ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? የክረምትን ወቅት እንዴት እያሳላፋችሁ ነው? በአቅራቢያችሁ ወዳለው ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርት እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፤ ምክንያቱም ትምህርት ተዘጋ ብለን ጊዜውን በጨዋታ ብቻ ልናሳልፈው አይገባም፡፡ ለመጪው የትምህርት ዘመን አዲስ ለምትገቡበት ክፍል ቅድመ ዝግጅት በማድረግ (መጻሕፍትን በማንበብ) ጊዜውን ልትጠቀሙበት ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የክረምት ወቅት ከበድ ያለ ዝናም የሚዘንብበት ወቅት በመሆኑ በእያንዳንዱ ነገር ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ! መልካም! ከዚህ ቀደም በተከታታይ መሠረታዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሥነ ፍጥረት፣ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን ስንማማር ቆይተናል፤ አሁን ደግሞ ስለ ሰባቱ ምሥጢራት እንማራለን!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይመደባል፤ ለዛሬ ወደ ጥልቅ ምሥጢራቸው ከመግባታችን በፊት እነማን እንደሆኑ፣ ለማን፣ እንዴት እንደሚፈጸሙ፣ ማን እንደሚፈጽማቸው እንመለከታለን፤ መልካም ትምህርት!
ሥርዓት ማለት “መሥራት፣ መሠራት፣ አሠራር፣ ሥራት፣ ደንብ፣ አገባብ፣ ሕግ፣ ትእዛዝ፣ ዐዋጅ፣ ፍርድ፣ ልማድ፣ የሥራ መንገድ ማለት ነው፤ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፷፸፹ /678) በመሆኑም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን/የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት/ ማለት የቤተ ክርስቲያን ሕግ፣ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ የቤተ ክርስቲያን የአሠራር መርሐ-ግብር ማለት ነው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሥርዓት ያስፈለገበት ምክንያት ማንኛውም ሥራ ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ነው፡፡ አንድ ሥራ ከየት ተጀምሮ ወዴት እንደሚሄድ ሥርዓት ከሌለው አሠራሩ የተዘበራረቀ ይሆንና ፍጻሜው አያምርም፡፡ እግዚአብሔር እንኳን ዓለሙን የፈጠረውና የሚያስተዳድረው በሥርዓት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አንድ ሐሳብና አንድ ልብ ለመሆን አንድ ዓይነት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ያለ አንድ ዓይነት ሥርዓት መንፈሳዊ አገልግሎትን ማገልገል አይቻልም፤ ምክንያም ሥርዓት ሳይኖር አንዱ ሲጀምር አንዱ የሚጨርስ፣ አንዱ ሲዘምር ሌላው የሚያስተምር ከሆነ መለያየትን ያመጣል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን…›› በማለት እንደገለጸው የአገልግሎቱን አንድነት ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋል፡፡ (፩ኛቆሮ.፲፬፥፵) ብዙ ስንሆን አንድ ልብና አንድ አሳብ የሚያደርገን ሥርዓት ነውና፡፡ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የሐዋርያት ሥራ ላይ ምእመናን በአንድነት ያለግሉ እንደነበር እንደዚህ በማለት ጽፎልናል፤ ‹‹…ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሯቸው…››፤ በሥርዓት ያገለግሉ ነበር፡፡ (የሐዋ.፬፥፴፪)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የሃይማኖት ምሥጢራትን ለመፈጸም ሥርዓት ያስልጋል፤ ለምሳሌ ጥምቀት፣ ቊርባን፣ ተክሊል ….ወዘተ የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ (ሥርዓት) ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲሁም የአፈጻጸሙ ሥርዓት ስለ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቊርባን መሠረተ እምነት የምንገልጽበት ነው፡፡ እንግዲህ ስለ ሥርዓት በጥቂቱ ይህንን ካልናችሁ ሰባቱ ምሥጢራት ቤተ ክርስቲያን የሚባሉት እነማን እንደሆኑ እንመልከት፤ ምሥጢረተ ጥምቀት፣ ምሥጢረተ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቊርባን፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ንስሐ እና ምሥጢረ ቀንዲል ይባላሉ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እነዚህ ምሥጢራት ደግሞ በሦስት ክፍል ይከፈላሉ፤ ምን በመባል መሰላችሁ? አንደኛው ክፍል የልጅነት ጸጋን አዲስ ሕይወትን የሚያሰጡ ምሥጢራት ይባላሉ፤ እነርሱም ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን ናቸው፤ እንዲህ መባላቸው ለምን መሰላችሁ? ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ እነዚህን ምሥጢራ የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሦስቱ በአንድ ቀን ሲፈጸሙ ነው ከእግዚአብሔር ተወልደን አዲስ ሕይወትን እንዲሁም ልጅነትን የምናገኘው፡፡
ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የአገልግሎትና አንድነት ጸጋን የሚያሰጡ ምሥጢራት ይባላሉ፤ እነርሱም ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ክህነት ናቸው፤ ምሥጢረ ተክሊል ደግሞ ሙሽሮች ሲጋቡ የሚፈጸምላቸው ሥርዓት ሲሆን ሁለቱ አንድ አሳብ እንዲያስብ ይሆናሉ የአንድነትን ጸጋ ይቀበላሉ፡፡ ምሥጢረ ክህነት ደግሞ እግዚአብሔር መርጧቸው፣ ለክህነቱ የሚሆነውን ትምህርት ተምረው ሲሾሙ የአገልግሎት ጸጋን ይጎናጸፋሉ፡፡
ሦስተኛው ክፍል ደግሞ ምን ይባላል መሰላችሁ? የነፍስና የሥጋን ቁስል የሚፈውሱ ምሥጢራት ይባላሉ፤ ምን ማለት መሰላችሁ? በሥጋችን ሕመም ሲገጥመን አባቶች ጸሎት አድርገውልን ቅብዐ ቀንዲሉን ሲቀቡን ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ ምሥጢረ ንስሐ ደግሞ የነፍሳችንን ቁስል የሚፈውስ ነው መባሉ ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ ነፍሳቸው ትታመማለች፤ በኃጢአት ባርነት ትያዛለች፤ ታዲያ ይህን ቁስል ለመፈወስ፣ ነጻ ለመውጣት ንስሐ ይገባሉ፤ ይድናሉ፡፡ (ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ገጽ ፪፻፵፭)
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በውስጣቸው ስላለው (ስለምናገኘው) ጸጋ በመጠኑ ተመልከተናል፤ ሌላው እነዚህ ምሥጢራት የሚደገሙና የማይደረሙ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚፈጸሙ፤ እንዲሁም ደግሞ ምእመናን ሁሉ የግድ የሚፈጽሟቸው የትኞቹ እንደሆኑ እንመልከት፡፡
- ምእመናንን ሁሉ የግድ የሚፈጽሟቸው የሚባሉት
ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቊርባን
- የሚደገሙ ምሥጢራት
ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ቊርባን፣ ምሥጢረ ቀንዲል
- የማይደገሙ ምሥጢራት
ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል
- የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚፈጽሟቸው ምሥጢራት
ምሥጢረ ክህነት፣ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ለዛሬ ይህንን ተመልክተናል፤ በቀጣይ ትምህርታችን በዝርዝር በመጠኑ እንመለከታቸዋልን፤ በሥርዓትና በአግባብ ልንኖር ያስልጋል፤ ሥርዓት የሚጀምረው ከቤታችን ነው፤ የወላጅን ምክር በመፈጸም፣ በመታዘዝ፣ ሥርዓት ይዘን በመኖር ከዚያም ከፍ እያልን ስንመጣ እንደ ዓቅማችን የቅድስናን ሥራ በመሥራት ልንኖር ይገባናል፡፡
ቸር ይግጠመን! በእምነት ጸንተን፣ በምግባር ጎልብተን፣ ሥርዓትን ጠብቀን (አክብረን) በመገኘት የክብር መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ ያድርገን! አሜን!!! ይቆየን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!