ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ክፍል ሁለት
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፳፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የዕረፍት ጊዜያችሁ እንዴት ነው? ዕረፍት ማለታችን በመደበኛ ይሰጥ የነበረው የዓመቱ የትምህርት ጊዜ ተገባዶ ፈተና ወስዳችሁ ውጤት ተነግሯችሁ፤ በአዲስ ዓመት ደግሞ ወደ አዲሱ ክፍል ገብታችሁ ለመማር ዝግጅት የምታደርጉበትን የክረምት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ ዕረፍት ሲባል ምንም አይሠራም ማለት አይደለም፤ በዚህ ጊዜ ተጨማሪ ለቀጣዩ የትምህርት ዘመናችሁ ድጋፍ የሚሆን እንዲሁም ደግሞ የተለያየን ተሰጥዖ ለማዳበር በወደዳችሁት ነገር መርጣችሁ እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋችን እሙን ነው፡፡
ታዲያ ከዚሁ ጋር በተጓዳኝ መንፈሳዊ የአብነት ትምህርት መማር አለባችሁ፤ ጊዜያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙ፤ በጨዋታ ብቻ ልታሳልፉት አይገባም፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የክረምት ወቅት ከበድ ያለ ዝናም የሚዘንብበት ወቅት በመሆኑ በእያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ! በባለፈው ትምህርታችን ስለ ሰባቱ ምሥጢራት ምንነት መግቢያውን ተምረናል፡፡ አሁን ደግሞ ስለ ምሥጢራት አፈጻጸም እንማራለን፤ ተከታተሉን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም በመባል ስለሚታወቁት በተማማርንበት ትምህርት በሦስት ክፍል ከፍለናቸው ምን ምን እንደሚባሉ አይተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከሦስቱ ክፍላት አንዱ የሆነውን የልጅነት ጸጋን አዲስ ሕይወትን የሚያሰጡ ምሥጢራትን ምሥጢረ ጥምቀትን፣ ምሥጢረ ሜሮንን፣ ምሥጢረ ቊርባንን እንማራለን፤ እነዚህ ሦስቱ ምሥጢራት በአንድ ጊዜ ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ ይፈጸማሉ፡፡
በመጀመሪያ ጥምቀት ቀጥሎ ሜሮን ከዚያ ቊርባን መቀበል ግዴታ ነው፤ ምእመናን ሁሉ ክርስቲያንነታቸውን የሚያስመሰክሩት በእነዚህ በሦስቱ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስቱ ናቸውና ሦስቱም አንድ ናቸው›› (፩ኛ ዮሐ.፭፥፰) በማለት እንደገለጸው ሦስቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያንነት ማረጋገጫ ምሥክሮች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ (ትምህርተ ሃይማትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ ፪፻፵፯)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የጥምቀት ሥርዓት የሚፈጸመው ተጠማቂው ማየ ገቦ ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ በማለት ነው፤ ይኸውም ምሳሌ አለው ከውኃ ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለታችን ጌታችን በመቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት የማደሩ ምሳሌ መውጣታችን ደግሞ ቤታ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የመነሣቱ ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን እንደተጠመቅን አታውቁምን፤ … ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን…፡፡›› (ሮሜ ፮፥፫-፬)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከተጠመቅን በኋላ ካህኑ ቅብዐ ሜሮን ይቀቡናል ሜሮን ማለት ‹‹ ቅብዐት›› ማለት ነው፡፡ ከጥምቀት ቀጥሎ የሚፈጸም ቅዱስ ቅብዐት ነው፤ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለዳችንን የሚያረጋግጥል ታላቅ ምሥጢር ነው፤ በቅብዐ ሜሮን በሚታይ ሥርዓት አማካኝነት የማይታየውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይሰጥበታል ፤ ሕፃናት ተጠምቀው ቅዱስን ቅባት ቅብዐ ሜሮን) ሲቀቡ የእግዚአብሔርን መንፈስ ጥበብንና ማስተዋልን መንፈሰ ምክርና ኃይልን፣ የዕውቀት፣ እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያድርባቸዋል፡፡ ቅብዐ ሜሮን የሃይማኖትን ምሥጢር፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን፣ መልካምንና ክፉውን ለይተን የምናውቅበት ኃይል ማስተዋል ጥበብን ያስገኛል፡፡ ካህናት አባቶቻችን አጥምቀው ቅብዐ ሜሮን ቀብተው ከዚያም አንገታችን ላይ የክርስትናችን ምልክት የሆነውን ክር ያስሩልናል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሕፃናት ሲጠመቁ የክርስትና አባት ወይም የክርስትና እናት እንዲኖራቸው ታዟል፡፡ የሚጠመቀው ወንድ ከሆነ ወንድ አንሽ (የክርስትና አባት የሚባለው) ተጠማቂዋ ሴት ከሆነች ሴት አንሺ (የክርስትና እናት የምትባለው) ይኖራቸዋል፡፡ ይኸውም በሃይማኖት፣ በሥርዓት እንዲያሳድጓቸው ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የተገራ ልቡና ካላቸው ሲያድጉ ለእግዚአብሔር የተመቹ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በጠቅላላው ከሃይማኖት ከምግባር እንዳይወጡ የሃይማኖት አባትና እናት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከተጠመቅን ቅብዐ ሜሮን ከተቀባን በኋላ እንቆርባለን ቅዱስ ቊርባን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የቆረሰው ሥጋው የፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ ቅዱስ ቊርባን የጌታችንን ማዳኑን የምንቀበልበት ታላቅ የሃይማኖት ምሥጢር ነው፤ ባለፈው ትምህርታችን በስፋት እንደተመለከትነው ቊርባን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፣ እንዲሁም ደግሞ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነው፡፡ (ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ ፪፻፶)
ምሥጢረ ቊርባንን የመሠረተልን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቀድሞ በትምህርቱ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻ ቀን አነሣዋለሁ›› (ዮሐ.፮፥፶፬) በማለት እንዳስተማረው ዐርብ ለእኛ ሲል በመስቀል ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ‹‹እንጀራውን (ኅብስቱን) አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፤ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፤ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው…›› እንዲል፤ (ማቴ.፳፮፥፳፮) ከተጠመቅን ቅብዐ ሜሮን ከተቀባን በኋላ እንቆርባለን፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበላችን የዘለዓለም ሕይወትን እናገኛለን፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ እነዚህ ሦስት ምሥጢራትን ተጠማቂው ሲፈጽም የእግዚአብሔርን ልጅነትን ያገኛል፤ ክርስቲያን ይሆናል፤ እኛም በልጅነታችን ስንጠመቅ (ወላጆቻችንን ክርስትና ሲያሥነሱን) እነዚህ ምሥጢራት ተፈጽመውልናል፡፡ የማስተዋል፣ በጎ ምግባርን የሚያሠራ፣ ከክፉ ሥራ እንድንለይ የሚያደርግን ኃይል አግንተናል፡፡
ታዲያ ይህን ጸጋ መጠበቅ አለብን፤ ክፉ ሥራ በመሥራት፣ ከጽድቅ ሥራ በመራቅ ልናጣው አይገባም፡፡ ክርስቲያን በሁሉ ነገር ጠንቃቃ መሆን አለበት፤ አስተዋይ፣ ጨዋ፣ ለሰዎች የሚያዝን፣ የፍቅር፣ የሰላም የይቅርታ ሰው ሊሆን ይገባዋል፡፡ ታዲያ እኛም በልጅነታችን ክርስትና ስንነሣ ያገኘናቸውን እነዚህን የእግዚአብሔር ስጦታዎች በሥራ ልንገልጣቸው ይገባል፤ መማራችን፣ ማወቃችን ለዕውቀት ብቻ መሆን የለበትም በሕይወታችን መተርጎም (መፈጸም) አለብን፡፡
ቸር ይግጠመን! በእምነት ጸንተን፣ በምግባር ጎልብተን፣ ሥርዓትን ጠብቀን (አክብረን) በመገኘት የክብር መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍቃድ ይሁንልን! አሜን!!! ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!