ሰሙነ ሕማማት (ከሰኞ እስከ ረቡዕ)

በመ/ር ኃይለ ማርያም ላቀው

ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ስለ ተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ የተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኃኔ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት ስለሚነገርበት ‹ቅዱስ ሳምንት› ይባላል፡፡ በተጨማሪም ‹የመጨረሻ ሳምንት› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመኾኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ መኾኑ ይነገራል፡፡ ‹‹ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ. ፶፫፥፬-፲፪)፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መኾኑን በመዘከር፤ ከማንኛውም የሥጋ ሥራ በመታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር ሰሙነ ሕማማትን ልናከብር ይገባል፡፡ ብድራትን የማያስቀረው አምላካችን እግዚአብሔር መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎናልና፡፡

ሰሙነ ሕማማት አስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከዐቢይ ጾም ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተከታለው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን (ኦርየንታል) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን ዐርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ ከእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሰኞ

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አከናውኗል፤ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ ‹‹በማግሥቱ ተራበ›› የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤›› ይላል (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበር፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፡- ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው፤›› ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ ‹‹ተራበ›› ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መኾኑን ለማጠየቅ ‹‹ተራበ›› ተባለ፡፡ ‹‹በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› ብሏል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ ‹‹አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፤›› ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤›› ይለናልና እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደ ኾነ ተናግሯል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?›› ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘላለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡

ማክሰኞ

በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማርቆስ ወንጌል ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ወንጌል ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ የትምህርት ቀን ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡

ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

 ረቡዕ

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፤

  • አንደኛ የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ  ተማክረዋል፤
  • ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
  • ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ሲኒሃ ድርየም› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማቷል፡፡

ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡

‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፤ ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለ ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፬-፮፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አዲስ አበባ፡፡