይባት በተፈጥሮ ፀጋዎች እጅግ የታደለች እኛም በኢትዮጵያዊነታችንና በአንድነታችን የምንኮራባት አገር ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ በተለይም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ በታሪክም የምንታወቅበትና ለሁሉም ዓለም ልዩ ሁነን የምንታይበት መለያችን አንድነታችንና መተሳሰባችን፣ ሌላውን እንደራሳችን አድርገን መውደዳችን፣ ያለንን ተካፍለን መኖራችን፣ ቤት የእግዚአብሔር ነው ብለን አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ማስተናገዳችን ፍጹም የኢትዮጵያዊነት መለያችን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት አለመግባባት እየተፈጠረ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ በአገር ሀብት ላይ ውድመት መድረሱ፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ እየተስተጓጐሉ መምጣታቸው፣ በተለይም በቢሾፍቱ ከተማ ይከበር በነበረ ዓመታዊ የእሬቻ በዓል ላይ በተከሰተ ግጭት ለበዓሉ ተሰብስበው ከነበሩት ውስጥ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በመገናኛ ብዙኃን ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያናችንና ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡
በመሆኑም ይህ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሕልፈተ ሕይወት መላውን የአገሪቱን ዜጎች አሳዝኗል፡፡ በቀጣይም በመሪዎችም ሆነ በሕዝቦች ዘንድ ፍፁም የእግዚአብሔር ሰላም ካልሰፈነ ውሎ መግባትም ሆነ አድሮ መነሳት ሥጋት ከመሆኑም በላይ ይህች በታሪኳ ሰላሟና አንድነቷ የተመሰከረላት ቅድስት አገራችን ስሟ እንዳይለወጥ ሁላችንም የመጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን፡፡ በግል ሠርቶ ለመበልፀግም ሆነ ለአገር መልካም ሥራ መሥራት የሚቻለው በአገር ፍቅርና ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ያለ ሰላም ሰው እግዚአብሔርን ቀርቶ ወንድም ወንድሙን ማየት አይችልም፡፡ በመሆኑም የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለሕዝባችንና ለአገራችን ሰላም እንዲሰጥልን በነቢዩ እንደተነገረው ሁላችንም ሰላምን ልንሻ ስለ ሰላምም አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!
ይህንኑ የወገኖቻችንን ሕልፈተ ሕይወት መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ ሐዘን የተሰማት በመሆኑ ቋሚ ሲኖዶስ በደረሰው አሳዛኝ ድርጊት ተወያይቶ የሚከተለውን ወስኖአል፡፡
- ከመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ እና በውጭው አገር በሚገኙ አህጉረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሕይወታቸው ለጠፋውና ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ወገኖቻችን እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጥልን ለሰባት ቀናት በጸሎት እንዲታሰቡ ቋሚ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
- ከዚሁ ጋር የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለአገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሰላሙን እንዲሰጥልን በችግሩ ምክንያት ተጎድተው በሕክምና የሚገኙ ወገኖቻችንን ጤናና ፈውስ እንዲሰጥልን በእነዚሁ ሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
- እንዲሁም ስለ አገራችን ዘላቂ ሰላም በሁሉም ዘንድ የጋራ ጥረት ማድረግ የሚገባ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን ግን ጥንትም ታደርገው እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ለሰላሙ መምጣት ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ የበኩሏን ጥረት በማድረግ የምትቀጥል ሲሆን በአገራችን ውስጥ ጥያቄ ያላቸውና ምላሽ የሚፈልጉ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎታቸውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ለመንግሥት እንዲያቀርቡ፤ መንግሥትም ባለበት አገራዊ ኃላፊነት መሠረት ጥያቄዎችን በአግባቡ እየተቀበለ ፍትሐዊና ወቅታዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡
- እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ዓለም የተለዩ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፣
- በሕክምና ላይ ላሉት ምሕረት ያድርግልን፣
- አገራችንና ሕዝቦቿን በሰላም ይጠብቅልን፡፡
አሜን፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት