ቅዱስ ፓትርያርኩ ለጻፉት ደብዳቤ ማኅበረ ቅዱሳን መልስ ሰጠ
ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታን አግኝቶ የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ሲፈተን ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናውን በምድራዊ ኃይል ሳይሆን በኃይለ እግዚአብሔር በብፁዓን አበው ጸሎትና በእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ምክርና ተግሣፅ ሲቋቋመው ቆይቷል፡፡
ነገር ግን አንዱ ፈተና ሲያልፍ ሌላው ከመተካቱ ውጭ አንድም ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳን ያለፈተና አገልግሎቱን ያከናወነበት ጊዜ የለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ሰሞኑን የተከሠተው ጉዳይ ነው፡፡ ሰሞኑን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንድ የመመሪያ ደብዳቤ ለተለያዩ አካላት መጻፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ደብዳቤ ብዙ ምእመናንንና አገልጋዮችን ያሳዘነ፣ ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ደስታን የፈጠረ ሆኗል፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩን ደብዳቤ መነሻ በማድረግም ማኅበረ ቅዱሳን እውነታውን ሁሉም አካላት ይረዱት ዘንድ መልስ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያሰተላለፉት የመመሪያ ደብዳቤና ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠው እውነታውን የሚያስገነዝብ የመልስ ደብዳቤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡