ሰበር ዜና ከአሰቦት ገዳም

መጋቢት 12/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የአብነት ተማሪው በታጣቂዎች ተገደለ

በምዕራብ ሐረርጌ ሜኤሶ ወረዳ በአሰቦት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም የአብነት ተማሪ የሆነው የ7 ዓመቱ ሕፃን ናታን አንበስ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በ3 ጥይት ተመትቶ መገደሉን የገዳሙ ዋና መጋቢና ምክትል አበምኔት አባ ዘወልደ ማርያም ገለጹ፡፡ ከአባ ሳሙኤል ገዳም በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ላይ ከእናቱ ጋር ወደ ገዳሙ በመውጣት ላይ እያለ ከእናቱ እጅ ቀምተው በመውሰድ ፊት ለፊቷ በሦስት ጥይት ገድለውት ሊያመልጡ ችለዋል፡፡ በእናትየው ጩኸትና በጥይት ድምጽ የተደናገጡት መነኮሳት ገዳዮቹን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 

የገዳሙ መነኮሳት እንደገለጹት ጉዳዩን ለፖሊስ በስልክ ያሳወቁ ሲሆን ፖሊስ “መኪና አግኝተን እስክንመጣ ድረስ ሟቹን  ቅበሩት” በማለታቸው ከቀኑ 8፡00 አካባቢ ሊቀበር ችሏል፡፡ ባቲ በተባለው አካባቢ በአሰቦት ቅድስት ከሥላሴ ገዳም ጀርባ ከሚገኘው አካባቢ ታጣቂ አርብቶ አደሮች ተሰባስበው ወደ ገዳሙ በመቃረብ ላይ መሆናቸውንና መነኮሳቱ ስጋት ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸውልናል፡፡

 

መጋቢት 1 ቀን ባቀረብነው ዘገባ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች እሳቱን በሚያጠፉት ምእመናን ላይ ተኩስ ከፍተው እንደነበርና የፌደራል ፖሊስ አባላት ምላሽ ሰጥተው ከአካባቢው እንዳራቋቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡