‹‹ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው›› (መዝ.፶፱፥፬)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መስከረም ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ቅዱስ መስቀል ቀስት ከተባለ ጠላታችን ዲያብሎስ እንድናመልጥና ድል እንድናደርገው የተሰጠን ነው፤ ቅዱስ መስቀል መድኅን ዓለም ክርስቶስ ተሰቅሎ በክቡር ደሙ ቀድሶ የሰጠን፣ ሰላማችን የታወጀበት ኃይላችን፣ የሰላም አርማችን ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰቀል ላይ ተሰቅሎ እኛን ከማዳኑ በፊት በኦሪቱ በአንዳንድ አገራት የወንጀለኞች መቅጫ ነበር፤ ጌታችን በማእከለ ምድር ቀራንዮ ተሰቅሎ በክቡር ደሙ ቀድሶ የኃጢአት ጨለማ ተወገደበት፣ የብርሃን ዐምድ ሆኖ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ነጻ ወጣን፡፡ በመስቀሉ በተፈጸመው ቤዛነት ሕይወተ ሥጋ፣ ሕይወተ ነፍስን አግኝተናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል አድርጎበታል፤ ለእኛም የድል ምልክት የነጻነት ዓርማ ሆኖናል፡፡ ‹‹..እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡›› (ኤፌ.፪፥፲፬-፲፮)
ቅዱስ መስቀል በዘባነ ኪሩብ ላይ የሚቆም የጌታችን እግሮች ተቸንክረው የዋሉበት የመድኅን ዓለም ክርስቶስ ዙፋን ነው፤ የእግዚአብሔርን ፍቅሩን የምናሳስብበት፣ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹…እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅሩን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል›› በማለት እንደገለጸው እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጸበት፣ በቅዱስ ደሙ ቀድሶ የሰጠን መስቀሉን ባየንና በተሳለምን ጊዜ ሁሉ የቀራንዮን ፍቅር እንድንዘክር፣ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ የሚሰብከን፣ ፍቅርን የሚያስታውሰን ፣ የእግዚአብሔርን ውለታ እንዳንረሳ የሚያደርገን ነው፡፡ (፩ኛዮሐ.፫፥፲፮)
ቅዱስ መስቀል ዲያብሎስ ያፈረበት፣ ሞተ ነፍስ ድል የተደረገበት፣ የሕይወት መንገዳችን እንቅፋት የነበረው ጠላታችን ዲያብሎስ ከመንገዳችን ተጠርቆ የተወገደበት፣ በእኛ ላይ የነበረው ኃይል የተነጠቀበት ነው፤ ‹‹… በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዝት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወገደው….›› እንዲል፤ (ቆላ.፪፥፲፬) ዲያብሎስ ከዙሪያችን እንዳይቀርብ፣ እንዲርቀን የምናደርገው በስመ ቅድስት ሥላሴ በቅዱስ መስቀል አማትበን ነው፡፡
ቅዱስ መስቀል ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የተፈተተበት፣ የመድኃኒታችን እናቱ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናትነት የምናስታውስበት ነው፤ ቅዱስ መስቀልን በተሳለምን፣ ባማተብን፣ ባየነው ጊዜ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት ሕይወትን እንዳደለን እናት ትሆነን ዘንድ እመቤታችንን በመስቀሉ ሥር እንደሰጠን ያስታውሰናል፡፡
ቅዱስ መስቀል በበደላችን ከገነት በወጣን ጊዜ በእሳት ሰይፍ ታጥራ የነበረችው ገነት በክርስቶስ ሞት እንደተከፈተችልን እና ዳግመኛም እንኖርባት ዘንድ እንደተሰጠችን ያስታውሰናል፤ መንፈሳዊ ኃይልን የሚያቀዳጀን ጠላታችን ላይ ግርማ ሞገስን የሚያላብሰን፣ ዲያብሎስን ቀጥቅጠን ዓለምን የምናሸንፍበትን ኃይል በቅዱስ መስቀሉ አግኝተናል፡፡ ‹‹…የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት እኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡›› (፩ኛቆሮ.፩፥፲፰)
ቅዱስ መስቀል ሥራችንን ሁሉ የምንባርክበት ትምክህታችን ነው፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናንን በላከው መልእክቱ ‹‹…ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› በማለት እንደገለጸው ቅዱስ መስቀል ትምክህታችን ነው፤ አጋንንትን እናርቅበታለን፡፡ (ገላ.፮፥፲፬)
ለቅዱስ መስቀል ክብር እንሰጣለን፤ የጸጋ ስግደትም እንሰግዳለን፤ ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ሲል፤ ‹‹…እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን …፡፡›› (መዝ. ፻፴፩፥፯) በማለት በተነበየው መሠረት የመድኅን ዓለም ክርስቶስ እግሮቹ በቅዱስ መስቀል ላይ በዕለተ ዐርብ ተቸንክረውበታል፤ በክቡር ደሙ ተቀድሷልና የጸጋን ስግደት እንሰግድለታለን፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎቷ ምስጋናን ስታቀርብ ‹‹..እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር…›› ለዚህ ነው፡፡ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ለተሰቀለበት በክቡር ደሙ ለቀደሰው መስቀል እሰግዳለሁ›› በማለት ምእመናንን ለቅዱስ መስቀሉ የአክብሮት ጸጋ ስግደት እንዲሰግዱ ሥርዓትን ያበጀች፡፡ የጌታችን መከራ መስቀሉ ስለ እኛ ሲል መሞቱ በሚታሰብበት በሰሙነ ሕማማት በዕለተ ዐርብ ቅዱስ ያሬድ እንዳስተማረን፣ ካህናት አባቶች እንዲህ በማለት ለቅዱስ መስቀሉ ስግደት እንደሚገባ በዜማ በታጀበ፣ በተግባር በተደገፈ የአክብሮት ስግደት ለቅዱስ መስቀሉ ያቀርባሉ፤ ‹‹…ለመስቀልከ ንሰግድ ኦ ሊቅነ፤ መምህራችን ሆይ ለመስቀልህ እንሰግዳለን፡፡›› ምእመናንንም የአባቶችን ፈለግ ተከትለው ክብር ለሚገባው ከጠላት ዲያብሎስ ፍላጻ ላመለጥንበት ኃይላችን፣ ቤዛችን (መዳኛችን) ለሆነው መስቀል ውዳሴን ከስግደት ጋር ያቀርባሉ፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጎብኘን፤ አሜን!