ስንክሳር፡- መስከረም ስድስት
መስከረም 6 ቀን 2008 ዓ.ም
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነብይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ዐረፈ፡፡
ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ፣ እሊህም ኦዝያን፣ ኢዮአታም፤ አካዝ፤ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው፡፡
በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ እነሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል፡፡ እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወለወዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፡፡
ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡
እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚያስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መስዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ፡፡
የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በእግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ፡፡
በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰናክሬም ሠፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ አርበኞችን ገደለ፡፡ የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሱ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ፡፡
ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ አንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው፡፡
ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፣ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ፡፡ ይህን ከነገረው በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነብዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ፣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፡፡ እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው፡፡
ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለመመለሳቸው ትንቢት ተናገረ፡፡ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ፡፡
ክብር ይግባውና ስለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ፣ እንዲህም አለ፡፡ እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም፡፡
ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በምናሴ ላይ ትንቢት ተናገረ፣ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው፣ ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ፡፡
ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል፡፡ እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና ጌታችን ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከሁላችን ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 23-25፡፡Â