ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!
ሁለመናችንን በሐዲስ ምግብና እየመገበ የሚጠብቀን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ፳፻፲፮ ዓ.ም. ወደ ዘመነ ማቴዎስ ፳፻፲፯ ዓ.ም. በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!
‹‹ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ፤ የልባችሁን መንፈሳዊ አእምሮ አድሱ›› (ኤፌ.፬÷፳፫)፤ በገሃዱ ዓለም በግልጽ እንደምናስተውለው ከሞላ ጎደል የማያረጅ የለም የማይታደስም የለም፤ መታደስ ባይኖር ኖሮ ሕይወታውያን ፍጡራን በሕይወት መቀጠል አይችሉም ነበር፤ የዘመን መታደስም የሥነ ፍጥረት አንዱ አካል ነው፤ እኛ ሰዎችም የሕዳሴው መሪዎች ሆነን የተሾምንባትን ምድር በየጊዜው በልማት እንድናድሳት እግዚብሔር አዞናል፤ የሃይማኖት ትልቁ ተስፋም መታደስ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ዘመንም እንደ ሌላው ያረጃል፤ ይታደሳልም፤ “ወናሁ እገብር ኵሎ ሐዲሰ እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የሚለው የእግዚአብሔር ቃልም የዚህ አስረጅ ነው፤ በዚህ ሕገ እግዚአብሔር መሠረት እነሆ አሮጌውን ዘመን የምንሸኝበት አዲሱን ዘመን ደግሞ የምንቀበልበት ምዕራፍ ላይ ነን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
ፍጥረታትን በማደስ ሕይወትን የማስቀጠል ሥልጣን በዋናነት የእግዚአብሔር ብቻ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሰውም ሥነ ፍጥረትን በማደስና በማጐስቈል ረገድ ያለው ሚና ቀላል አይደለም፤ ይህም ሰው በምድር ላይ እንዲሠለጥን ወይም ፍጥረትን እንዲገዛና እንዲመራ በፈጣሪ ከተሰጠው ሥልጣን የሚመነጭ ነው፤ ዛሬም ዓለማችን በመታደስ ያይደለ በማርጀት ላይ የምትገኘው ከሰዎች ድርጊት የተነሣ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ የአየሩ መለወጥ፣ የበረዶው መቅለጥ፣ የሙቀቱ ማሻቀብ፣ የዝናሙ ማጥለቅለቅ፣ የባሕሩ መናወጥ ወዘተ. እየተፈጠረ ያለው ኃላፊነት ከጐደለው የሰው አጠቃቀም የተነሣ እንደሆነም ተደጋግሞ እየተነገረን ነው፤ እኛም በዓይናችን እያየን ነው፤
ከዚህ በተለየ ደግሞ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰው ምድረ በዳውን ወደ ሐመልማለ ገነት ሲቀይር የሚስተዋልበት ሌላ ገጽታ አለ፤ ይህ የሚያሳየው ሰው በሥነ ፍጥረት ላይ የማደስና የማጐስቈል ብሎም የማጥፋት ሚና ያለው መሆኑን ነው፤ ሰውም እንደሌላው ሥነ ፍጥረት የሚያረጅም የሚታደስም ነው፤ ይህም በብዙ አቅጣጫ ሊከሠት ይችላል፤ ሰዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሁለቱንም ማለትም ማርጀትና መታደስን ሊያስተናግዱ ይችላሉ፤ ሰዎች በመንፈሳዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በማኅበራዊና በመልካም አስተዳደር ወዘተ. የላቀ ዕድገትን ሲያስመዘግቡ በመታደስ ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፤ የዚህ ተቃራኒ የሆነውን ይዘው እየተጓዙ ከሆነ ደግሞ ተቃራኒውን ወይም ማርጀትን እያስተናገዱ እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች በመንፈሳቸውም ሆነ በአእምሮአቸው፣ በነፍሳቸውም ሆነ በአካላቸው በመታደስ እንዲኖሩ እንጂ እርጅና እንዲጫጫናቸው አይፈልግምና “የልባችሁን መንፈስ አድሱ” በማለት ያስተምረናል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
የክርስትና ሃይማኖት የመጨረሻው ግብ የፍጥረት መታደስ ነው፤
ይህም ማለት የሃይማኖቱ አስተምህሮ መዳረሻ ከሞት በኋላ ትንሣኤ ከዚያም ፍጻሜና እንከን የሌለው ጣዕመ ሕይወት አለ ብሎ ሰውን ለዘላለማዊ ሕዳሴ ማብቃት ነው ማለት ነው፤
ከዚህ አንጻር የሰው የመጨረሻ ዕድሉ ማርጀት ሳይሆን መታደስ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ እግዚአብሔር የሰውንና የፍጥረታትን መታደስ የሚሻው በሰማያዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በምድራዊው ዓለምም ጭምር ነው፤ ለዚህም ነው በየወቅቱ የሥነ ፍጥረትን ውበት እያደሰ የሚመግበን፤ አሁን ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው እኛስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመታደስ ተዘጋጅተናል ወይ? የሚለው ነው፤ ዛሬ እያንዳንዳችን ይህንን ጥያቄ አንሥተን ኅሊናችንን በጥልቀት መጠየቅ አለብን፤ በዚህም ሳናበቃ መልሱን በትክክል ማግኘት አለብን፤ በሁለንተናችን ለመታደስም ቈራጥ ውሳኔ በራሳችን ላይ ማሳለፍ አለብን፤ አዲሱ ዘመን አዲስና ብሩህ የሆነ የደስታ ሕይወት ሊያጐናጽፈን የሚችለው በዚህ መንፈስ ተቀብለን ስንጠቀምበት ነው፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት የታደሱ ያይደሉ በርካታ ዓመታት ተጭነውን አልፈዋል፤ ቀድሞ እንበልጣቸው ከነበሩ አህጉር በታች ሆነንም በርካታ ዓመታትን አስቈጥረናል፤ የእርስ በርስ ግጭት፣ ረኃብ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ኋላ ቀርነት የመልካም አስተዳደር እጦት በዓለም ፊት ልዩ መለያችን ሆኖአል፤ ዛሬም ከዚህ አልተላቀቅንም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አጠናክረን ለማስቀጠል ውል የገባን እስክንመስል ድረስ እየቀጠልንበት እንገኛለን፤ በእውነቱ እንዲህ የመሰለ ልምድ ልናፍርበትና ንስሐ ልንገባበት እንጂ ልናስቀጥለው አይገባም፡፡
በተፈጥሮ የታደለች ሁሉንም አሟልታ የምትገኝ ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ይዘን ከሰው በታች ሆነን ስንገኝ በስንፍናችሁ ከምንባል በቀር የሀብተ ጸጋ እጥረት አለባችሁ የሚለን አናገኝም፤
ስለዚህ አሁንም ለኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በአጽንዖት የምናስተላልፈው መልእክት ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውን አይደለም ለዓለም የሚተርፍ ሀብተ ጸጋ አላትና ለኔ ለኔ በመባባል የሕዝባችንን ሰቆቃው አናስረዝም፡፡
ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት የሚለውን ጥሬ ሓቅ በደምብ አላምጠን መዋጥ አለብን፣ ከዚያም በእኩልነትና በአንድነት ሀገራችንን እናድስ፤ ከሌሎች በደባል የሚመጡ ነገሮችን ሳይሆን የሀገሪቱ በሆኑ ዕሤቶች እንመራ፤ ለበርካታ ዓመታት የተሸከምነው ደባል የአስተዳደር ስልት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ከማንም በላይ በፈጣሪው እንደሚመካ እሱንም አጥብቆ እንደሚያምን ልኂቃኖቻችን ተገንዘቡልን፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ታሪካችን ከእግዚአብሔር ተለይተን አናውቅም፤ በዚህም ተጠቃሚዎች እንጂ ተጐጂዎች የሆንበት ጊዜ የለም፤ በለመደው እምነት ባህልና ዕሤት ሕዝቡን ብንመራው ሁሉም ነገር ቀላል ይሆንልናል፤ ከዚህ ውጭ እንምራህ ብንለው ግን ያጋጠመንን ችግር ማስቀጠል ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ የሁሉም መነሻ ማለትም የክፋትም ሆነ የደግነት መነሻ ውሳጣዊ አእምሮአችን ነውና እሱን በማደስ በአዲሱ ዓመት አገራችንን እንድናድስ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም
አዲሱ ዘመን በሃይማኖት መንፈስ ግጭትን በውይይት፣ መለያየትን በአንድነት፣ አለመግባባትን በዕርቅ ፈትተን በመታደስ ማማ ላይ የቆመ ማኅበረ ሰብን ለመገንባት ሁላችንም ጥረት እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
አዲሱ ዓመት የሰላም የዕርቅ የእኩልነትና የአንድነት ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ