‹‹ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሺ፥ ተመለሺ›› (መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን ፯፥፩)

ክፍል ሁለት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ጥቅምት ፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

እሾህ በተባለ ጥንተ አብሶ አዳማዊና ሔዋናዊ ኃጢአት መካከል ያበበች የፍሬ ሕይወት ክርስቶስ መገኛ አማናዊት የሃይማኖት አበባ እመቤታችን በዚህ በአበባው ወቅት (በጽጌ ወራት) መራራው የጣፈጠበት፥ ፍሬ ሕይወት ልጇን እንዳይገሉባት መራራውን የስደት ሕይወት የተጋፈጠችበት መታሰቢያ ወቅት ነው፡፡

ምክንያተ ስደት፡- ጌታችን በተወለደ ጊዜ ቤተ ልሔም በእሳት ተቀጽራ አጋንንት ሊቀርቧት፣ ሊወጡባት ሊወርዱባት አልቻሉም፡፡ ለአለቃቸው ነግረውት እርሱም እንደ ጌታ እሆናለሁ ብሎ በኪሩቤል አምሳል አራት ጸወርተ መንበር አዘጋጅቶ በእነርሱ ላይ ሆኖ ቢወርድ መላእክት በሐጸ እሳት እየነደፉ አላስቀርብ አሉት፡፡ በዚህም ክርስቶስ እንደ ተወለደ አስቦ ለሄሮድስ “የእኔን ሥልጣን የአንተን መንግሥት የሚነጥቅ ንጉሥ ተወልዷልና ልብስ እቀዳለሁ/እሰጣለሁ፤ ቀለብ እሰፍራለሁ ብለህ ዓመት፣ ዓመት ከመንፈቅ፣ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ሕፃናት ሰብሰቡልኝ ብለህ ፍጃቸው፤ ከእነዚያ መካከል አንዱ ይሆናል” ብሎ ላከበት፡፡

በዚህ ጊዜ መልአኩ ዮሴፍን ‹‹ንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወጕየይ ውስተ ብሔረ ግብፅ›› ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ” ብሎት ወጥተው ሄደዋል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፫) ሄሮድስም ዐዋጅ አስነግሮ ያላቸው ልጆቻቸውን፣ የሌላቸው ልጅ ተውሰው ልብስ ቀለብ ሊቀበሉ የተሰበሰቡ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናት አስፈጅቷል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፮) እነዚህም ሕፃናት በዘመነ ሐዲስ በኩራት ሆነው ደማቸውን በማፍሰስ ሰማዕት የሆኑ ናቸው፡፡ (ራእየ ዮሐንስ የዓለም መጨረሻ እና ትርጓሜ ሠለስቱ ሐዲሳት) ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ወደ ግብፅ መሸሻቸውን ቢነግሩት “አራት ቤት ጭፍራ ሸልሞ ይዛችሁ ያመጣችሁልኝ እንደሆነ ሙሉ ሽልማት እሸልማችኋለሁ” ብሎ ልኳቸዋል፡፡ እነ እመቤታችንም ከጊጋር መስፍነ ሶርያ ቤት ሰንብተው ስደታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ታሞ ወደ ኋላ ቀርቶ ነበርና ጭፍራ እንደተከተላቸው የጊጋር ብላቴኖች ሲነጋገሩ ሰምቶ ወጥቶ እየሮጠ ሲሄድ ሰይጣን መንገድ ላይ ጠበቀና ‹‹ምንት ያረውጸከ ከመዝ›› ምን ያስሮጥሀል? አለው፡፡ ሄሮድስ “ዘመዶቸን ያዙ ብሎ ጭፍራ ሰደደ ቢሉኝ ይህን ልነግራቸው ብዩ ነው” አለው፡፡ ያዘነ መስሎ “እነርሱማ ቀድመውህ ሄደዋል እስከ አሁን ገድለዋቸው ይሆናልና አትድከም ተመለስ” አለው፡፡ከሞቱም እቀብራቸዋለሁ ካሉም እነግራቸዋለሁ ብሎ ትቶት ሮጠ፡፡ (መዝገበ ታሪክ ቁጥር አንድ)

እመቤታችንና ዮሴፍ ደክሟቸው ዐረፍ ብለው ሰሎሜ ጌታን ስታጥበው አግኝቷቸው “እናንተ ሄሮድስ ይዛችሁ አምጡልኝ ብሎ ጭፍራ ልኮ ከዚህ ተቀምጣችኋል?” አላቸው፡፡ እመቤታችን ደንግጣ ጌታን ከሰሎሜ ተቀብላ እንባዋ በፊቱ ላይ እስኪወርድ ድረስ አለቀሰች፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስ ‹‹አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኅዘ እምአዕይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ›› የሚለው ይህን ነው፡፡

ጌታም ዮሳን “አመጣጥህ መልካም ዋጋ የሚያሰጥ ነበር፤ ነገረ ግን እናቴን ስላስደነገጥካት በዳግም ምጽአቴ አስነሥቼ ዋጋህን እስክከፍልህ ድረስ ይህን ድንጋይ ተንተርሰህ ተኛ” ብሎት ከዚያው ድንጋይ ተንተርሶ ድንጋይ መስሎ ቀርቷል፡፡

ከዚህ በኋላ ተነሥተው ሲሄዱ የሄሮድስ ጭፍሮች ገስግሰው ደረሱባቸው፡፡ አንዲት የሾላ ዛፍ ተከፍታ ከነጓዛቸው ከእነ አህዮቻቸው ሰውራቸዋለች፡፡ እነዚያም አህዮች ከውስጥ ሆነው ሲያናፉ ድምፃቸውን እየሰሙ ነገር ግን ሊያገኟቸው ስላልቻሉ የሄሮድስ ጭፍሮች ተመልሰዋል፡፡ ከዚያ ወጥተው መንገዳቸውን ሲጓዙ በደረሱባት ሀገር በአደባባዮቿ ሲሄዱም ግመሎች መጡ፡፡ በመንገድም አስቸገሯቸው፤ ጌታም አያቸውና ቁሙ አላቸው፡፡ አምስቱም እስከ አሁን ድንጋይ ሆነው አሉ፡፡ (ድርሳነ ማርያም)

እመቤታችንና ልጇ መንገዳቸውን በእግዚአብሔር መልአክ እየተመሩ፣ የሲናን በረሃ አቋርጠው ወደ ግብፅ ሀገር ሄዱ። በዚያን ሰዓት ውርጩ፣ ብርዱ፣ ረኃቡ፣ እንግልቱ በዝቶባቸው ነበር፤ ጉዞውም አስጨናቂ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር የደረሰባት እንግልት፣ ሥቃይ፣ ረኃብ፣ ጥምን ሁሉ በሰው አንደበት የማይገለጽ እጅግ መራራ እንደ ነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

አባታችን ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ‹‹አዘክሪ ድንግል ረኃበ ወጽምአ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኩሎ አጸባ ዘበጽሃኪ ምስሌሁ አንዘ ትጎይዪ ምስሌሁ እምሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ርጉም፤ ድንግል ሆይ፥ ርጉም በሆነ በሄሮድስ ዘመን ከእርሱ ጋር ከሀገር ወደ ሀገር ስትሸሺ ረኃቡንና ጥሙን ችግሩንና ኀዘኑን ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ›› በማለት ገልጾታል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም)

ስደት መከራንና ሥቃይን መቀበል ነው፡፡ ነቢያት፣ በኋላም ሐዋርያት ቅዱሳን ተሰደዋል፤ ‹‹እውነተኞች ምንጊዜም ስደት አለባቸውና›› (፪ኛጢሞ.፫፥፲፪) የክርስቶስ የሆኑ ሁሉ ይሰደዳሉ፤ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ያሳድዳቸዋል፡፡ እመቤታችንም የክርስቶስ ናትና እውነትና የእውነት መገኛ ራሷም እውነት ናትና ስደትን ተሰደደች፤ በስደቷም ብዙ መከራ አገኛት፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ አንባብያን! የልጇ ፈቃድ ቢሆን የእርሷም ምልጃዋ ቢረዳን እመቤታችን ከኢየሩሳሌም ተነሥታ እስከ ምድረ ግብፅ ስትጓዝ የደረሱባት ዋና ዋና ችግሮችና የተደረጉ ተአምራትን በክፍል ሦስት ይዘንላችሁ እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት፡፡

ይቆየን!