ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ክፍል አራት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ጳጉሜን ፩፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ምሥጢረ ክህነት እና ተክሊል

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? በዕረፍት ጊዜያችሁ ምን እየሠራችሁ ነው? ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር እንዲሁም ደግሞ ለዘመናዊ ትምህርታችሁ አንዳንድ ማጠናከሪያ የሆኑ ትምህርቶችን በመማር እያሳለፋችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን! ምክንያቱም በጨዋታ ብቻ ማሳለፍ የለብንም!

እንግዲህ አዲሱን ዘመን ልንቀበል በዝግጅት ላይ ነን! ባለፈው የቡሄ ዕለት ወንዶች ልጆች ዝማሬን እየዘመሩ በዓሉን እንዳከበሩት አሁን ደግሞ ተራው የእኅቶቻችን ነው! አበባ አየሽ ሆይ እያልን የፈጣሪያችንን ድንቅ ሥራ የሚገልጡ ዝማሬዎችን እየዘመራችሁ በዓሉን ለማክበር እየተዘጋጃችሁ ነው አይደል? በርቱ!

ታዲያ በአዲስ ዓመት በሚጀመረው ትምህርት በርትታችሁ ለመማር ዝግጅት ማደረጉንም እንዳንረሳ፤ ሌላው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን መሄድን መንፈሳዊ ትምህርትን መማርን መቀጠል አለባችሁ፤ ባለፈው ትምህርታችን ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የነፍስና የሥጋን ቁስል (ሕመም) የሚፈውሱ ስለሆኑት ምሥጢረ ንስሐ እና ምሥጢረ ቀንዲል ተምረን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የአንድነትና የአገልግሎት ጸጋን ስለሚያሰጡን ሁለት ምሥጢራት እንማራለን፤ መልካም!

ምሥጢረ ክህነት

«ካህን» የሚለው ቃል በቁሙ ሲተረጎም “ጳጳስ ፣ ቄስ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ የሕዝብ መሪ፣ አስተማሪ ፡ መንፈሳዊ አባት” ማለት ነው፡፡ ክህነት የሚለው ደግሞ «ተክህነ» ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ካህንነት፣ ተክኖ ማገልገልን፣ መንፈሳዊ ሹመት መቀበልን ያመለክታል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፭፻፳፪)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካህናት የሚባሉት “የማሠር ፣ የመፍታት ፣ የመባረክ ፣የማጥመቅ፣ የማስተማር፣ ሥጋ ወደሙን የማቀበል” ሥልጣን ያላቸውን አባቶቻችንን ነው፡፡ ምሥጢረ ክህነትን ምሥጢር ያሰኘው በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋን ስለሚያሰጥ ነው፡፡ የሚታይ አገልግሎት የሚባለው ጳጳሱ ካሀኑን በአንብሮተ ዕድ ሲሾም፣ ለክህነት የሚያበቃው የተለየ የቡራኬ ጸሎት ሲጸልይ የሚታየው ሲሆን የማይታይ ሀብት የሚባለው ሥልጣነ ክህነት፣ የማሠር፣ የመፍታት፣ የማንጻትና የማዳን ሥልጣን ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለቅዱስ ጤሞቴዎስ በላከው መልእክቱ ‹‹…እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል›› በማለት እንደገለጸው ሥልጣነ ክህነትን የሚሰጡ አባች ጳጳሳት እጃቸውን ሥልጣነ ክህነት በሚቀበለው ሲጭኑ ይታያል የሥልጣን ጸጋው ሲሰጥ ግን አይታይም፡፡ (፩ኛ ጢሞ.፬-፲፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ካህን ማለት ምን ማት እንደሆነ ተገነዘብን አይደል! እንግዲህ የክህነት አገልግሎት መቼ ተጀመረ ቢባል የመጀመሪያው ካህን አባታችን በአዳም ነው:: እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በልጅነት አክብሮ ነቢይ፣ ካህን አድርጎ ስለሾመው መሥዋዕት ሲያቀርብ ኖሯል፡፡ ከእርሱ በኋላም የተነሡ አባተቶቻችን ክህነትን ከአባቶቻቸው በቡራኬ እየተቀበሉ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር፤ እንደ ምሳሌ ብንመለከት «ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ከንጹሕ እንሰሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፤ በመሠዊያውም ሳይ መሥዋዕትን አቀረበ፤ እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፡፡» (ዘፍ.፰፥፳)

ሌሎችም አባቶቻችን መሥዋዕትን ይሠው ነበር፤ ከዚያም ልጆች ከብዙ ዘመን በኋላ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተባለው አባታችን በነበረበት ዘመን እግዚአብሔር ሌዊ ከሚባለው ወገን ካህን ሆነው እንዲያገለግሉኝ መርጫለውና ሹምልኝ አለው፤ እግዚአብሔር ሙሴን «ወንድምህን አሮንንና ልጆቹን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ» በማለት ካዘዘው በኋላ. እንዴት አድርጎ ሥልጣነ ክህነትንም እንደሚሰጣቸው ሥርዓቱን ገልጾታል፡፡ (ዘጸ.፳፰፥፩፣ ፴፱፥፩- ፴፯)

ሊቀ ነቢያት ሙሴም አሮን የተባለውን አባትና ልጆቹን ክህነት ሰጣቸው፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ካህናት በቤተመቅደስ እግዚአብሔርን ማገልገል ጀመሩ፤ ሕዝቡ ለቤተ እግዚአብሔር መባዕ (ስጦታ) ሲያመጣ እየተቀበሉ ይሰው ነበር፤ ያስተምሩ፣ ይመክሩ፣ ይገሥጹ ነበር፤ (ዘጸ. ፴፱፥፲፪) ካህናቱ ዕጣን ማጠን፣መሥዋዕቱን ተቀብሎ መሠዋት፣የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ለሕዝቡ ማሰማትና ማስተማር፣ በሰዎች መካከልም ጠብ ፣ ክርክር ሲነሣ ፍርድ መስጠት/ማስታረቅ፣ ሕዝቡን መምራት አገልግሎትን ያከናውኑ ነበር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ይህ ሥልጣነ ክህነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እኛን ለማዳን ከተወለደ በኋላም ቀጥሏል፤ ጌታችን ፲፪ ሐዋርያት መርጦ ሥልጣነ ክህነትን ሰጣቸው፡፡ ‹‹…እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፳፪፥፳)

ቅዱሳን ሐዋርያትም ለተከታዮቻቸው በአንብሮተ ዕድና በንፍሐት እያስተላለፉ እስከ ዛሬ የክህነት አገልግሎት ቆይቷል ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ (የሐዋ.፮፥፫፣ ፲፬-፳፫፣ ፩ኛጢሞ.፫፥፩-፲፫፣፬-፲፬፣ ፪ኛ ጢሞ.፩፥፮፣ ቲቶ ፩፥፭)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በአዲስ ኪዳን ያሉ አባቶቻችን ካህናት እግዚአብሔርንና ሰውን ለማገልገል ማለት ሰማያውያን መላእክትን መስለው ሌሊት በሰዓታት በማኅሌት፣ ሲነጋ በኪዳን፣ በቅዳሴ እግዚአብሔርን ያገለግላሉ፤ ያመሰግናሉ፤ በጥምቀት ልጅነትን በማሰጠት፣ የምእመናንን ኃጢአትን በማሥተሰረይ፣ የሕይወትን ቃል በማስተማር፣ ከደዌ ሥጋና ከአጋንንት በመፈወስ፣ ሥጋ ወደሙን ለምእመናን ያቀብላሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሢመተ ክህነት ሦስት ደረጃዎች አሉት፤ እነርሱም፡- ዲቁና፣ ቅስና፣ ጵጵስና ከዚህ በላይ ሊቀ ጳጳስና ፓትርያርክ አለ፡፡ ካህናት ማዕርጋቸው እንደ ሐዋርያት የማሠር፣ የመፍታት፣ ሰባቱን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመፈጸም፣ የማክበርና የማስከበር፣ የመቀደስና የማቁረብ ሥልጣንና ጸጋ አላቸው፡: (ፍት.ነገሥ. አንቀጽ አምስት፣ ገጽ ፹፭-፹፱ ፣ አንቀጽ ስድስት፣ ገጽ ፻፱፣ አንቀጽ ሰባት፣ ገጽ ፻፲፱)

ምሥጢረ ተክሊል

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው የአንድነትን ጸጋ የሚያሰጥ ምሥጢር የተባለው ምሥጢረ ተክሊል ነው፤ ተክሊል ማለት “ከለለ፣ አከበረ” ካለው ግሥ የወጣ ቃል ነው፤ ትርጉሙም ክብር ማለት ነው፡፡ ሥርዓተ ተክሊል የጋብቻ ሥርዓት የሚፈጸምበት ካህናት ሙሽራውንና ሙሽራይቱን አንድ የሚያደርጉብት ትእዛዘ እግዚአብሔርን የሚያፀኑበት ሥርዓት ነው፡፡

ምሥጢር መባሉ ደግሞ ለሙሽሮቹ ጸሎተ ተክሊል ተደግሞላቸው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ጌታችንም በትምህርቱ ‹‹ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ» በማለት እንዳስተማረው፤ ሥርዓተ ተክሊሉ ደርሶ ቅዳሴ ተቀድሶ ሲቆርቡ አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ (ኤፌ.፭፥፴፩) ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው» በማለት የጋብቻ ምሥጢር ታላቅ መሆኑን አስረድቶናል፡: (ኤፌ.፭፥፫-፴፪)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጋብቻን የመሠረተው ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ጋብቻ ከሕግጋተ እግዚአብሔር አንዱ ነው። ስለጋ ብቻ በኦሪትም በወንጌልም ሕግ ተሠርቶአል፤ በንጽሕና በድንግልና ሊኖሩ እግዚአብሔር ከፈቀደላቸው ሰዎች በቀር ሁሉም በጋብቻ እንዲኖሩ ጌታ አስተምሮአል፡፡

ጋብቻን እግዚአብሔር እንደ መሠረተው «እግዚአብሔር አምላክም አለ፤ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ ረዳት እንፍጠርለት» ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ዘፍ.፪፥፲፰) ሥርዓተ ተክሊል የሚፈጸምላቸው ሙሽሮች በሥርዓት አድገው ከጋብቻ በፊት ድንግልናቸውን ጠብቀው ለኖሩት ነው፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ልጅ ይወልዳሉ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሙሽሮች የጋብቻቸው ዕለት ነጭ ልበስ ለብሰው በቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ፤ ከዚያም ሥርዓተ ጸሎቱ ይደርስላቸዋል፤ ካባውን ይደርባሉ፤ አክሊል ይደፋሉ (በራሳቸው ላይ ይጫንላቸዋል)፤ ቀለበትም ያደርጋሉ፤ ቅዳሴው ተቀድሶ ይቆርባሉ፤ ስለ ክብራቸው ዝማሬ ይዘመራል፤ ለዚህ ያደረሳቸው እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ እንግዲህ ሰፊ ከሆነው ትምህርት ለእናንተ በሚመጥን መልኩ በአጭሩ አቀረብንላችሁ፤ ወደፊት ደግሞ በስፋት ትማሩታላችሁ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ምሥጢራት የአንድነትና የአገልግሎት ጸጋን የሚያሰጡ ናቸው፤ ወንዶች የሆንን የአብነት ትምህርት በመማር ዲያቆን ከዚያም ቄስ ወይም ደግሞ ጳጳስ መሆን እንችላለን፤ በሥርዓት አድገን ለዚህ ክብር ለመብቃት ከአሁኑ ጠንክረን መማር አለብን፤ በእምነት ጸንተን በምግባር ጎልብተን ሥርዐትን ጠብቀን (አክብረን) በመገኘት የክብር መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ ያድረገን! አሜን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!