“ስለ ምን ጾምን?” (ኢሳ.፶፰፥፫)
መምህር ዮሴፍ በቀለ
ጥር ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የነነዌ ከተማ ሰዎች ኃጢአት በትንቢተ ዮናስ ውስጥ አንድ ሁለት ተብሎ አልተገለጸም፤ በጥቅሉ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ” ተብሎ በእግዚአብሔር ከመገለጹ በቀር አልተዘረዘረም። (ዮናስ ፩፥፪) ሆኖም ክፉታቸው ወደ ፊቴ ወጥቶአልና የሚለው የልዑል አምላክ ቃል የኃጢአታቸውን ታላቅነት ያመለክታል። ኃጢአታቸው በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ አልተዘረዘረም አልን እንጂ በሌሎቹ መጻሕፍት ውስጥ ግን ተዘርዝሯል። ለምሳሌ ነቢዩ ናሆም የነነዌ ኃጢአት ምን ምን እንደነበረ ገልጿል። እነዚህም፡-
፩ኛ ክፋትን ማሰብ
ክፋት፡- ለሰው ጉዳት የሚሆን ሁሉ ክፋት ይባላል፡፡ ክፋት በኃጢአት ምክንያት ወደ ዓለም ገባ፤ ሰው ኃጢአት ስለሠራ ፥እግዚአብሔር በሰው ላይ ፈርዶ ቅጣት ወሰነ፡፡ (ዮናስ ፫፥፲፣የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፻፺፭) በዚህም ክፋት በሥነ ምግባር ሰዎች በዕለት ተዕለት ኑሮዋቸው ውስጥ የሚያሳዩት ጠባይ ወይም ድርጊት አንድን ነገር ለመሥራትና ላለመሥራት የሚወስኑበት ሕሊናዊ ሚዛን ነው፡፡ በጎ ምግባር ክፉ የሆኑ ነገሮችን አስወግዶ ደግ የሆኑትን መምረጥ መሥራት ሲሆን በተቃራኒው ክፉ ምግባር ከበጎ ይልቅ ክፉ ነገሮችን መርጦ መሥራት ማለት ነው፡፡ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉና በጎን መለየት እንዲችሉ አስቀድሞ በሕገ ልቡና ከዚያም በሕገ ኦሪት በኋላም በሥጋ ተገልጦ የሰው ልጅ ሊኖር የሚገባውን ኑሮ ምሳሌ አርአያ ሆኖ አሳይቶናል፡፡
ክፉ የምንላቸው ነገሮች በሰው ልጅ ሥነ ተፈጥሮ ውስጥ ያልነበሩ ነገር ግን በበደል ምክንያት የክፉ ነገር ምንጭ የሆነ ዲያብሎስ ወደ ሰው ልጅ ሕይወት ያመጣችው ስስት፣ መግደል፣ ዝሙት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት “ክፋት” ሁለት ትርጉም ይዞ ይገኛል፤ አንደኛው ኃጢአት ማለት ሲሆን ሌላው ደግሞ ፈተናንና መከራን ያሳያል፤ ይህ ጥቅስ የተጠቀሰው (ክፋት) ትርጉሙ ኃጢአት ማድረግ ሳይሆን ፈተናንና መከራን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህም በጻድቁ ኢዮብ ታሪክ ላይ ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል፤ ኢዮብ ፈተና በወደቀበትና ሚስቱ ባጉረመረመች ወቅት እንዲህ ሲል ገሥጿት ነበር “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፣ ከእግዚአብሔር እጅ መልካምን ተቀበልን ክፉ ነገርስ አንቀበልምን?፡፡” (ኢዮብ ፪፥፲) ኢዮብ ከዚህ ላይ “ክፉ” ሲል መከራ ገጠመኝ ማለቱን እናያለን፡፡ የኢዮብ ሦስት ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት ከሀገራቸው መጡ” ይላል፡፡ (ኢዮብ ፪፥፲፩)
በተመሳሳይ ጌታ እግዚአብሔር ሲናገር “እነሆ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ ማለት ክፉ ነገር በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አመጣለው” ብሏል፡፡ (፪ኛ ዜና ፴፬፥፳፬) እርግጥ ነው እዚህ ላይ ጌታ ክፉ ነገር ሲል ኃጢአት ማለቱ አይደለም፤ በመከራ እንደሚቀጡ ግን ያሳያል፤ ሌላው አምላካችን እግዚአብሔር “እነሆ የሰማውን ሰው ጆሮ ጭው የሚያደርግ ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ አመጣለው” ብሎ የኤርምያስን ትንቢት ደግሞ ተናግሮታል፤ (ኤር.፲፱፥፫) እዚህ ላይ እግዚአብሔር “ክፉን” ወይም መከራን የሚያመጣው “ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት፣ በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ነው” (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፲፬) እንዲሁም ለሕዝቡ ከመከራው የተነሣ መንፈሳዊ ጥቅም እንዲያገኝ ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ ነው፡፡ (ያዕ.፩፥፪-፬)
በነነዌ ከተማ ባለ ሥልጣናት ምሳሌ ሆነው ንስሐውንና ሱባኤውን በመጀመርና በመምራት ሕዝባቸውንና ከተማቸውን ከእግዚአብሔር ቁጣ ባዳኑባት ሱባኤ ንስሐ ግቡባት፤ ዕድል አያምልጣችሁ፤ በእግዚአብሔር ስም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብላ ቤተክርስቲያናችን ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ታስተምራለች፡፡ በዚህም ምንም ያህል በደል ብትፈጽሙ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ አይክበዳችሁ፤ የምንበድለው አባታችን እግዚአብሔር ክፋታችንን እንጂ እኛን አይጠላም “ኑ ና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና” ተብሎ እንደተጻፈ። (ኢሳ.፩፥፲፰-፳)
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይቅርታ እንድናገኝ እንጂ ማናችንም ከእነ ኃጢአታችን እንድንጠፋ አይፈቅድምና አምላካችን እግዚአብሔር ወደ እርሱ እስክንቀርብ ዕድሜ ለንስሐ እየሰጠ ሁል ጊዜ እንደሚታገሠን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ሳለ ስለ እናንተ ይታገሣል፡፡” የእግዚአብሔርን ትዕግሥት በዚሁ እንደምንረዳ የሐዋርያው ቃል ያስተምረናል፡፡ አያይዞም በንስሐ ወደ እርሱ ለመቅረብ መፋጠን አንዳለብን “የጌታ ቀን ግን እንደሌባ ሆኖ ይመጣል” በማለት ፈጥነን ወደ ንስሓ መቅረብ እንዳለብን ይመክረናል፡፡ (፪ኛጴጥ.፫፥፱-፲)
፪ኛ በሰው ልጅ ላይ መጨከናቸው
መጨከን፣ ክፋት አለመራራት፣ አለማዘን፣ በመጣበት በደረሰበት መከራ አለመሰቀቅ የሚሉ ትርጉም ሲኖሩት የነነዌ ሰዎች ጨካኝ ባሕርያቸው የአራዊት ንጉሥ በሚባለው በአንበሳ ተመስሏል፤ “አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም ሰበረላቸው፤ ዋሻውን በንጥቂያ፥ መደቡንም በቅሚያ ሞልቶታል” ተብሎ በምሳሌ እንደተነገረው። (ናሆም ፪፥፲፪-፲፫)
በመሆኑም በነቢዩ ዮናስ ዘመን የነበሩት በእርሱም ስብከት አምነው እና ተጸጽተው ንስሐ ቢገቡም በንስሐ የሚገኙትን ልማት፣ በረከት፣ ጤና እና ሕይወት ክፋታቸው ሸፍኖባቸው እንደገና ወደዚሁ ከተማዋ እንድትገለበጥ ወደሚያደርስ ክፋታቸው በመመለሳቸው ነቢዩ ናሆም ተላከባቸው። ይሁንና በሰው ልጅ ላይ መጨከናቸው ለዘለዓለማዊ ሕይወት መንገድ ስለማይሰጣቸው እንዲህ ዓይነቱ ርኩሰት በንስሐ ካልተወገደና በዚህ ሁሉ ርኩሰት ፈንታ ጾምና ጸሎት፣ ፍቅርና ሰላም ፍትሕና ርትዕ እምነትና ምግባር ካልተተካ ድህነትና ስደት፣ ጦርነትና ሑከት፣ ደም መፍሰስና መናከስ፣ በሽታና አንበጣ፣ ሥቃይ መከራ ከምድር ላይ አይርቁም። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ሞትና ሕይወትን በእጃችን ሰጥቶናል፤ ንስሐ እንግባ።
፫ኛ ዝሙትና በመተት እንዲሁም ጣኦትን ማምለክ
ስለ ነነዌ ሸክም በሚለው በነቢዩ ናሆም መጽሐፍ “ስለ ተዋበችው ጋለሞታ ግልሙትና ብዛት ይህ ሆኖአል፤ እርስዋም በመተትዋ እጅግ በለጠች፥ አሕዛብንም በግልሙትናዋ፥ ወገኖችንም በመተትዋ ሸጠች” ተብሎ የተነገረውን አስተውሎ መረዳት ይችላል፡፡ (ናሆም ፫፥፬) በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደ ተገለጸው ዘማዊቷ በነነዌ ከተማ የፍቅር አምላክ እየተባለች ትመልክ ነበረ። የነነዌ ኃጢአቶች ከላይ የተዘረዘሩት ብቻ አልነበሩም፤ በንግድ አጭበርብሮ መብዝበዝና የመሳሰሉት ሁሉ እንደነበሩ በትንቢተ ናሆም ተገልጿል።
የነነዌ ኃጢአቶች በዘመናችን በየቤቱ፣ በየከተማው፣ በየሀገሩ፣ በየቤተ መንግሥቱ የማይሠራ የትኛው ነው? ክህደቱ፣ ደም ማፍሰሱ፣ ጭካኔው፣ በእግዚአብሔር ላይ ማሤሩም፣ ዝሙቱ፣ መተቱ፣ ጥንቆላው፣ ግፉ፣ በንግድ ማጭበርበሩ ሰማይ አልነካም ወይ? በእነዚህ ታላላቅ የነነዌ ኃጢአቶች ያልተበከለ ሀገርስ በዘመናችን ይኖር ይሆን? በየትኛው አህጉር ነው የሚገኘው? ዓለማችን አሁን እኮ ከእኛ የራቀች አይደለችም። በሀገራችን በኢትዮጵያ በእኛ ዘመን የሚታየው፣ የሚሰማው፣ የሚደረገው ከነነዌ ኃጢአት ቢከፋ እንጂ የሚሻል ቢባዛ እንጂ የሚያንስ አይደለም።
ስለዚህ የነነዌ ሰዎች ይህን ሁሉ በደል በበደሉ ሰዓት ያደረጉት ምንድን ነው?
፩ኛ ጾም መጾም፡- የነነዌ ሰዎች የመጀመሪያ ተግባራቸው ነው ያደረጉት ጾምን ነው፤ እነርሱም ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ” እንዳለን የነነዌ ሕዝቦች ስለ ምን ጾሙ? (ኢሳ. ፶፫፥፫) እኛም በዚህ ጾም እግዚአብሔርን የመፍራትና ፊትን ወደ እርሱ የማዞር ምልክትና የእግዚአብሔርን ገጸ ምሕረት መለመኛ መንገድ እንደሆነ በመረዳት ልክ እንደ እስራኤል ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ እግዚአብሔርን ከመተው እርሱን ወደ ማምለክ ፈታችንን በመመለስ ልንጾም ይገባል፡፡ “ኢዮሣፍጥም ፈራ፣ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና፣ በይሁዳም ሁሉ ጾም ዐወጀ” እንዲል። (፪ኛ ዜና ፳፥፫)
እንዲሁም ካህኑ ዕዝራ እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ምክንያት ተማርከው ባቢሎን ወርደው ሰባ ዓመት በኖሩበት ዘመን ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፣ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛ ለልጆቻችንና ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።” (ዕዝራ ፰፥፳፩፡) በዚያ በጾማቸው ስላገኙት ጥቅም ሲናገር ደግሞ “ስለዚህም ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔር ለመንን፤ እርሱም ተለመነን” በማለት ጾም እግዚአብሔርን መለመኛና ጸሎታችን እንዲሰማ የሚያደርግ መልካም መሣሪያ መሆኑን በተግባር ካገኙት ነገር በመነሣት መስክረዋል፤ የነነዌ ሕዝብም በነቢዩ ዮናስ አማካኝነት የሦስት ቀን ጾምን ዐውጀዋል፡፡
፪ኛ ኃጢአታቸውን እና ክፉ ተግባራቸውን መናዘዝ
ንስሐ ኀዘንን እና ችግርን ለእግዚአብሔር መንገሪያና ጭንቀታችንን ሁሉ የምናስወግድብት መንገድ መሆኑን በመረዳት ኃጢአታችንን መናዘዝ ይገባል፡፡ የኢየሩሳሌም ከተማ ቤተ መቅደሷ ፈርሶ፣ ቅጥሮቿ ሁሉ ተቃጥለውና ጠፍተው ስለ ነበር ነህምያ ያን ባሰበ ጊዜ በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ኀዘኑን ገለጸ፤ እንዲህ ሲል፡- “ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፤ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር” (ነህ. ፩፥፬) በጾምና በጸሎትም እግዚአብሔር ለነህምያ በማረካቸው ንጉሥ ፊት ሞገስን ሰጠው፤ ንጉሡም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ቅጥሮቿን እንደገና እንዲሠራ ፈቃድ ሰጠው (ነህ. ፪)፡፡
ልበ አምላክ የተባለ ዳዊትም “እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት” እንደዚሁም “ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፤ ለስድብም ሆነብኝ” በማለት ስለ ሌሎች ወገኖቻችን ችግር መጾም ተገቢ መሆኑን፣ እንዲሁም ጾም ማለት ሰውነት እስኪደክምና ረኃብ እስኪሰማው ድረስ ከእህልና ከውኃ መከልከል መሆኑን ይናገራል፡፡ (መዝ.፴፬፥፲፫፡) እንዲሁም (መዝ ፷፰፥፲)
ነቢዩ ኢዩኤልም “ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ” በማለት ጾም የሚታወጅ መሆኑን እና ወደ እግዚአብሔር መጮኺያ መንገድ መሆኑን ተናግሯል፡፡ (ኢዮ.፩፥፲፬)
ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔርም በጾም ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር፣ በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። በጽዮን መለከትን ንፉ፣ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም ዐውጁ” በማለት ነግሮናል፡፡ (ኢዩ. ፪፥፲፪) የነነዌ ሕዝቦችም ክፋትን በልቦናቸው በማሰብ በመተግበርም፣ በሰው ልጅ ላይ የጭካኔ በትራቸውን በማንሣታቸው የሰው ልጅን አብዝተው በማሠቃየታቸው በዚህም ክፉ ተግባራቸው ዝሙትን እንደ መልካም ተግባር በመቁጠር እና በሰው ላይ መተት፣ ጥንቆላ በማድረግና ጣዖትን በማምለክ ተጠምደው ስለነበር ወደ እነርሱ በተላከው በነቢዩ ዩናስ አማካኝነት ብሔራዊ ጾም ዐወጁ። ጥፋተኝነታቸውንም አመኑ፤ ከልብ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ወሰኑ። ከንጉሥ እስከ ሎሌ፣ ከሕፃን እስከ አዛውንት እንስሳትም ጭምር እንዲጾሙ ማቅ እንዲለብሱ ብሔራዊ የጾም ዐዋጅ ዐወጁ።
፫ኛ መልካም ትውልድ ለማፍራት መጣራቸው፡- እግዚአብሔር ምን ዓይነት ጾም እንደሚያስደስተውና በዚያ መንገድ ብንጾም ምን በረከትና ጥቅም እንደምናገኝ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- “እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፤ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፤ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹን፣ ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? (ኢሳ.፶፰፥፮-፲፬)
የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ፤ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ፤ እርሱም፡- እነሆኝ ይላል፡፡ … ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል፤ ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል፡፡” እግዚአብሔርም ሁል ጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል፤ አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፤ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። …” የእግዚአብሔር አፍ ተናግሯልና። (ኢሳ.፶፰፥፮-፲፬)
እግዚአብሔር አምላካችን “ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፤ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል” በማለት በግልጽ እንደ ተናገረው ያለፉ ስሕተቶቻችንና በሀገርና በወገን ላይ ያሳደሯቸው አሉታዊ ጠባሳዎች ያፈረሷቸው ስፍራዎችና መልካም ነገሮች ሁሉ የሚጠገኑትና ተመልሰው የሚሠሩት በጾም ነው፡፡ ያለፈው ብቻ ሳይሆን የሚመጣው ትውልድም በጥሩ መሠረት ላይ የሚመሠረተው እንዲሁ በጾም ነው፡፡
ከዚህም ጋር በአግባቡ የሚጸመውን ሰው “አንተም ሰባራውን ጠጋኝ ትባላለህ” እንደተባለ ጾም የተሰበረው የሚጠገንበት ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የስብራት መጠገን ሲባል ደግሞ በዋናነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በኃጢአት ምክንያት ተሰብሮ ከነበረ የሚጠገንበት መንገድ ጾም መሆኑን ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነገረን፡፡ በዚህ ተግባራቸው እስራኤላውያን የጾምን ጥቅም በመገንዘብ እና ጾም የመልካም ነገር ዋዜማና መጥቅዕ ስለ መሆኑ በመረዳት እግዚአብሔር ያለውን ተረድተውበታል። ምክንያቱም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም፣ የሰባተኛውም፣ የዐሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ፣ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፡። ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ።” እንደተባለ። (ዘካ.፰፥፲፱)
በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሕዝቦችና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል ያለው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለበት ወቅት እኛም ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ” ብሎ አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ነው፡፡ እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን ጸልየን ከኃጢአታችን እንድንነጻ ነው፡፡ ብንጾም ራሳችን፣ ሀገራችንን፣ ዕፅዋቱንና እንስሳቱም ሳይቀር በእኛ በደል ምክንያት በድርቅ በቸነፈር እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነውና በብዙ ፈተና ውስጥ የምትገኘውን ሀገራችን ኢትዮጵያን፣ እኛን ሕዝቦቿን ይጠብቀን!