“ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ፡፡”
ጥር 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ሰሎሞን መኩሪያ
ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ቁ.6
በረከቱ ይደርብንና ይህንን ቃል የተናገረ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጅ የሆነው ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በብሉይ ዘመን በቅዱስ ዳዊት ሕይወት የተከወነውን በምስጢር ስቦ አምጥቶ የሰማዕታትን ክብር አጎልቶ ተናግሮበታል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትን እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል አነገሠው፡፡ በዙሪያው የነበሩ ኤሎፍላዊያንን አጥፍቶ ደብረ ጽዮንን /መናገሻ ከተማውን/ አቅንቶ ሲኖር ከዕለታት አንድ ቀን ዳዊት ታመመ፡፡የዳዊትን መታመም ሰምተው፣ ካሉበት ተነስተው የዳዊትን ከተማ በተለይም ቤተልሔምን ከበቧት፡፡ ዳዊት ይህ ሰምቶ “ወይ እኔ ዳዊት! ድሮ ታመምሁና ጠላቶቼ ሰለጠኑ ሲል የኀያላኑን ልቦና ለመፈተን ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች ሦስቱ ማለትም አዲኖን፣ ኢያቡስቴ ኤልያና ረዋታቸውን /የውኃ መያዣ/ ይዘው፣ ጦራቸውን አሰልፈው፣ ጠላቶቹን ድል ነስተው፣ ዳዊት ሊጠጣ የወደደውን ውኃ አመጡለት፡፡ቅዱስ ዳዊትም ያንን ውኃ አፈሰሰው “ለምን አፈሰስከው?” ቢሉት “ደማችሁን መጣጠት አይደለምን?” ብሎ፤ ይህም ከጽድቅ ገብቶ ተቆጠረለት፡፡ 2ሳሙ.23፥13-17
አባቶቻችን ይህንን ሲያመሰጥሩት የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ አባታችን አዳም ከተድላ ገነት ወደ ምድረ ፋይድ፥ ከነጻነት ወደ መገዛት፥ ከልጅነት ወደ ባርነት፥ በወረደና ፍትወታት እኩያት ኀጣውእ በጠላትነት በተነሱበት ጊዜ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተገኘ ከጌታ ጎን የተገኘ ማየ ገቦ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ የትሩፋት አበጋዞች ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ፈጥነው ተነሱ፡፡ በአጋንንት ከተማ ተዋጉለት ይጠጣው ዘንድ የወደደውን ማየ ገቦ አመጡለት፡፡ ማለትም የአዳም ልጅነት በከበረው የክርስቶስ የደሙ ፈሳሽነት የሥጋው መሥዋዕትነት ተመለሰለት፡፡ ይህንን ለአዳምና ለልጆቹ የባህርይ አምላክ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ እያሰቡ ሰማዕታት በእግዚአብሔር ፍቅር ተቃጥለው “እግዚአብሔርን ካዱ ለጣዖት ሰገዱ” ሲባሉ “እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም” ብለው ደማቸውን አፈሰሱ ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፡፡ /ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ ዘሐሙስ/
“ሰማዕት” ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ ይህ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ማፍሰስ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፥ የዳዊት ወታደሮች ስለ ዳዊት ፍቅር ብለው “ደማችን ይፍሰስ” እንዲሉ፤ ዳዊትም ያመጡለትን ውኃ መጠጣት ደማችሁን እንደመጠጣት ነው ብሎ በፍቅር ምክንያት ውኃውን እንዳፈሰሰው፥ ይህም ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት፥ የእግዚአብሔር ወዳጆች የሆኑ ቅዱሳን ሰማዕታትም እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር ሃይማኖት የሆነችው እውነተኛይቱን ሃይማኖት ወደው ደማቸውን አፈሰሱ፣ አጥንታቸውን ከሰከሱ፣ ስለዚህ እንደ ፀሐይ አብርተው በሰማያት ዛሬም ስለ እኛ እየማለዱ አሉ፡፡ “ለመሆኑ ከዚህ ክብር የደረሱት እንዴት ነው?” ብሎ ለሚጠይቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሲመልስ ሦስት ነገሮችን ያነሣል፡፡
1. “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ” ይላል
ዓለም እንደየዘመኑ የተለያየ ጠባይ አላት፤ ልክ እንደ እስስት ትለዋወጣለች፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ከእውነት ይልቅ ሐሰት፥ ከፍቅር ይልቅ በእውነተኞቹ ላይ ጥላቻ፥ በግልጽ ይታይባታል፡፡ የራሷ የሆነውን እጅግ አድርጋ ትወዳለች ስለዚህም በተለያየ መረብ እያጠመደች ለዘለዓለሙ ትጥላለች፡፡ “ሰማዕታት” /ምስክሮች/ ግን የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ማለትም እውነት እግዚአብሔርን፥በሐሰት ጣዖት አልለወጡም ስለዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ በክብር ተቀምጠው ስለ እኛ እያማለዱ አሉ፡፡ ትምህርታችንን የበለጠ ግልጽ እንዲያደርግልን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሸዋ ቁጥራቸው ከበዛ በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ካላቸው ቅዱሳን ሰማዕታት መካከል የሰማዕታት አለቃ ተብሎ በፈጣሪው በእግዚብሔር ዘንድ ስለተሾመው ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጋድሎ ሕይወት ጥቂት እንመለከታለን፡፡
በረከቱ ይደርብንና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአባቱ ስም ዘሮንቶስ የእናቱ ስም ቴዎብስታ ይባላል፡፡ አባቱ በፍልስጥኤም አገር መስፍን ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሕፃን ሳለ አባቱ በሞት ተለየው ከዚያ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሹመት ለመቀበል ወደ ዱድያኖስ ንጉሥ ዘንድ ሄደ፡፡ ንጉሡም ጣዖት አቁሞ ጣዖትን እንዲያመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡ ይህንን አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ፤ በእርሱ ዘንድ ያለውን ለንጉሡ እጅ መንሻ ያመጣውን ገንዘቡን ለድሆች እና ለምስኪኖች ሰጠ፡፡ ባሮችንም ነጻ አወጣቸው ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ “በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ በግልጽ እኔ ክርስቲያን ነኝ” አለ፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡ ዱድያኖስ በዘመኑ ከነበሩ በሥልጣኑ በሥሩ ከሚተዳደሩ 70 ነገሥታት ጋር ሆኖ አባብለው እግዚአብሔርን እንዲክድ ለጣዖት እንዲሰግድ ይህንን ቢያደርግ ብዙ ብር እና ወርቅ እንደሚሰጠው ከእርሱም በታች ባለ ሥልጣን እንደሚያደርገው ቃል ገባለት፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ይህንን አልተቀበለም፡፡ በፊቱ ናቀው እንጂ ጌታ በቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል” ማቴ.16፥26 እንዳለ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በወጣትነቱ እግዚአብሔርን ክዶ ለጣዖት ሰግዶ የሚያገኘውን ወርቅ እና ብር እንዲሁም ሥልጣን ናቀ፡፡ ይህ እግዚአብሔር ለማገልገል በሕይወቱ ያሳየውን ቆራጥነት እራስን መካድን ያሳየናል፡፡ ማቴ.16፥24፡፡ ከዚህ ቅዱስ ሕይወት ተምረን እኛም በዓለም ውስጥ ከሚሠራው የኀጢአት ሥራ በንስሐ ሕይወት በጽድቅ ሥራ መለየት ይገባናል በዘመናችንም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓለምን ጣዕም መናቅ ማለት እውነትን በሐሰት አለመለወጥ ማለትም እውነተኛ ሆኖ መገኘት የሚበላውን ከማይበላው ጋር ቀጥቅጦ አለመሸጥ በሚዛን አለመበደል ፍርድ አለማጉደል ጉቦ ተቀብሎ ድኃ አለመበደል በምንሠራበት መሥሪያ ቤተ ሰነድ አለመሰረዝ አለመደለዝ ባጠቃላይ በሕይወታችን በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ በእውነት ታምነን መገኘት ይገባናል፡፡ ለዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ምልጃ ይርዳን፡፡
2. ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ
እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ዱድያኖስ ንጉሥ የዚችን ዓለም ጣዕም አቅምሶ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማባበል ለጣዖት ማሰገድ በተሳነው ጊዜ የወሰደው እርምጃ በዘመኑ በነበረው የተለያየ መሣሪያ ተጠቅሞ የቅዱስ ጊዮርጊስን ደም ማፍሰስ ነበር፡፡ በገድለ ጊዮርጊስ እንደተጻፈ ለቆመው የወርቅ ምስል አልሰግድም እነርሱንም አላመልክም ይልቁንም ዐይን እያላቸው የማያዩ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ እጅ እያላቸው የማይዳስሱ እግር እያላቸው የማይሄዱ በአፋቸው ትንፋሽ የሌለ ግዑዛን ናቸው፡፡ እነርሱን የሚያመልኩ እንደነርሱ ይሁኑ ብሎ በቅዱስ ዳዊት ቃል ንጉሡን እና ጣዖታቱን በዘለፈ ጊዜ መዝ.113፥12-16 ዱድያኖስ ንጉሥ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስገረፈው በተገረፈ ጊዜ ደሙ እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከዚያም ጨለማው ጥልቅ ወደ ሆነ የእስር ቤት ጣሉት፡፡ ዱድያኖስና ሰባው ነገሥታት በዚህ መከራ ይሞታል የእርሱን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የተመለከቱ ሌሎች ሰዎችም በመፍራት በእኛ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት ፀንተው ይኖራሉ ብለው አስበው ነበር፡፡
ነገር ግን የቅዱስ ጊዮርጊስን መከራ መቀበል የደሙንም መፍሰስ የወደደ ይህንንም ለክብር ሊያደርግለት ፈቃዱ የሆነ ቅዱስ እግዚአብሔር በግርፋቱና በደሙ መፍሰስ እንዲሞት አልተወውም ስለዚህ ወደ እስር ቤቱ የጨለማውን ጥልቀት በብርሃን የሚገልጥ ቁስሉንም የሚፈውስ የሚያጽናና መልአክ ላከለት፤ መልአኩም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብቶ ቁስሎቹን ፈወሰ፤ እርሱንም አጽናንቶ ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ ያደረገለት ያለውን ሁሉ በግልፅ ነግሮት በክብር አረገ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ሲነጋ የዱዲያኖስ ወታደሮች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጡ ጊዜ ምንም የግርፋትና የደም መፍሰስ ምልክት ባላገኙ ጊዜ፣ ይልቁንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አግኝተው ተደነቁ፡፡ ከዚያም “እኛም በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እናምናለን፡፡” ብለው ብዙ ሰዎች ሰማዕትነት ተቀበሉ፡፡አንድ ዛፍ በተቆረጠ ጊዜ ከስሩ ብዙ ችግኝ እንዲገኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ መከራ መቀበል ብዙ ሰዎች ወደ ሃይማኖት መጡ፡፡
3. ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ
ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲህ ያለውን ተአምት በማድረግ ብዙ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ የተመለከተ ዱድያኖስ አሁንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የሚደርሰውን የመከራ ስልት በመቀያየር አትናስዮስ የተባለ ጠንቋይ አስመጥቶ መርዝ በጥብጦ እንዲጠጣ አዘዘ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የቀረበለትን መርዝ በሰው ሁሉ ፊት በትእምርተ መስቀል አማትቦ ባጣጣመ ጘራራ የሆነውን የሞት ጽዋ ተጎንጭቶ ከባድ መከራ ተቀብሎ እንዲሞት የእግዚብሔር ፈቃዱ ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስን ክብር እርሱን ፍፁም መውደዱን ለመግለጽ አምላካችን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርምን ባለሟሎቹ ቅዱሳን መላእክትን ወዳጆቹ ነቢያት ሐዋርያት ቅዱሳንን አስከትሎ አፅሙ ወደ ተዘራበት ወደ ይድራስ ተራራ ወረደ በክብር ወረደ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልን አዘዘው የተበተነው የወዳጄን የቅዱስ ጊዮርጊስን አፅም ስብሰባህ አምጣ አለው እርሱም እንደታዘዘው ሰበስቦ ወደ ጌታችን አቀረበ ያን ጊዜ ጌታችን በምሕረት እጁ ተቀብሎ አዳምን የፈጠሩ እጆቼ አንተንም የፈጠሩ አሁንም ወዳጄ ጊዮርጊስ እኔ አዝዤአለሁ ከሞት ተነሣ አለው፡፡ ያን ጊዜ ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሸራ አምሮበት ከሞት ተነሣ ጌታችንም በአፍ መሳም ሳመው የሚጸናበትን ቅዱስ መንፈሱን አሳደረበት ከዚያም ሊቀበለው ያለውን መከራ የሚያገኘውን ዋጋ ነግሮት በክብር አረገ፡፡
ይህ የሆነው ጥር 18 ቀን ነው፡፡ ይህንን መራራ ሞት በእሳት መቃጠል በመንኮራኩር መፈጨት እንደ እህል መዘራት ታግሶ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተደረገለት ተአምራት ከሞትም በመነሣቱ ብዚ ሰዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምነው ወደ እውነተኛይቱ ሃይማኖት ተመልሰዋል፡፡ እንግዲህ በገድሉ መጽሐፍ እንተጻፈ ለ7 ዓመት መራራ መራራ የሆነ ብዙ መከራዎችን ታግሶ በስተመጨረሻ በሰይፍ ተከልሎ /አንገቱን ተቆርጦ ከአንገቱም ደም ውኃ ወተት ፈሶ ለተጋድሎው 7 የድል አክሊል ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበለ የከበረ ቃል ኪዳን የተቀበለ ሰማዕት ነው፡፡ እኛም ከዚህ ቅዱስ ገድል ተምረን አሰረ ፍኖቱን በመከተል ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እንድናጸና ዘመኑ የሚጠይቀውን ሰማዕትነት ምግባር ማቅናት እንድናቀና የሠማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎትና ቃል ኪዳን ተራዳኢነት አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች የክብርት እመቤታችን አማላጅነት የቅድስት ሥላሴ ቸርነት አይለየን አሜን፡፡