ሰባቱ ኪዳናት

ክፍል ሦስት

ኪዳነ አብርሃም

መጽሐፍ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳንም ሆነ በብሉይ ኪዳን አብዝቶ ከሚዘክራቸው ቅዱሳን እንደ አባታችን አብርሃም የሚሆን የለም፡፡ ከታራም ትውልድ የተወለደው ቅዱሱ አባት በሥነ ፍጥረት ምርምር አምላኩን ያወቀ ጥበበኛ ሰው ነው፡፡ በኋላም የሕዝብና የአሕዛብ አባት፣ ሥርወ ሃይማኖት፣ የጽድቅም አበጋዝ ለመባል በቅቷል::

በፈቃደና በትእዛዘ እግዚአብሔር አብርሃም ከአባቱ ወገኖችና ከዘመዶቹ ተለይቶ ሀገሩን ትቶ በመውጣት አምላኩን ሲያገለግሎ ኖሯል፡፡ በዚህም ጊዜ ፈጣሪ እንዲህ አለው፤ ‹‹ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፡።›› (ዘፍ.፲፪፥፩-፪)

ከሚስቱ ሣራ ጋር በከነዓን ምድር በቅድስና ሕይወት ሲኖርም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጸመ፡፡ ስለዚህም አምላካችን እግዚአብሔር ተገለጠለትና እንዲህ በማለት ቃል ኪዳን ገባለት፤ ‹‹እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ አምላክም እሆናቸዋለሁ።›› (ዘፍ.፲፯፥፫-፰)

ዳግምም እግዚአብሔር ለአብርሃም እንዲህ አለው፤ ‹‹አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆናል። የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።›› (ዘፍ.፲፯፥፱-፲፬) በዚህም አምላካችን ለአባታችን አብርሃም ግዝረት የቃል ኪዳን ምልክት እንዲሆነው ሰጥቶታል::

ኪዳነ ሙሴ

ሊቀ ነቢያት ሙሴ በውልደቱ ጊዜ በእግዚአብሔር ድንቅ ተአምር የእስራኤላውያን ወንድ ልጆች በመወለዳቸው ወቅት እንዲገደሉ ከወጣው ዐዋጅ መትረፍ የቻለ፣ በፈርዖን ቤት በእናቱ እጅ ያደገ፣ በኋላም በእግዚአብሔር ጥሪ በቅድስና ከመኖርም አልፎ እስራኤላውያንን በአምላክ ኃይል ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ወደ ምድር ርስት መርቶ ያስገባ ታላቅ ነቢይ እንደ ሆነ ቅዱሱ መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ ሙሴ የነቢያት አለቃ፣ የእስራኤል እረኛ፣ የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነበር::

ነቢዩ ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ ለ፵ ዘመናት በበረኃ በመራበት ወቅት ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና ዐሥርቱን ትእዛዛት ተቀብሏል:: በዚህም ጊዜ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት ተናገረው፤ ‹‹ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፣ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።

የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና። የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ ወንድ ልጅህም፣ ሴት ልጅህም፣ ሎሌህም፣ ገረድህም፣ ከብትህም፣ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።

አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፤ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም፣ ገረዱንም፣ በሬውንም፣ አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።›› (ዘፀ.፳፥፩-፲፯)

ነቢዩ ሙሴ ከአምላክ ጋር በተደጋጋሚ ፊት ለፊት የተነጋገረ ነቢይ መሆኑን ቅዱሳት መጽሐፍት ይገልጻሉ፡፡ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ከሙሴ ጋር መነጋገርን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጥቶታል። (ዘፀ.፴፩፥፲፰) በዚህ የኪዳን ቃል የሰው ዘር ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆና በትእዛዙ በመኖር መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ የአምላክ ፈቃዱ ነው፡፡ በነቢዩ ሙሴ በኩል የተሰጠን ትእዛዘ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳንም (በዘመነ ሐዲስም) ልንተገብረው የሚገባ መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡

ኪዳነ ዳዊት

ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት ውልደቱ ከኤፍራታዊው ሰው ከእሰይ ዘር የሆነ፣ በብላቴናነት ዕድሜው በእረኝነት መስክ ተሰማርቶ በነበረበት ጊዜ ከሰባቱ ወንድሞች መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ ለንግሥና የተመረጠ፣ ኃያል ጦረኛና ጥበበኛ ንጉሥ መሆን የቻለ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለበርካታ አገልግሎት የምትጠቀምበትን ፻፶ መዝሙራትን የደረሰ የአምላክ ባለሟል ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት፣ ጻድቅ፣ የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው:: አምላካችን እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ ካደረገው በኋላ ‹‹ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ›› በማለት ቃል ገብቶለታል:: (መዝ.፻፴፩፥፲፩) ፈጣሪያችን ይህን ቃል ኪዳን ‹‹ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ›› በማለትም በመሐላ አጽንቶታል፡፡ (መዝ.፹፰፥፴፭)

እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ፣ ለድንነት ዓለም ወደዚህች ምድር እንደሚመጣና ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ የመወለዱን ነገር አስቀድሞ አምላክችን ለነቢዩ ዳዊት ከዘሩ እንደሚወለድ ሲነግረውም ቃሉ ይፈጸም ዘንድ እንደወደደ ቅዱስ ኤፍሬም በኀሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ጽፎት እናገኘዋለን፤ ‹‹ጻድቅ እርሱ ዳዊት ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ማደሪያ ፈልጎ ያገኝ ዘንድ ወደደ፡፡ ይህንንም በታላቅ ትጋት ፈጸመ፡፡ ከዚህ በኋላ “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው” ብሎ በመንፈስ ቅዱስ አሰምቶ ተናገረ፡፡ ይህችም አማኑኤል እኛን ለማዳን በሥጋ ይወለድባት ዘንድ የመረጣት የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ናት›› እንዲል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከኃጢአት ባርነትና ከጠላት ቁራኝነት ነጻ ለማውጣት ሲል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ መከራንና ሥቃይን የተቀበለው እንዲሁም በመልዕልተ መስቀል የተሰቀለው ከሰው በነሣው ሥጋ ሲሆን ነቢዩ ዳዊት ለዚህ ታላቅ ክብር በመመረጡ ደስታው እጅግ የበዛና የተገባ እንደ ነበር ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ገልጾታል፡፡ እኛም የሐዲስ ኪዳን ምእመናን አምላካችን ለሰዎች ድኅነት ያደረገልንን ሁሉ እያሳብን ሐሴት ልናደርግ እንዲሁም በመሠረትልን የእውነት መንገድ ልንጓዝ ይገባል፡፡

ይቆየን!