ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የወሰነው ውሳኔ ለማኅበሩ መድረሱ ተገለጸ
ሐምሌ 23ቀን 2004 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
የ2004 ዓ.ም. የግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የወሰነው ውሳኔ በደብዳቤ የተገለጸ መሆኑን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጻፉት ደብዳቤ ማኅበሩ ለብፁዕነታቸው ተጠሪ እንዲሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መወሰኑን ጠቅሰው ከማኅበሩ እድገት ጋር አብሮ ሊሄድ እንዲችል የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አስጠንተው ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በቁጥር 451/275/2004 በቀን 13/11/2004 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ “ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተለይቶ የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ተጠንቶ እስኪወጣለት ድረስ ተጠሪነቱ ለብፁዕነትዎ ሆኖ ሲሠራ እንዲቆይ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወስኗል፡፡” በማለት ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጠኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የተመረጡትን የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስም ዝርዝር ጠቅሰዋል፡፡በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፤ ጌዴኦና አማሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ፤የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት የክብር ፕሬዚዳንት ቢሮ ዋና ጸሐፊና የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ የሰዋሰወ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፤ ከሕግ ባለሙያዎችና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር በመሆን መተዳደሪያ ደንቡን አስጠንተው ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲያቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወጥቶ ለጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ እንዲሆን በግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወሰነ ሲሆን በዚሁ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶስ ስለማኅበሩ በሰጠው አስተያየት “ማኅበረ ቅዱሳን የመሥራት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰና በቤተ ክርስቲያኒቱ እየሠራ ባለው ሥራ ሁሉ አብተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በስፋት እየጠቀመ ያለ በምሁራን የታቀፈ፤ ሁለንተናዊ ዝግጅት ያለው ማኅበር ስለሆነና ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ በመሆኑ እራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ሊዘረጋለት ይገባል” ማለቱ ይታወሳል፡፡