ቅዱስ ላሊበላ
ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ዣን ስዩምና ከእናቱ ኪርወርና በታኅሣሥ ፴፱፣ ፲፻፩ ዓ.ም በላስታ ቡግና ወረዳ ልዩ ስሟ ሮሀ በተባለችው ሥፍራ ተወለደ፡፡ አባቱ በላስታ አውራጃ የቡግናው ገዢ ነበር፤ እናቱ ደግሞ አገልጋይ ነበረች፡፡ የልደቱን ነገር አስቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነግሯት ነበር፤ ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜም ብዙ ነጫጭ ንቦች መጥተው በሰውነቱ ላይ አርፈው እንደ ማር እየላሱት ስለታዩ እናቱ ‹‹ልጄን ንብ ዘበኛ ሆኖ ይጠብቅልኛል›› ስትል ስሙን ‹‹ላል ይበላል›› ብላዋለች፡፡ ‹ላል› በአገውኛ ‹ንብ› ማለት ነው፡፡ በጊዜ ብዛት በተለምዶ ነው ‹‹ላሊበላ›› ተብሎ መጠራት ተጀመረ፡፡ ንቦቹ ግን ሥጋዊ ንቦች ሳይሆኑ በንብ የተመሰሉ መላእክት ናቸው፡፡ ንጉሥ መሆኑን እያመለከቱ ሃይማኖትና ምግባር ማር ከእርሱ እንደሚቀዳ ለማመልከት በንብ ሠራዊት ተመስለው ሰውነቱን ላሱት፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ኤርምያስም በእናቱ ማኅፀን ሳለ ነው መንፈስ ቅዱስ ሞላበት፡፡
ወላጆቹም እግዚአብሔርን በመፍራትና በበጎ ምግባር አሳደጉት፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ካደገ በኋላም ስለ ቅድስናውና ስለ ንግሥናው ትንቢት እየተነገረ ስለነበር ወንድሙ ቀናበት፡፡ በዚህም የተነሣ ላሊበላ ሀገሩን ለቅቆ ወደ እየሩሳሌም አቀና፤ በዚያም ለብዙ ዓመታት ቆየ፡፡
ቅዱስ ላሊበላም ከስደት እንደተመለሰ ወንድሙ መልእክቶኞችን ልኮ ካስመጣው በኋላ ምክንያት አድርጎ ከሦስት እስከ ሰባት ሰዓታት ያህል እንዲገረፍ አደረገ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከግርፋቱ ሠውሮት ስለነበር ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፡፡ ወንድሙም ከፊቱ ባቀሞው ጊዜ ይህን ተአምር አይቶ ከመካንንቶቹ ጋር አደነቀ። ይቅርታ እንዲያደርግለትም ቅዱስ ላሊበላን ጠይቆት እርቅ ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ መስቀል ክብራን አገባ፡፡ በ፲፻፩፻፶፮ ዓ.ም ‹ገብረ መስቀል› ተብሎ ነገሠ፡፡
በዘመነ መንግሥቱም ዘወትር ለድሆችና ለምስኪኖች እንዲሁም ለችግረኞች ይመጸውት ነበር፡፡ በአንድ ወቅትም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ወደ ሰማያት አወጣው፤ ዐሥሩን አብያተ ክርስቲያናትንም እንዴት መሥራት እንደሚችል አሳየው፡፡ ወደ ምድርም ተመልሶ መንፈስ ቅዱስ እንዳረቀቀው በአስደናቂ ጥበብ አብያተ ቤተ ክርስቶያናቱን አነጻቸው፡፡
ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በሦስት መደብ የተከፋፈሉ ናቸው፤ ሁሉም የመሬት ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያም አላቸው፡፡ በመጀመሪያው መደብ ውስጥ ‹ቤተ መድኃኒዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ-መስቀል፣ ቤተ-ደናግል፣ ቤተ-ጎለጎታ እና ቤተ-ሚካኤል ሲገኙ፤ በሁለተኛው መደብ ውስጥ ደግሞ፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-መርቆሪዮስ፣ ቤተ-ሊባኖስ እና ቤተ-ገብርኤል› ይገኛሉ፡፡
በሦስተኛው መደብ ውስጥ የሚገኘው ‹ቤተ-ጊዮርጊስ› ነው፡፡ ቤተ-ጊዮርጊስ ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በስተመጨረሻ የተሠራና እጅግ ያማረ፣ በኪነ ሕንፃ ውበቱም ከሁሉም የላቀ ነው፡፡
ይህም የአብያተ ክርስቲያናቱ ሠሪዎች በሥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ የመምጣታቸው ምሥክር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜም የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲወሱ የሚታየው ምስል የዚሁ የቤተ-ጊዮርጊስ ምስል ነው፡፡ ገድለ ላሊበላ እንደሚያስረዳው የፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ ሥራ የተጀመረው በላሊበላ ዐሥረኛ ንግሥ ዘመኑ ነው፡፡ ሥራውን ለማጠናቀቅም ፳፫ ዓመት ፈጅቷል፡፡ አብያተ ክርስቲያነቱንም አንጾ ከጨረሰ በኋላ መንግሥቱን ለወንድሙ አወረሰው፡፡
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በብርሃን ሠረገላ ተቀምጦ የሚስፈራ መብረቅን የተጎናጸፉ አእላፍት ሠራዊቶቹ ዙሪያውን ሆነው ወደርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ ‹‹ወዳጄ ላሊበላ ሆይ ሰላም ይሁንልህ፤ እኔ በማያታበል ቃሌ እነግርሃለሁ፤ ማደሪያህ በክብር ሁሉ ከከበሩ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያቶቼ ጋር ይሁን፡፡ በጸሎትህና በቃል ኪዳንህ ለሚታመን እምነቱ እንደ ጴጥሮስና ጳውሎስ ደም መፍሰስ ይሆንለታል፡፡ ወደ ቤተ መቅደስህም የሄደ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደሴ እንደ ሄደ ይሆንለታል፤ መቃብርህንም የተሳለመ የሥጋዬን መቃብር እን ተሳለመ ይሆንለታል፡፡ በዓመታቱ ወሮች ሁሉ የተራቡትን እያጠገበ የተጠመቁትንም እያጠጣ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ የተሠወረ መና እመግበዋለሁ፤ የሕይወት ጽዋንም አጠጣዋለሁ፡፡ በመታሰቢያህ ቀንም ዕጣን ወይም ስንዴ የሚያገባውን እኔ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በውስጠኛው መጋረጃ አስቀምጬ ከተቆረሰው ሥጋዬ አቆርበዋለሁ፤ በአማላጅነትህም እየታመነ የገድልህንና የቃል ኪዳንህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ያንተ ስም በተጻፈበት ቦታ እኔ ስሙን እጽፋለሁ፤ በፍጹም ልቡ ለሚያምን ይህን የማይታበል ቃል የተናገርኩ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ እኔ ነኝ፡፡›› ቅዱስ ላሊበላም ይህን ቃል ኪዳን በተሰጠው ጊዜ ጌታችን እያመሰገነ በምድር ወድቆ ሰገደ፡፡ ጌታችንም ሰላምታ ከሰጠው በኋላ በክብርና በምስጋና ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ከዚህ በኋላ ጥዊት ታሞ በሰላም ዐረፈ፤ የብርሃን መላእክትም ነፍሱን ተቀብለው የዘለዓለም ሕይወት ማደሪያ ወደሆነው ማረፊያው ገነት አስገቡት፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በቅዱስ ላሊበላ ጸሎት ነፍሳችንን ያማርልን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡- ገድለ ላሊበላ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ