በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ሰላም ማለት ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል፡፡ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሰላምን ሻት ተከተላትም” ብሎ ከመናገሩ አስቀድሞ የመጽሐፉን ክፍል ወደ ኋላ መለስ ብለን የተነሳንበትን ኃይለ ቃል ሙሉ አሳቡን ለመረዳት ስንመለከተው እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካንም አድርግ ሰላምን ሻት ተከተላትም” ይላል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሰላምን የምንሻበትን ምክንያት በዚሁ በተመለከትነው ኃይለ ቃል ላይ ገልጦታል፡፡ እንደ አባትነቱ እግዚአብሔር ልጆቹ ለምንሆን ለእኛ ሊያስተምረን የፈቀደለትንና እርሱ በሕይወቱ ገንዘብ አድርጎት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተመረጠበትን ጥበብ ለእኛም ሲያካፍለን “እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁአለ፡፡ምክንያቱም እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ይልቅ ቀዳሚ ነውና፡፡ ለዚህም ነው አባትና ልጅ ተባብረው(ተቀባብለው) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የነገሩን(መዝ. 111፥10፣ምሳ.1፥7፣9፥10)፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ በሕይወታችን እግዚአብሔርን መፍራት ትርጉም ላለው ሕይወት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላምን የምንሻበት መንገድ እሱ ነውና፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን መፍራት ሕይወትን የሚያስገኝና በጎ ዘመንን ለማየት የምንችልበት የጥበብ  (የዕውቀት) ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ይህንንም ከገለጸ በኋላ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? ብሏል፡፡ ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ቀጥለን በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡

                                                                                                       ፩ኛ አንደበትን ከክፉ መከልከል

የሰው ልጅ በልቡ ያሰበውን በአንደበቱ ይናገራል፡፡ በልብ የታሰበውን መልካምም ይሁን ክፉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ነገር ግን የታሰበው ነገር በውጫዊ ሰውነት ላይ በሚታዩ ምልክቶች  (ገጽን በማየት) መታወቅ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም በአንደበት ቢነገርና በሥራ ቢተገበር ሰዎች ይረዱት ይሆናል፡፡

ይሁንና አንደበትን ከክፉ ካልከለከሉት ሰዎችን የሚጎዳና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የማለፍ በዚያም ሰበብ ተናጋሪውን ሳይቀር ሁለተኛውን አካል በቁጣ በመጋበዝ ለሞት የማብቃት ዕድል አለው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ምላስ እሳት ናት እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት ሥጋችንን ትበላዋለች ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች” ይላል፡፡

ስለዚህ ሕይወትን የሚፈቅድና በጎ ዘመንን ለማየት የሚፈልግ ሰው አንደበቱን ከክፉ ነገር መከልከልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ተናግሮ ሰውን ላለማስቀየምና ላለማስከፋት መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሌላውንም ሰው ወደ ጥፋት ላለመምራት ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ አንደበት ኃያል ነውና ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል የሚል አባባል እንዳለ እናስታውሳለን፡፡

አንደበትን ከክፉ ካልከለከልነው ስድብንና ሐሜትን እናበዛለን፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት ጎዳና የሚያወጣ ክፉ ተግባር ነው፡፡ በጓደኛ መካከል፣ በባልና ሚስት መካከል፣ በአንድ ሀገርና በሌላው ሀገር መካከል፣በጎሳና በጎሳ መካከል ፣ በጎረቤትና በጎረቤት መካከል ሐሜትና መነቃቀፍ፣ ስድብና ጥላቻ ካለ በጎ ዘመንን ማየት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕይወትንም ሆነ በጎ ዘመንን ለማየት አንደበትን ከክፉ መከልከልና በጎ ነገርን ማውራት አስፈላጊ ነው፡፡

                                                                                  ፪ኛ. ከክፉ መሸሽ

ከክፉ መሸሽ ማለት ክፉን ከማድረግ መቆጠብና ክፉ ከሚያደርጉት ጋር በክፋታቸው አለመተባበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ሁል ጊዜም ቢሆን ከክፉዎች ጋር ኅብረት የለውም አባታችን ያዕቆብ ልጆቹን በሚመርቅበት ጊዜ ክፉ ሥራ ከሠሩ ከልጆቹ የክፋት ሥራ ጋር እንደማይተባበርና ከክፋት ጋር ኅብረት እንደሌለው ገልጧል፡፡ “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመጽን ፈጸሟት በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው አሳቤም በአመጻቸው አትተባበርም በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቆርጠዋልና ቁጣቸው ርጉም ይሁን ጽኑ ነገርና ኩርፋታቸውም ብርቱ ነበርና በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ” (ዘፍ.49፥5)

ያዕቆብ ምንም እንኳ በሥጋ የወለዳቸው ልጆቹ ቢሆንም በፈጸሙት ክፉ ሥራ ግን እንደማይተባበር ከክፉ ሥራቸው የራቀና ከክፋት የተለየ መልካም አሳብ እንዳለው ገልጧል፡፡ ዛሬም ቢሆን የሰው ልጆች ክፋትና በደል እየበዛ ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔር ልጆች ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከውሸት፣ ከሌብነት፣ ከቅሚያ፣ ከዝርፊያ፣ ከጭካኔ፣ ከሴሰኝነት፣ ከዘማዊነት፣ ከዘረኝነት በአጠቃላይ ለራስም ለሀገርም ከማይበጁ እኩይ ምግባራትና ከሚፈጽሟቸው ሰዎች ጋር መተባበር የለብንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ሕይወትን ለማግኘት የምንሻና በጎ ዘመን ለማየት የምንፈልግ ሁሉ ከክፉዎች ጉባኤ መለየትና አለመተባበር ያስፈልጋል፡፡

                                                                                             ፫ኛ. መልካም ማድረግ

ሕይወትን ለማግኘትና በጎንም ዘመን ለማየት የሚሻ ሰው ሁሉ መልካምን ሁሉ ሊያደርግ ያስፈልገዋል፡፡ ከክፉ መሸሻችንና ከከፉዎች ጋር አለመተባበራችን መልካም ሥራ ለመሥራት መሆን አለበት እንጂ  ከሥራ ርቀን እንዲሁ እንድንኖር አይደለም፡፡ያለ በጎ ሥራ መኖር ስንፍና ነውና፡፡

እግዚአብሔር የሰውን ውድቀቱንና መጥፋቱን የማይሻ አምላክ ስለ ሆነ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በክፉ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ሁሉ ሊመለስና በሕይወት ሊኖር ይገባዋል፡፡ በቀደመው ስሕተቱ ወንድሙን ያሳዘነ፣ሰው የገደለ፣አካል ያጎደለ፣ ግፍን የፈጸመ፣የድሃውን ገንዘብ በተለያየ ሰበብ የዘረፈ፣ጉቦ የተቀበለ፣በነዚህና መሰል እኩይ ሥራዎች ሀገሩን የጎዳ፣ እግዚአብሔርን የበደለ ሁሉ ከልብ በመጸጸት በልቅሶና በዋይታ ወደ እገዚአብሔር መመለስ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም  አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ አድሮ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንዳለበት አስገንዝቦናል፡፡

“እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው (በደለኛው) ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከከፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለምንስ ትሞታላችሁ? (ሕዝ.33፥11) እንዲል፡፡

እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮ እንደ ነገረን በደለኛ ሰው በበደሉ ቀጥሎ መጥፋት የለበትም፡፡መመለስና በሕይወት መኖር ያስፈልገዋል እንጂ፡፡ እሱም እንደ በደሉ ዓይነት የቅርታ ጠይቆ፣ ንስሓ ገብቶ፣ የበደለውን ክሶ፣ የሰረቀውን መልሶ፣ የሰበረውን ጠግኖ፣ ያጎደለውን መልቶ በፍጹም መጸጸት ሊመለስና መልካም በመሥራት ሌት ተቀን ከሚተጉት ጋራ በመልካም ሥራ ሊተባበር ያስፈልገዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ስለዚህ ሐሰትን ተውአት ሁላችሁም ከመንገዳችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ እኛ አንድ አካል ነንና አትቆጡ አትበድሉም ፀሐይ ሳይጠልቅም ቊጣችሁን አብርዱ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም” (ኤፌ. 4፥25) ይላል፡፡

                                                        ሰላምን መሻት

ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው፡፡ ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል፡፡ በአይነቱ ሰላምን በሁለት መልኩ እናየዋለን፡፡ እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ብለን እንመድበዋለን፡፡

የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊ ሰላምም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሐት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋትና ወዘተ ነጻ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል፡፡ ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል፡፡ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ከሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን መኖር ነው፡፡ በመሆኑም ሰላም ከጥል፣ ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው፡፡  ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

 

የሰላም መገኛ

ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል፡፡ እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ. 15፥33)፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል፡፡ “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥6) እንዲል፡፡

ዓለም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያህል ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ይኖር የነበረ ሲሆን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ መሞትና መነሣት እውነተኛውን ሰላም አግኝቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ሞት ምክንያት ፍርሐት ጸንቶባቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት “ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም (ዮሐ.14፥27) በማለት ፍርሐትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን፣ ሁከትን፣ መረበሽን የሚያርቀውን (የሚያስወግደውን) እውነተኛውን ሰላም አደለን፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል፡፡ መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን ሻት ካለ በኋላ ተከታላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት የራሳችን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የነገረን፡፡በሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተሰማ ያለው የሰላም ዜና፣እየዘነበ ያለው ሰላም ፣እየተጠረገ ያለው የሰላም መንገድ ለዚሁ ማሳያ ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ተራርቀው የነበሩ ሁለት አካላት የሚያለያያቸውን የጥላቻ ድንበር አፍርሰው የሚያገናኛቸውን የፍቅር ድልድይ መመሥረት አንዱ የሰላም መንገድ የሰላም መገለጫ ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን አባቶችም ስንመጣ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ተለያይቶ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነቱን እንደ ውበት ቆጥሮ ወደ መቀራረብና ወደ አንድነት ጉባኤ ለመምጣት የዘረጋው የሰላም መድረክ አንዱ የሰላም መገለጫ ነው፡፡ስለዚህ እንደ ግል ከራስ ጋር ተስማምቶ፣እንደ ሀገር በሀገር ውስጥ ካሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ተግባብቶ መኖር የሚያስችሉትን የፍቅር መረቦች መዘርጋት የሰላም መንገድ፣ ሰላምን መሻትና መከተል ነው፡፡

የእግዚአብሔር ሰላም ለሁላችን ይሁንልን፡፡ አሜን

ምንጭሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት  ቁጥር 3 ሐምሌ 2010ዓ.ም