ቅዱስ ዑራኤል በግሸን አምባ

ጥቅምት 29 ቀን 2005 ዓ.ም.

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

  • ‹‹መስቀሉ በአዳል ሜዳ በር  እንዲገባ ያመላከተው ቅ/ ዑራኤል ነው››
  • ‹‹ጥር 22 ቀን ቤተ ክርስቲያኑ ይመረቃል››

 

ቅዱስ ተብለው የሚጠሩት ደገኛው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ካሌብ የሀገረ ናግራን ክርስቲያኖችን ለመታደግ ዘምተው የአሕዛቡን ንጉሥ ፊንሀስን ድል አድርገው ሲመለሱ በነበራቸው መንፈሳዊ ፀጋ እንዲሁም በአበ ነፍሳቸው ፈቃደ ክርስቶስ  ምክር የግሸን ደብረ ከርቤን ክብር በመረዳት ፤በ517 ዓ.ም ታቦተ እግዚአብሔር አብንና ታቦተ ማርያምን ከሀገረ ናግራን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በግሸን አምባ ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ቀዳሽና አወዳሽ መድበው ደብረዋታል፡፡ በወቅቱም አምባው መግቢያ ካለመኖሩ የተነሣ ተራራውን ሲዞሩ የንብ መንጋ በማየታቸው “አምባ አሰል” ብለውታል፡፡ ትርጓሜውም የማር አምባ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢው አምባ ሰል ሲባል ይኖራል፡፡

 

የግሸን አምባ ቀደሞ በቅዱሳን ስትገለገል የነበረች በመሆኗ በተለያዩ ጊዜያት ነገሥታት፣ የነገሥታት ቤተሰቦች ጎብኝተዋታል፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንና ሥርዓተ ንግሥና ተምረውባታል፡፡ ከዚህም የተነሣ ስመ ታፍልሶ ገጥሟታል፡፡ በዐፄ ድልነአድ ዘመነ መንግሥት በ866 ዓ.ም ደብረ ነጎድጓድ በ11ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረውና በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አናፂነቱ የሚታወቀው ንጉሥ ላልይበላ ከቦታው ደርሶ ቤተመቅደስ ለመሥራት ሲጀምር ‹‹ከዚህ ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን የምታነጸው አንተ ሳትሆን ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ነው፡፡›› ተብሎ በህልሙ ስለተነገረው፤ በሀገሩ በላልይበላ የእግዚብሔር አብ ቤተመቅደስን ሠርቶ ስለነበር ‹‹ደብረ እግዚአብሔር›› ብሎ ሰየመው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ነገሥታቱ ይማጸኑበት የክብርና የማዕረግ ዕቃዎችን ያስቀምጡበትና ይማሩበት ስለነበር ‹‹ደብረ ነገሥት›› ተባለች፡፡

 

በ1446 ዓ.ም ዕቅበተ እምነትን ከንግሥና አስተባብረው የያዙት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከአባታቸው ዐፄ ዳዊት ድንገተኛ ዕረፍት በኋላ ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድሩ ሥልጣነ መንበሩን በመያዛቸው ቀድሞ ለአባታቸው ተሰጥቶ የነበረውን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀል ተረከበው ‹‹መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር›› ተብለው በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ ለማሳረፍ ሱባኤ በመያዝ ጸሎተ ምህላ በማድረግ መስቀሉን ይዘው ኢትዮጵያን መዞር ጀመሩ ኋላም ፤ የመስቀሉን ማረፊያ መስቀለኛውን ቦታ ግሸን አምባን  አገኙ፡፡ ነገር ግን ወደ አምባው መግቢያ በር ባለማግኘታቸው ወደፈጣሪያቸው ጸሎት ማድረሱን ቀጠሉ በዚህ ጊዜ በቀራንዮ አደባባይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ሥጋውን ሲቆርስ ደሙን ሲያፈስ በጽዋዕ ብርሃን ተቀበሎ ደሙን ቤተ ክርስቲያን በሚሠራበት ቦታ ሁሉ የረጨው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል  ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብንና ሠራዊታቸውን መስቀሉን ይዘው በሚጓዙበት ሁሉ እየባረከና እየረዳቸው ግሸን አምባ ተራራን ሦስት ጊዜ ዞረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ አዳል ሜዳ በሚባለው ቦታ ‹‹በዚህ በኩል መስቀሉን ይዘህ ውጣ›› ብሎ ገለጸላቸው፡፡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብም በጣም ተደስተው በአዳል ሜዳ በኩል ባለው ገደል እየተንጠላጠሉ መስቀሉን ወደ ተራራው አውጥተው መስከረም 21 ቀን 1449 ዓ.ም  የእግዚአብሔር አብ ቤተመቅደስን በጥሩ ሁኔታ አሳንጸው መስቀሉንና በርካታ ንዋያተ ቅዱሳትን በብልሃትና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አደረጉ የእመቤታችንን ቤተመቅደስም ንግሥት እሌኒ አሳንጹ።

 

ከዘመናት በኋላ በ1940 ዓ.ም አካባቢ የተራራው እግረ መስቀሉ  በሆነው እና ደላንታ ሜዳ በተበለው ቦታ ላይ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አሰሩ፡፡ ኋላም ቀድሞ የነገሥታት ልጆች ይማሩበት በነበረው ቦታ ላይ ከአዳል ሜዳ ከፍ ብሎ በሚገኘው ቦታ ላይ በ1979 ዓ.ም የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተሠራ፡፡

 

በስተምሥራቅ አቅጣጫ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት መስቀሉ የገባበትና ቀድሞ ያረፈበት አዳል ሜዳ ከግሸን ተራራ መስቀለኛ አቀማመጥ አንፃር ሲታይ ሰፊና ማራኪ የመሬት አቀማመጥ አለው፡፡ ነገር ግን ከ500 ዓመታት በላይ በቦታው ቤተ ክርስቲያን ሳይሠራ ቆይቷል፡፡ ‹‹ጊዜ ሲደርስ አምባ ይፈርስ›› እንዲሉ አበው፤ አዳል ሜዳ ቅዱስ ዑራኤል መስቀሉ ወደ ተራራው እንዲገባ የመራበት፤ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በቅዱስ ዑራኤል ስም ቤተ ክርስቲያኑ እንዲታነጽ መስከረም 1994 ዓ.ም በአንድ ምእመን ሊሠራ ታስቦ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአቡነ አትናቴዎስ ተባርኮ ሥራው ሊጀመር ቻለ፡፡ ሆኖም ግን የሕንፃ ሥራው ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራው ሊቀጠል አልቻለም፡፡ ለዓመታትም ባለበት ሁኔታ ቆመ፡፡  ኋላም በ2004 ዓ.ም ስማቸው እንዲጠቀስ ባልፈለጉ አንድ ምእመን የቅ.ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ፡፡

 

7

ቤተ ክርስቲያኑን በገንዘባቸው ያሠሩት ምእመን  ስለ ቤተ ክርስቲያኑ አጀማመርና የሥራውን መፋጠን ሲገልጹ “የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተጀምሮ በመቆሙ ሁሌ ያሳስበኝ ነበር፡፡ ግሸን በመጣሁ ቁጥር ጅምሩን ቤተ ክርስቲያን ተሳልሜ ጸሎት አድርጌ እመለሳለሁ፡፡ ለምን እኛ አንሠራውም የሚል ሀሳብ መጣልኝ ጉዳዩንም ከጓደኞቼ ጋር ተወያየን፡፡ ከሰበካ ጉባኤው አባላት ጋር ውይይቶች አድርገን  ፈቃዳቸውን ገለጹልን፡፡  በዚህ መሰረት ኅዳር 17 ቀን 2004 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኑን እንድንሠራ ተስማማን፡፡ ተፈራረምን፡፡ ”በማለት ገልጸው በአጭር ጊዜ ተሠርቶ ማለቁን ሲያብራሩ አሰሪው  ‹‹ይገርመኛል የግሸን ተራራ መንገድ ለትራንስፖርት አይመችም ያውም በክረምት ግን በስድስት ወር መጠናቀቁ  ሊቀ መልአኩ የሠራው መሆኑን ነው የሚረዳኝ›› ለወጣቶች ምን ምክር አለዎት? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ቤተ ክርስቲያንን የሚሠራው እግዚአብሔር ነው፡፡ ትልቁ ነገር መልካም ልቦና መያዝና  የእግዚአብሔርን ፈቃድ መጠየቅ ነው፡፡ ›› በማለት ገልጸውልናል፡፡

 

ሕንፃውን ለማሠራት በአሰሪው ምእመን የተወከሉት መምሬ እሸቱ ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ መፋጠን ሲገልጹ ኅዳር 17 ቀን 2004ዓ.ም፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ለመሥራት ቢወሰንም ሥራው የተጀመረው ታኅሣሥ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ነው ፡፡  በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ግን ከዚህ  መድረሱ የመልአኩ ርዳታ ታክሎበት ነው፡፡ እኔ ያደኩበት ያገለገልኩበት ቦታ ነው ፡፡በተለይ ይህንን ቤተ ክርስቲያን ተወክዬ ማሠራቴ በጣም አስደስቶኛል፡፡ የቦታውን ክብርና ታሪክ አውቃለሁና፡፡

 

የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አባ ገ/ሥላሴ የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን መሥራትን አስመልክተው ሲገልጹልን ‹‹የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በዚህ ቦታ (አዳል ሜዳ) መሥራት የግሸን አምባን ሃይማኖታዊና ታሪካዊነት ማጉላት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክንፍ ስያሜ አለው ይህ ክንፍ አዳልሜዳ ይባላል፡፡  የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ያለበት ቦታ ደላንታ ሜዳ ፣ዋናው በር፣ በግራ ክንፍ ያለው ቦታ መሳቢያ ወይም ጋሻውድም ይባላሉ፡፡ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ መስቀሉን በኢትጵያ ምድር ለሦስት ዓመታት ይዘው ከዞሩ በኋላ፤ ከመስቀሉ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ያለው ቅዱስ ዑራኤል  ንጉሡ የግሸን አምባ ተራራ መግቢያ በቸገራቸው ሰዓት ‹‹በዚህ በኩል መስቀሉን ይዘህ ግባ›› በማለት አዳል ሜዳ በተባለው በኩል እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የቅዱስ ዑራኤልን ቤተ ክርስቲያን በግሸን ተራራ ላይ መሥራት፣ ማሠራት፣ መተባበር መታደል ነው፡፡ ባለታሪክ መሆን ነው፡፡ የሃይማኖቱ ዋጋ ተካፋይም ነው፡፡ ” በማለት ገልጸዋል።

 

የቅዱስ ዑራኤልን ቤተ ክርስቲያን ህንጻ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠቱን የሚናፍቁት የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም አስተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ  ተክለማርቆስ ከደስታቸው ብዛት የተነሣ ንግግራቸውን ከምርቃት ይጀምራሉ፡፡ ‹‹መልአኩ አይለያችሁ ለሥጋም ለነብስም ዋስ ጠበቃ ይሁናችሁ፡፡ ቦታውን እንዳሰባችሁት እሱ ያሰበላችሁ፡፡” ብለው ንግግራቸውን ይጀምራሉ ‹‹አሁን ቤተልሔሙን ከሠራን አገልግሎቱን መቀጠል እንችላለን፡፡ እስካሁንም የመንገዱ ሁኔታ ባለመመቸቱ እንጂ ይጠናቀቅ ነበር፡፡ ተመስገን ነው ፈቃዱ ከሆነ ጥር 22 ቀን 2005 ዓም.ቤተ ክርስቲያኑ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

 

እኛም ጥር 22 ቀን 2005ዓ.ም በግሸን አምባ ተራራ የቀድሞ መግቢያ(አዳልሜዳ) ላይ የተሠራውን የቅ.ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ምረቃ ላይ እንድንገናኝ እግዚአብሔር ይርዳን እንላለን፡፡