ቅዱስ ያሬድ በደብረ ታቦር ከተማ ተዘክሮ ዋለ
ደብረ ታቦርና ባህር ዳር ማዕከል
ሰንበት ትምህርት ቤቱ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አቀባበል አደረገ
«ዝክረ ቅዱስ ያሬድ» በሚል ርዕስ ከህዳር 11-12 ቀን 2003 ዓ. ም. ለሁለት ቀናት የቆየ የሥዕል ዓውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ተካሄደ፡፡ ዝግጅቱ የተካሄደበት ሰ/ት/ቤት አዲስ ለገቡ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አቀባበል አደርጓል።
በደብረ ታቦር ከተማ የተካሄደውን መርሐ ግብር ያዘጋጀው በማኅበረ ቅዱሳን የደብረታቦር ማዕከል ሲሆን ኢትዮጵያ በብሉይና በሐዲስ፣ የቅዱስ ያሬድ ማንነት፣ ቅዱስ ያሬድና አፄ ገ/መስቀል፣በመርሐ ግብሩ በመሪጌቶች በዜማ ገለጻ የተደረገባቸው 8ቱ የዜማ ምልክቶችና የዜማ መሣሪያዎች በሥዕል ዓውደ ርዕዩ የተካተቱ ሲሆን የአሁኑን ሐመረ ተዋሕዶ እትም የሽፋን ሥዕል በመጠቀም ያለውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን አርማና እንቅስቃሴ ገለጻ ተደርጐባቸዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማው በሚገኘው በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት አዳራሽ ተያያዥ መርሐ ግብር ተደርጓል፡፡ በዚህም በሰንበት ት/ቤቱ ሕፃናትና ወጣቶች መዘምራን እንዲሁም በግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች መዝሙሮች ቀርበዋል፡፡ የቅዱስ ያሬድን ሕይወት በተመለከተ፤ ዜማን በተመለከተም በግዕዝ ቋንቋ በሰንበት ት/ቤቱ ወጣቶች ጭውውት ቀርቧል፡፡ በመርሐ ግብሩ በርካታ ምዕመናን፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተሣታፊ እንደነበሩ ከሥፍራው የደረሠን ዘገባ ያስረዳል፡፡
ቀጥሎ ባለው ቀን የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ተቀብሏቸዋል፡፡ በዕለቱ ሰንበት ት/ቤቱ ስለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሕብረት መሥራት ይጠበቅብናል በማለት ለተማሪዎቹ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
በተያያዘም፣ ስብከተ ወንጌልንና አጠቃላይ ሁኔታን በተመለከተ መስከረም 22 ቀን 2003 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።ውይይቱን ያዘጋጀው በማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማዕከል ሲሆን ለውይይቱ መነሻ ይሆን ዘንድ በማዕከሉ ስለ ስብከተ ወንጌል አጀማመርና ሂደት እንዲሁም አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በጥናት መልክ ቀርቧል። ተሳታፊዎቹም በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት አካሂደዋል።
ተሳታፊዎቹ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ ወደ ፊት ከማዕከሉ ጋር አብረው ለመሥራት ቃል ገብተዋል። የማዕከሉ ሰባክያንም በየዓውደ ምህረቱ እየተገኙ አሁን እየታየ ያለውን ጉድለትና የስብከት መደጋገም ለማስቀረት በስብከት እንዲያገለግሉ ተጠይቀዋል።
በዕለቱም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ ዘላለም ደስታና የወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊ መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁንን ጨምሮ ከሀገረ ስብከቱና ከወረዳው ቤተ ክህነት እንዲሁም የየአድባራቱ ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎችና ሰባክያን ተሳታፊ ሆነዋል።