ቅድስት አፎሚያ

ሰኔ 12 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ፍቃዱ ሣህሌ

በወርኃ ሠኔ መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ቅዱሳን መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራ የአስተራኒቆስ ሚስት የሆነች የቅድስት አፎምያን ታሪክ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

 

ቅድስት አፎምያ በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ነበረች፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ እንደነበር ታሪካቸው ይነግረናል፡፡

 

ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡

 

ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ ባያት ጊዜ ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ፣ ሌላ ባል አግብታ፣ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡

 

ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ፤ እነሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ፤ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡

 

በሠኔ ፲፪ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡

 

ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡

 

ለጊዜው “በኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡

 

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሠኔ ፲፪ ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡

 

ይህች የታመነች ቅድስት አፎምያ በሰላም እስክታርፍ ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጎዳና አስተውለን ይሆን? አስቀድማ ከባሏ ጋር አንድ ሆና በታማኝነት ፈጣሪዋን አገለገለችው፡፡ በኋላም የባሏን ኑዛዜ አክብራ ምንም እንኳን ኃጢአት ባይሆንባትም በሁለተኛ ትዳር ራስዋን ማጠላለፍ አልፈለገችም፡፡ በጎ ሥራ አብልጣ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ተፋጠነች እንጂ፡፡

 

ሰይጣን ልጅ አለመውለዷን ተጠቅሞ ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ መርምሩ” ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘውን መመሪያ ተጠቅማ ሰይጣንን በተወክሎ እግዚአብሔር ተቃውማ አሸነፈችው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ርዳታ ያገኘችውና በሰላም ዐርፋ ወዳገለገለችው እግዚአብሔር በክብር የሔደችው በጽናት ተጋድላ ነው፡፡

 

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፣ ድርሳነ ሚካኤል ዘወርኃ ሰኔ