ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ክፍል ሦስት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ነሐሴ ፳፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ምሥጢረ ንስሐና ቀንዲል

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ጾመ ፍልሰታን እንዴት አሳለፋችሁ? ከሕፃን እስከ አዋቂ በአንድነት የሚጾሙት ጾመ ፍልሰታ እንግዴት አበቃ! ሁላችሁም እንደ ዓቅማችሁ በመጾም ስታስቀድሱ እንደ ነበር እናምናለን፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ትንሣኤዋን እና ዕርገቷን እንዲመለከቱ ሱባኤ በገቡ ጊዜ እንደባረከቻቸው እኛንም ዛሬ ትባርከናለች፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዓመቱ እየተገባደደ ነው፤ በአዲስ ዓመት በሚጀመረው ትምህርት በርትታችሁ ለመማር  ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው? ታዲያ በክረምቱ ሰ/ት/ቤት በመሄድ እንማር፤ እንዘምር እንደነበር፣ ትምህርት ሲከፈትም በዕረፍት ቀናችሁ ቤተ ክርስቲያን መሄድን፣ መንፈሳዊ ትምህርትን መማርን መቀጠል አለባችሁ፤ ባለፈው ትምህርታችን ከሰባቱ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የልጅነት ጸጋን አዲስ ሕይወትን የሚያሰጡ ምሥጢራት የሚባሉትን ምሥጢረ ጥምቀት፣ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን ተመልክተናል፤ ዛሬ ደግሞ የነፍስና የሥጋ ቁስልን (ሕመም) የሚፈውሱ ስለሆኑት ምሥጢረ ንስሐ እና ምሥጢረ ቀንዲል እንማራለን፤ መልካም!

ንስሐ የሚለውን በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ሲገልጸው “ኀዘን፣ ጸጸት፣ ቁጭት ምላሽ መቀጮ ቅጣት፣ ቀኖና፣ የኃጢአት ካሣ” በማለት ያብራራዋል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፮፻፶፮) ምሥጢረ ንስሐ አንድ ሰው ከጥምቀት (ልጅነትን) ካገኘ በኋላ የፈጸመውን ጥፋት ላለመድገም ወስኖ፣ በእግዚአብሔርና በካህኑ ፊት ተንበርክኮ ፣ከልቡ ተጸጽቶ ኃጢአቱን በመናዘዝ ከኃጢአቱ እስራት የሚፈታበት፣ ከእግዚአብሔር ይቅርታ የሚያገኝበት ታላቅ የጸጋ ምሥጢር ነው፡፡ (ትምህርተ ሃይማትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፣ ገጽ ፪፻፷፯)

ሰው ንስሐ የሚገባው ኃጢአት ሲሠራ ነው፤ ኃጢአት ማለት ከጽድቅ ሥራ መራቅ፣ አድርጉ የተባለውን አለማድረግ ነው፤ እንዲሁም አታድርጉ የተባለውን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ስንፈጽም ነፍሳችን ትታመማች (ትቆስላለች)፤ ኃጢአት መሥራት ሕግ መተላለፍ፣ ትእዛዝ አለማክበር ለብዙ መከራ ይዳርጋል፤ ከእግዚአብሔር ያርቀናል፤ ልጅነታችንን ያስነጥቀናል፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው…›› እንዳለ፡፡ ( ዮሐ.፰፥፴፬)

ቅዱስ ጳውሎስም ለገላቲያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ…›› በማለት እንደገለጸው ኃጢአት ስንሠራ ልጅነትን አጥተን በባርነት እንያዛለን፤ ( ገላ.፭፥፩) ታዲያ በኃጢአት ስንወድቅ ዳግመኛ የምንነሣው፣ክብራችንን የምናስመልሰው በንስሐ ነው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ምሥጢረ ንስሐን የመሠረተልን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ነው፡፡ ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃሁ፤ በምድርም የምታስረስው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል›› በማለት ሰዎችን ከኃጢአት ማሰሪያ የሚፈቱበትን ሥልጣነ ክህነት ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡ (ማቴ.፲፱፥፲፱) ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹…ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል…›› ብሏል፡፡ (ምሳ.፳፰፥፲፫) ምሕረትን ለማግኘት፣ የነፍሳችንን ቁስል ለመፈወስ ንስሐ እንገባለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ምሕረትን ለማግኘት ንስሐ ስንገባ መሐሪ የሆነ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል፤ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹…ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፤ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው …›› ብሎናል፡፡ ( ፩ኛዮሐ.፩፥፰) አምላካችን ንስሐ ስንገባ ይቅር ይለናል፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማራቸው ጊዜ ልባቸው በትምህርቱ ሲማረክ ምን እናድርግ ብለው ሲጠይቁት ‹‹…ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ…›› አላቸው፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፮፥፴፰)

እንግዲህ ኃጢአቱን አምኖ ንስሐ የሚገባ ሰው ሦስት ነገሮችን ይፈጽማል፤ ኀዘን፣ ኑዛዜ፣ ቀኖና ምን ማለት መሰላችሁ አንድ ንስሐ የሚገባ ሰው መጀመሪያ ኃጢአቱን ያስታውሳል፤ ሰውና እግዚአብሔርን መበደሉን አምኖ ያዝናል፤ እግዚአብሔር ኀዘኑን፣ ጸጸቱን አይቶ ያዝንለታል፡፡ (ትምህርተ ሃይማትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፣ ገጽ ፪፻፷፯)

ስሕተት መሥራትን አምኖ፣ ሕግ ማፍረሱን ተገንዝቦ፣ ስላጣው ክብር ስለደረሰበት ቅጣት አስቦ ያዝናል፤ ማዘኑ ስለጥፋቱ ነው፤ ከዚያም ወደ ካህኑ መጥቶ ይናዘዛል፤ እያወ በድፍረት ሳያውቅ በስሕተት የፈጸማቸውን በደሎች ለካህኑ ይናዘዛል፤ መናዘዝ ማለት የሠሩትን ጥፋት ሳይፈሩ ሳይደብቁ ኃጢአትን ይቅር የሚያስብል የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ለተሰጣቸው አባቶች ካህናት ጥፋትን መንገር ነው፡፡

ለካህኑ ነገርን ማለት ደግሞ ለእግዚአብሔር ነገርን ማለት ነው፡፡ ‹‹…ልጄ ሆይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ አትሸሽግ…›› እንዲል፡፡ (ኢያ.፯፥፲፱)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው እንግዲህ ኃጢአት የሠራ ሰው ከተናዘዘ በኋላ ካህኑ እንደ በደሉ መጠን ቀኖና ይሰጠዋል፤ ቀኖና ኃጢአት የሠራ ሰው ምክርና ተግሣጽ አግኝቶ የንስሐ ቅጣት ካሣ የሚከፍልበት ነው፤ አባቶች ካህናት ንስሐ የገባውን ሰው እንዲጾም እንዲጸልይ፣ እንዲሰግድ፣ እንዲመጸውት ያደርታል፡፡ ያንን ፈጽሞ ሲመጣ  በተሰጣቸው  ከኃጢአት የመፍታት ሥልጣን ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› ሲሉ ተነሳኂው ከኃጢአቱ እስራት ይፈታል፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ ይቅርታን ያገኛል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  በሥጋችን ደዌ (ሕመም) ሲገጥመን ስንታመም ደግሞ ፈውስ (ድኅነት) የሚያሰጠን አንዱ ምሥጢረ ቀንዲል ነው፤ ቀንዲል ማለት በዘይት የሚበራ መብራት ዌም ማብሪያ ማለት ነው፤ ካህኑ ለታመመው ክርስቲያን በሚያደርገው ጸሎትና በሚሰጠው ቡራኬ በሚቀባው ቅብዐ ቅዱስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ጸጋ ታማሚው ከደዌ ሥጋ ይፈውሳል፡፡ (ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ ፪፻፸፫)

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹እንዲያስተምሩ እና ሕሙማንን እንዲፈውሱ ባዘዛቸው ጊዜ እያስተማሩ በርኩስ መንፈስ ከተያዙት ላይ አጋንንትን አወጡ፣ ቅዱስን ዘይትም እየቀቡ ሕሙማንን ፈወሱ ‹‹..ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው…›› (ማር.፮፥፲፪)

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ‹‹…ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት፤ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል…›› በማለት ስንታመም አባቶች ካህናት ቅዱስ ቅብዐት  በመቀባት ጸሎት አድርገውልን ሲቀቡን እኛም ከሕመም እንደምንድን አስተምሯል፤ ( ያዕ.፭፥፲፬) ታዲያ ታመን ሥርዓቱ እንዲፈጸምልን ስንመጣ እንደምንድን አምነን ተስፋ አድርገን መሆን አለበት፡፡

ልብ ልንለውና ልንገነዘበው የሚገባው ነገር ቢኖር ክርስትና ስንነሣ የመንፈስ ቅዱስ ማሳደሪያ የሆነው ቅብዐ ሜሮንና ፣ቅብዐ ቀንዲል ልዩነት እንዳላቸው ነው፤ ቅብዐ ቀንዲል (ቅብዐ ቅዱስ) ሰው ሲታመም ከደዌ የሚፈወስበት ነው፤ ቅብዐ ሜሮን ደግሞ የልጅነት ጸጋን ለማግኘት ስንጠመቅ የምንቀባው ነው፡፡ ቅብዐ ቀንዲል (ቅብዐ ቅዱስ) በተደጋጋሚ የሚፈጸም ምሥጢር ነው፡፡

አንድ ሰው ታሞ ከዳነ በኋላ እንደ ገና ቢታመም ቅብዐ ቀንዲሉን ( ቅብዐ ቅዱስን ) ከሕመሙ ለመፈወስ ድጋሚ መቀባት ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ ሥርዓቱን የሚፈጽሙት ወይም ደግሞ የሚቀቡን አባቶች ካህናት ናቸው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹…ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት፤ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሣዋል…›› እንዳለው ሥርዓቱን መፈጸም የሚችሉት ካህናት ብቻ ናቸው፡፡ (ያዕ.፭፥፲፬)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ምሥጢራት በነፍስና በሥጋ ስንታመም የምንፈወስባቸው ናቸው፤ ታዲያ ሁለቱንም ሥርዓት ስንፈጽም ከእምነት ጋር መሆን አለበት ፤አንድ ሰው ስለበደሉ ንስሐ ሲገባ ኃጢአቱ እንደሚሰረይለት አምኖ መሆን አለበት፤ ሲታመም ቅብዐ ቅዱስን ካህናት ሲቀቡት እንደሚድን አምኖ መሆን አለበት፡፡ በጣም ሰፊና ጥልቅ ከሆነም ትምህርት ለግንዛቤ የሚሆነውን ጥቂቱን ብቻ ነው የተመለከትናው! በቀጣይ የአንድነትና የአገልግሎት ጸጋን የሚያሰጡ ምሥጢራትን እንማራለን፤ ቸር ይግጠመን!

በእምነት ጸንተን፣ በምግባር ጎልብተን፣ ሥርዐትን ጠብቀን (አክብረን) በመገኘት የክብር መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ ያድረገን! አሜን!!! ይቆየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!