ሰሙነ ሕማማት(ለህጻናት)
ሚያዚያ 1/2004 ዓ.ም.
በአዜብ ገብሩ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? እንኳን ለሰሙነ ሕማማት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ልጆች ሰሙነ ሕማማት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላች? ሰሙነ ሕማማት ከትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሲሆን በዚህ ሳምንት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የሰው ልጆች ለማዳን ሲል የተቀበለውን መከራ ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ሳምንት ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል፡፡ እስኪ ልጆች ቀናቱንና በቀናቱ ውስጥ የተፈጸሙትን ተግባራት በዝርዝር እንመልከት፡-
1. እሑድ /ሆሣዕና/፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርቦ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች በተለይም ሕፃናት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ብለው እየዘመሩ ጌታችንን አመስግነውታል፡፡
2. ሰኞ፡- ይህ ዕለት የሆሣዕና ማግስት ሲሆን በዚህ ዕለት ጌታችን ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን አከናውኗል፡፡
- ጌታችን እርቦት ስለነበር ወደ አንዲት በለስ ሄደ፡፡ በለሷ ግን ቅጠል ብቻ ሆና ፍሬ አላገኘባትም ነበር፡፡ ያቺ በለስም ዳግመኛ ፍሬ እንዳታፈራ ረገማት፡፡
- ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ሰዎች አስወጣቸው፡፡
– ልጆች በዚህ ዕለት ማር.11÷12-19 እና ሉቃ.19÷45-46 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ፡፡
3. ማክሰኞ፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ስለሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ የጠየቁትም የካህናት አለቆች ነበሩ፡፡ ጌታችን በዚህ ምድር በነበረበት ወቅት ብዙ ተአምራትን አከናውኗል፡፡ የታመሙትን ፈውሷል፣ የተራቡትን መግቧል፣ …፡፡ እናም የካህናት አለቆች ይህን ሁሉ ተአምር በምን ሥልጣን እንደሚያደርግ ነበር የጠየቁት፡፡ ልጆች በዚህ ጥያቄ መሠረት ጌታችን ቀኑን ሙሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ረጅም ትምህርት አስተምሯል፡፡
– በዚህ ዕለት ማቴ.21÷23፣ ማር.11÷27፣ ሉቃ.20÷1 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ እሺ፡፡
4. ረቡዕ፡- በዚህ ዕለት ሦስት ነገሮች ተደርገዋል፡-
- የካህናት አለቆች ጌታን ሊሰቅሉት ተማክረዋል
- ጌታ በስምዖን ቤት ተገኝቶ ሳለ አንዲት ሴት ሽቶ ቀብታዋለች፡፡
- ይሁዳ የተባለው ሐዋርያ ጌታን ለካህናት አለቃ አሳልፎ ለመስጠት በ30 ብር ተስማምቷል፡፡
– በዚህ ዕለት ማቴ.26÷3-16፣ ማር.14÷1-11፣ አና ሉቃ.22÷1-6 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ እሺ፡፡
5. ሐሙስ፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
- ጌታ የሐዋርያትን እግር አጠበ
- የቊርባንን ሥርዓት ሠራ
- በዮሐንስ ወንጌል ምራፍ 17 ላይ ያለውን ረጅም ጸሎት በጌቴ ሴማኒ ጸለየ፡፡
- በዚህ ዕለት ሌሊት ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለካህናት አለቆች ሰጠው፤ ወታደሮችም ያዙት፡፡
– በዚህ ዕለት ዮሐ.18÷1-12፣ ሉቃ.22÷7-53፣ ማቴ.26÷17 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ፡፡
6. ዐርብ፡- ይህ ዕለት “ስቅለተ ዐርብ” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዕለት የተለያዩ ድርጊቶች በጌታችን ላይ ተፈጽመዋል፡፡
- የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ በማለቱ በጲላጦስ ፊት በሐሰት ከሰሱት፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን ስለ እኛ ሲል ተሰቀለ፡፡ በሰዎች ፈንታ ሞትን ተቀበለ፡፡
– በዚህ ዕለት ማቴ.27÷1-60 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንበቡ፡፡
እንግዲህ ልጆች በሰሙነ ሕማማት በእያንዳንዱ ዕለት የተፈጸሙትን ተግባራት በደንብ ተረድታችሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሂዱ፡፡ የሰሙነ ሕማማት ጸሎት ያለበት መጽሐፍ ይዛችሁ ሥርዓቱን በደንብ ተከታተሉ፡፡ በየዕለቱ የሚነበበውን የወንጌል ክፍል አንብቡና ያልገባችሁን ታላላቆቻችሁን ጠይቁ፡፡ አቅማችሁ የቻለውን ያህል ስግደት ስገዱ፡፡ በሉ እንግዲህ ልጆች መልካም የሰሙነ ሕማማት ሳምንት ይሁንላችሁ እሺ፡፡ ደህና ሁኑ ልጆች፡፡