ሰሙነ ፋሲካ (ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ)

በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ የሚጠሩ ሲኾን፣ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

ሰኞ

የትንሣኤው ማግሥት ሰኞ ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሰትኾን፣ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

በዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ሰኞ ደግሞ ገበሬው፡- ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ዅሉ፤ ሴቶቹ፡- ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለ ኾነች ‹እጅ ማሟሻ ሰኞ› ትባላለች፡፡

ማክሰኞ 

የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ሐዋርያው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹እኔ ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ ቶማስ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡ 

ረቡዕ 

ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ትኾን ዘንድ፤ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡ 

ኀሙስ 

ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡

ዐርብ

ከሆሣዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ ደግሞ የጌታችን ዐርባው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት ዕለት በመኾኗ በቤተ ክርስቲያን ‹ተጽዒኖ› ትባላለች፡፡ የከባድ ሥራ ማቆሚያ (ማብቂያ) ዕለት በመኾኗም በሕዝቡ ዘንድ ‹የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ› ትባላለች፡፡

ዳግኛም በመጀመርያ የሰው ልጆች አባትና እናት የኾኑት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፤ በኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም ስለ ተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለ ፈጸመባት ‹ዕለተ ስቅለት፣ አማናዊቷ ዐርብ› ትባላለች፡፡

የሰሙነ ፋሲካዋ ማለትም የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ስትባል፣ በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችን ከዅሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ ኾና ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡

የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ

በዚህች ሰንበት ከላይ እንደ ተጠቆመው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!» ብሎ ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡

በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግንሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ «ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!» በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡

ቶማስንም «ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤» ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ» አመነ፡፡ ስለዚህም ማለትም የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ፋሲካ የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዅሉ ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡