ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ሐምሌ ፪ ቀን ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ የኾው የቅዱስ ታዴዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ከመጽሐፈ ስንክሳርና ከገድለ ሐዋርያት ያገኘነውን የሐዋርያው ታዴዎስን ታሪክ በአጭሩ እነሆ፤

ቅዱስ ታዴዎስ አባቱ እልፍዮስ ይባላል /ማቴ.፲፥፫/፡፡ ሐዋርያው *ታዴዎስ ልብድዮስ*፣ *የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ* እየተባለም ይጠራል /ሉቃ.፮፥፲፮፤ ዮሐ.፲፵፥፳፪፤ ሐዋ.፩፥፲፫፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት አስቀድሞ ቅዱስ ታዴዎስን እንደ መረጠው መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡

ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ከአይሁድና ከአረማውያን ወገን ብዙዎችን በክርስትና ሃይማኖት አሳምኖ አስጠምቋል፡፡ አንድ ቀን ወደ ሀገረ ስብከቱ ወደ ሦርያ ለስብከተ ወንጌል ሲሔድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጐልማሳ አምሳል ተገልጦ *ወዳጄ ታዴዎስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ* ብሎ ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም የሐዋርያት አለቃ ነውና እንደ አባትነቱ ወደ ሦርያ ለማድረስ አብሮት ሔዶ ነበረ፡፡ ከከተማዋ አጠገብ ሲደርሱም አንድ ሽማግሌ በሮችን ጠምደው ሲያርሱ አገኙ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ሽማግሌውን ምግብ በለመናቸው ጊዜ *በሮቼን ጠብቁ* ብላዋቸው ምግብ ሊያመጡላቸው ወደ ቤታቸው ሔዱ፡፡

ሽማግሌው እስኪመለሱ ድረስም ቅዱስ ጴጥሮስ በሮችን ጠምዶ ሠላሳ ትልም ካረሰ በኋላ ቅዱስ ታዴዎስም በዚያ የነበረውን የሥንዴ ዘር መዝራት ጀመረ፡፡ የተዘራው ዘርም ወዲያዉኑ በቅሎ፣ አድጎ፣ እሸት ኾነ፡፡

ሽማግሌው ምግብ ይዘው ከቤታቸው ሲመለሱም ሐዋርያት ያደረጉትን ተአምር አይተው ደነገጡ፡፡ ከእግራቸው ሥር ወድቀው ለሐዋርያት ከሰገዱላቸው በኋላም *እናንተ ከሰማይ የወረዳችሁ አማልክት ናችሁን?* አሏቸው፡፡ እነርሱም *እኛ የእግዚአብሔር ባሮች እንጂ አማልክት አይደለንም* አሉ፡፡

ሽማግሌውም *ስላደረጋችሁልኝ በጎ ሥራ በምትሔዱበት ቦታ ኹሉ ልከተላችሁን?* ባላቸው ጊዜ *ይህንን ልታደርግ አይገባም፤ ነገር ግን በሮችን ለጌታቸው መልስና በቤትህ የምንበላውን ታዘጋጅልን ዘንድ ለባለቤትህ ንገራት፡፡ እኛ ወደዚህች ከተማ ገብተን እግዚአብሔር እስከሚጠራን ጊዜ ድረስ እንቆያለንና* አሏቸው፡፡

ሽማግሌውም ከሥንዴው እሸት ይዘው፣ በሮችን እየነዱ ወደ ከተማ ሲሔዱ የከተማው ሰዎች ወቅቱ የእርሻ እንጂ የእሸት ጊዜ አልነበረምና እየተገረሙ *ይህንን እሸት ከወዴት አገኘኸው?* አሏቸው፡፡ ሽማግሌው ግን ምላሽ አልሰጧቸውም ነበር፡፡

ሽማግሌው ሐዋርያት እንደዘዟቸው በሮችን ለጌታቸው መልሰው ቤታቸውን አዘጋጅተው ራት እንድታዘጋጅላቸው ለሚስታቸው ነገሩ፡፡

ወሬውን የከተማው መኳንንት በሰሙ ጊዜም ሽማግሌውን *በክፉ አሟሟት እንዳትሞት እሸቱን ከወዴት እንዳገኘኸው ንገረን* ብለው መልእክተኞችን ላኩባቸው፡፡ ሽማግሌውም *ሕይወት ከእኔ ጋራ ሳለ ሞትን አልፈራም* ካሉ በኋላ ሐዋርያት ያደረጉትን ኹሉ ነገሯቸው፡፡

መኳንንቱ *ሐዋርያቱን አምጣቸው* ሲሏቸውም ሽማግሌው ወደ እርሳቸው ቤት ሲመጡ ማግኘት እንደሚችሉ ነገሯቸው፡፡

መኳንንቱም ሰይጣን ልቡናቸዉን ስለ ለወጠው ሐዋርያቱን ለመግደል ተነሳሡ፡፡ እኩሌቶቹ ግን *አምላካቸው ኢየሱስ የሚሹትን ኹሉ እንደሚያደርግላቸው ሰምተናልና ልንገድላቸው አንችልም፡፡ ነገር ግን አመንዝራ ሴት ወስደን በከተማው በር ርቃኗን እናስቀምጣት፡፡ እርሷን ሲያዩ ወደ ከተማችን አይገቡም፤* አሉ፡፡

እንደተባባሉትም ሴትዮዋን በከተማው በር ርቃኗን አስቀመጧት፡፡ ሐዋርያው ታዴዎስ ባያት ጊዜም *ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ ከተማው ገብተን በከበረ ስምህ እስክንሰብክ ድረስ ይህቺን ሴት በአየር ላይ ይሰቅላት ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላክልን* ብሎ ጸለየ፡፡

ጌታችን ጸሎቱን ተቀብሎት ሴትዮዋ በተሰቀለች ጊዜም የከተማው ሰዎችና መኳኳንንቱ ኹሉ እያዩአት *አቤቱ ፍረድልኝ* እያለች ትጮኽ ጀመር፡: መኳንንቱ ግን ሰይጣን ልቡናቸውን አጽንቶታልና የሐዋርያትን ትምህርት አልተቀበሉም፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ የሰዎቹን ልቡና የማረኩ መናፍስትን ርኩሳንን አባረረላቸው፡፡ ሰዎቹም የሐዋርያትን ትምህርት ተቀብለው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡

ሐዋርያው ታዴዎስም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ካጠመቃቸው በኋላ ኤጰስ ቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው፡፡ በአየር ላይ የተሰቀለችውን ሴትም አውርዶ ዲያቆናዪት አደርጎ ሾማት፡፡

በሐዋርያት እጅም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዕውሮች አዩ፤ ሐንካሶች ቆመው ሔዱ፤ ዲዳዎች ተናገሩ፤ ደንቆሮዎች ሰሙ፤ ለምጻሞች ነጹ፤ አጋንንትም ካደሩባቸው ሰዎች እየወጡ ተሰደዱ፤ ሙታንም ተነሡ፡፡ የከተማው ሰዎችም ይህንን ተአምር አይተው በቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ በእግዚአብሔር አመኑ፡፡

አንድ ሰይጣን ያደረበትና ገንዘብ የሚወድ ጐልማሳ ባለጸጋም ወደ ሐዋርያው ታዴዎስ መጥቶ ሰገደለትና *የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?* ሲል ጠየቀው፡፡

ሐዋርያው ታዴዎስም *እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፡፡ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር፡፡ በአንተ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌላው ላይ አታድርግ፡፡ ደግሞም ገንዘብህን ሸጠህ ለድኆችና ለምስኪኖች ብትሰጥ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ድልብ ታገኛለህ* አለው፡፡

ጐልማሳውም ይህንን በሰማ ጊዜ ተቈጥቶ ሐዋርያውን አነቀው፡፡ የእግዚአብሔር ኀይል በይረዳው ኖሮ ሐዋርያው ከመታነቁ ጽናት የተነሣ ዓይኖቹ ሊወጡ ነበር፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም *የክርስቶስን አገልጋይ እንዴት ደፍረህ ታንቃለህ?* ባለው ጊዜ ጐልማሳው ቅዱስ ታዴዎስን ለቀቀው፡፡

ያን ጊዜም ቅዱስ ታዴዎስ *ጌታችን ሀብታም መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ሲል በእውነት የተናገረው እንዳንተ ላለው ሀብታም ነው* አለው፡፡

ጐልማሳውም *ይህ ሊኾን አይችልም* ባለ ጊዜ ሐዋርያው ታዴዎስ በመንገድ ሲያልፍ ያገኘውን ባለ ግመል አስቁሞ መርፌ ገዝቶ ሊያሳየው ወደደ፡፡ መርፌ ሻጩም ሐዋርያውን ለመርዳት ፈልጎ ቀዳዳው ሰፊ የኾነ መርፌ አመጣለት፡፡

ቅዱስ ታዴዎስም *እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ፤ ነገር ግን በዚህች አገር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ቀዳዳው ጠባብ የኾነ መርፌ አምጣልን* አለው፡፡

ሐዋርያው ቀዳዳው ጠባብ የኾነውን መርፌ ተቀብሎም *ኀይልህን ግለጥ* ብሎ ወደ ጌታችን ጸለየ፡፡ እጁንም ዘርግቶ ባለ ግመሉን *በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከግመልህ ጋር በመርፌ ቀዳዳው ውስጥ እለፍ* አለው፡፡ ሰውየውም እስከ ግመሉ ድረስ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡

ዳግመኛም *ሕዝቡ የፈጣሪያችንን የክርስቶስን ኀይል ይረዱ ዘንድ ዳግመኛ ገብተህ እለፍ* አለውና ሦስት ጊዜ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡

ሕዝቡም ይህንን ተአምር አይተው *ከቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ በቀር ሌላ አምላክ የለም* እያሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፡፡

ያ ጐልማሳ ባለጸጋም ከሐዋርያው ታዴዎስ እግር በታች ወድቆ ሰገደና *ኀጢአቴን ኹሉ ይቅር በለኝ፡፡ ገንዘቤንም ኹሉ ወስደህ ለድኆችና ለምስኪኖች አከፋፍልኝ* አለው፡፡ ሐዋርያውም እንደ ለመነው አደረገለት፡፡

የክርስትናን ሃይማኖትን ሕግ አስተምሮም አጠመቀውና ሥጋውንና ደሙን አቀበለው፡፡ ኹሉንም በቀናች የክርስትና ሃይማኖት አጸናቸው፡፡ ከዚያ በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ከዚያች ከተማ ወጡ፤ ሕዝቡም በሰላም ሸኟቸው፡፡

ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ ቆይቶ ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራ ከደረሰበት በኋላ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሐምሌ ፪ ቀን በሰላም ዐርፏል፡፡

በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመንም ሐምሌ ፳፱ ቀን የከበረ ዐፅሙ ከሦርያ ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ፈልሷል፡፡ በዚያች ዕለትም ቤተ ክርስቲያን ሠርተው የቅዱሱን ዐፅም በውስጧ አስቀምጠውታል፡፡ ከዐፅሙም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገልጠዋል፡፡

ኹላችንንም የሐዋርያው ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሐምሌ ፪ እና ፳፱ ቀን፤

ገድለ ሐዋርያት፣ ፲፱፻፺፬ ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፣ ገጽ ፻፷፭-፻፸፩፡፡